Thursday, October 8, 2015

ዚቅ ወመዝሙር አመ ፴ ለመስከረም

  
 እንኳን ለዘመነ ጽጌ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ በቤተክርስቲያናችን ዘመነ ጽጌን እና የእመቤታችንን ስደት አስመልክቶ ለሚቀጥሉት 6 እሑዶች (መስከረም ፴ ጥቅምት፯ ጥቅምት፲፬ ጥቅምት፳፩ ጥቅምት፳፰ ኅዳር፭) የሚቆመውን የማኅሌተ ጽጌ ዚቅና መዝሙር በየሳምንቱ ይዘንላችሁ እንቀርባለን::




ነግሥ ለኵልያቲክሙ...ዚቅ

ወኃይዝተ ወንጌል የዓውዳ ለቤተክርስቲያን፤
እም አርባዕቱ አፍላጋት፤
እንተ ትሰቀይ ትእምርተ ለለጽባሑ፤
እማቴዎስ ልደቶ ወእማርቆስ መንክራቶ፤
እም ሉቃስ ዜናዊ ተሰምዮ ወእም ዮሐንስ በግዓ፤
ወዘንተ ሰሚዓ ትገብር በዓለ በፍግዓ፤

ማኅሌተ ጽጌ

ጽጌ አስተርአየ ሠሪፆ እምዐፅሙ፤
ለዘአማኃኪ ጽጌ ለገብርኤል በይነ ሰላሙ፤
ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዓዛ ጣዕሙ፤
ለተአምርኪ አኀሊ እሙ ማኅሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ፤

Friday, September 25, 2015

መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ

  በቅmeskel dameraድሚያ ከዘመን ወደ ዘመን ያሸጋገረን ለብርሃነ መስቀሉ ያደረሰን በሀብቱ የሳበን በረድኤቱም ያቀረበን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

ከላይ በርዕሱ ያነሣነው ኃይለ ቃል ቅዱስ አትናቴዎስ የመስቀሉን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ የተናገረው ነው፡፡ አስተሀፈረ ኃጢአተ በዲበ ምድር ወሰአረ መርገመ በዲበ ዕፀ መስቀል ወአብጠለ ሞተ በውስተ ሲዖል ወነሰተ ሙስና እምውስተ መቃብር”

“በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” በማለት ጌታችን ለሰው ልጆች ነጻነት እና ድኅነት የከፈለውን የቤዛነት ሥራ በተናገረበት ክፍል የተናገረው ነው የሰው ልጆች ነጻነታቸው የተዋጀው በመስቀል ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በሥልጣኑ ለይቶ ዲያብሎስን በመስቀሉ ገሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ከአጋንንት ቁራኝነት ከሲዖል ግዛት ነጻ አውጥቷቸዋልና፡፡

Wednesday, September 23, 2015

ተቀጸል ጽጌ- የዐፄ መስቀል


 ተቀጸል ጽጌ ማለት የአበባ በዓል ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፣ ድጡ፣ ማጡ፣ ችግሩና ጨለማው ተወግዶ ምድር በልምላሜ የምታሸበርቅበት፣ በአበባ የምትደምቅበት ወቅት በመሆኑተቀጸል ጽጌ እየተባለ ይከበራል፡፡የተቀጸል ጽጌ በዓል የተጀመረው በ6ኛው ምዕተ ዓመት በዐፄ ገብረ መስቀል አማካይነት ሲሆን በዓሉ የሚከበረው የክረምቱ ማብቃት የሚያበስሩ አበቦች በሚፈኩበት ወር በመስከረም 25 ቀን ለንጉሡ የአበባ ጉንጉን /አክሊል/ በማበርከት ነበር፡፡

Friday, August 14, 2015

የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ

     

የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገዳሙ ከጎንደር ከተማ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ኮሶዬ ከተማ ሲደርሱ ሶስት ሰአት የእግር መንገድ እንደተጓዙ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የጩጊ ማርያም ገዳም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተ ጥንታዊ ገዳም ሲሆን የመሰረቱትም አባ ምእመነ ድንግል የተባሉ ጻድቅ ናቸው፡፡ገዳሙም ጻድቁ የጸለዩበት እና ከጌታችን ከመድሃኒታች ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ቅዱስ ቦታ ነው፡፡
የአባ ምእመነ ድንግል ታሪክ
አባ ምእመነ ድንግል የተወለዱት በወገራ አውራጃ ሲሆን ገና በህፃንነታቸው በእናት በአባታቸው ቤት እያሉ ጀምሮ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በመስራት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ምእመነ ድንግል የምንኩስና ልብስና የእግዚአብሔር ጸጋ በመፈለግ አዳጋት ማርያም ወደ ምትባል ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፤ጽናታችውን ያዩ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባትና መምህር እንዲሆኗቸው ቢጠይቋቸው እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ “እኔ መምህርና አባት ልሆን አይገባኝም ” በማለት እንቢ ቢሉም መነኮሳቱ አበምኔት አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ አባታችንም በተሾሙበት በዚህ ገዳም በከፍተኛ ተጋድሎና በእግዚአብሔር ጸጋ ብዙ መንፈሳዊ መነኮሳትንና መምህራንን በትምህርታቸው አፍርተዋል፡፡

Tuesday, August 4, 2015

ጾመ ፍልሰታ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም


ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡ ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 37 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡