Friday, August 19, 2016

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር


‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን ይህም ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር የተያያዘ እንደዚሁም ከምሥጢረ ሥጋዌና ከነገረ ድኅነት ጋር የተሳሰረ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ መገለጥ ነው፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሣፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡