Friday, August 14, 2015

የጩጊ ማርያም ገዳም ታሪክ

     

የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገዳሙ ከጎንደር ከተማ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ኮሶዬ ከተማ ሲደርሱ ሶስት ሰአት የእግር መንገድ እንደተጓዙ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የጩጊ ማርያም ገዳም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተ ጥንታዊ ገዳም ሲሆን የመሰረቱትም አባ ምእመነ ድንግል የተባሉ ጻድቅ ናቸው፡፡ገዳሙም ጻድቁ የጸለዩበት እና ከጌታችን ከመድሃኒታች ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ቅዱስ ቦታ ነው፡፡
የአባ ምእመነ ድንግል ታሪክ
አባ ምእመነ ድንግል የተወለዱት በወገራ አውራጃ ሲሆን ገና በህፃንነታቸው በእናት በአባታቸው ቤት እያሉ ጀምሮ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በመስራት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ምእመነ ድንግል የምንኩስና ልብስና የእግዚአብሔር ጸጋ በመፈለግ አዳጋት ማርያም ወደ ምትባል ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፤ጽናታችውን ያዩ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባትና መምህር እንዲሆኗቸው ቢጠይቋቸው እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ “እኔ መምህርና አባት ልሆን አይገባኝም ” በማለት እንቢ ቢሉም መነኮሳቱ አበምኔት አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ አባታችንም በተሾሙበት በዚህ ገዳም በከፍተኛ ተጋድሎና በእግዚአብሔር ጸጋ ብዙ መንፈሳዊ መነኮሳትንና መምህራንን በትምህርታቸው አፍርተዋል፡፡

Tuesday, August 4, 2015

ጾመ ፍልሰታ ለቤተ ክርስቲያን ሰላም


ኢትዮጵያ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአሥራት አገር ናት፡፡ ሊቃውንትም ነቢያት የተነበዩትን ትንቢት የቆጠሩትን ሱባዔ መሠረት በማድረግ ቅድስት ድንግል ማርያም በኪደተ እግሯ ኢትዮጵያን መባረኳን ያስተምራሉ፡፡ «ነቢዩ ዕንባቆም የኢትዮጵያ ድኳኖች ሲጨነቁ ዐየሁ፤» ዕንባ. 37 ብሎ የተናገረው ቃለ ትንቢት እመቤታችን የኢትዮጵያን አውራጃዎች ለመባረኳ ማስረጃ መሆኑን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይተረጉማሉ፤ ያመሠጥራሉ፡፡
 
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ አሥራት አድርጐ በመሥጠቱ በእርሷ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሆን የነገረ ድኅነት ምሥጢር በመከናወኑ ኢትዮጵያውያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተለየ ፍቅር አለን፡፡ የአብነት /የቆሎ/ ተማሪዎች በትምህርት ዓለም ከአንዱ ወደሌላው እየተዘዋወሩ /የአብነት/ ትምህርት ሲማሩ በእንተ ስማ ለማርያም፤ ስለማርያም እያሉ፡፡ የእመቤታችን ስም ስንቅ ምግብ ሆኗቸው ይጠቀሙበታል፡፡ ግሼን ደብረ ከርቤ የልጇ ግማደ መስቀል ከከተመበት አምባም የሚጓዙ ምእመናን «አንድ እፍኝ ሽምብራ አልያዝኩም ከቤቴ ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» እያሉ በፍቅሯ ተማርከው ግብር ሰፍረው ዕጣን ቋጥረው ሱባዔ እየገቡ ይማፀኗታል፡፡