Thursday, April 23, 2015

ሰማዕታቱ እና ሰማዕትነት




ሰማዕት የሚለው ቃል ከግዕዙ “ሰምዐ” ካለው የወጣ ነው፡፡ትርጉሙም መሰከረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰማዕት ላለው ቃል መነሻው ምስክር ማለት ነው፡፡“በኢየሩሳሌም ፣ በይሁዳ ፣በሰማርያ እሰከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሐዋ 1፥8-22 እንዳለው፡፡ እንግዲህ ምስክር የሚለው ቃል በመጀመሪያ ለሐዋርያት የተሰጠ ስም ሲሆን በኋላም ሀይማኖታቸውን እንደ ሐዋርያት ለሚገልጡ ምእመናን የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ደግሞ ምስክርነታቸውን የገለጡት በማስተማር ብቻ ሳይሆን ስለሚያስተምሩት ትምህርት(ወንጌል) ትክክለኛነት በፈቃዳቸው ሰማዕት እስከመሆን ደርሰው ነው፡፡ስለዚህ ሰማዕትነት ማለት ስለሃይማኖት ሲባል በፈቃድ ሞትን(መከራን) መቀበል ማለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሰማዕትነት ሶስት ነገሮችን የያዘ ነው፡፡

 የመጀመሪያው የሰማዕትነት ምክንያቱ ሲሆን ይህም ሃይማኖት(እምነት) ነው፡፡ ሰማዕትነትን የሚቀበለው ሰው ምክንያቱ ሃይማኖቱ(እምነቱ) ነው ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ ሰርቆ፣ የሰው ነፍስ በከንቱ አጥፍቶ በወንጀል ተይዞ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር ሞት ፈርደውበት የሞተ እንደሆነ ወይም ሰክሮ መኪና ገጭቶት ከሞተ  ወይንም ደግሞ በሰው ግጭት ውስጥ ገብቶ መከራ የተቀበለ ከሆነ ይህ ሰማዕት ሊባል አይችልም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ሲያረጋግጥ “ ከእናንተ መካከል እንደ ነፍሰ ገዳይ፣ ወይም እንደ ሌባ፣ ወይም እንደክፉ አድራጊ፣ ወይም በሌሎች ጉዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራ የሚቀበል አይኑር” 1ጴጥ 4፥14 በማለት ተናገረ፡፡ነገር ግን ሰማዕትነት ስለ እምነት ሲባል የሚቀበሉት መከራ መሆኑን ደግሞ ሲነግረን “የክርስቲያን ወገን እንደመሆኑ መከራን ቢቀበል ግን ስለዚህም ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር፡፡” አለ፡፡ ስለዚህ ስለ እምነት ሲባል የምንቀበለው መከራ ደስ ብሎን እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ዋጋም የምንቀበልበት ነው፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ሰማዕትነት በፈቃድ የሚቀበሉት ነው፡፡ ይህም ማለት ሰማዕት የሚሆነው ሰው በማንም በጎ ፈቃድ ወይም በየትኛውም ሰው ግፊት ሳይሆን በራሱ መልካምነት አምኖ የሚቀበለው መሆኑ ነው፡፡ ሃይማኖትህን ካድ እና በሰላም ኑር ሲባል ክዶ መኖር እየቻለ (ልክ እንደ አስመሳዮቹ ገንዘብ ይሰጥህ ሃይማኖትህን ለውጥ ሲባሉ በፍጥነት ሃይማኖታቸውን እንደሚለውጡ እና ክርስቶስን እንደሚክዱ አይነት ሰዎች) ክርስቶስን በተራ ተራ እንደሚያውቁት ፣ የክርስቶስን መከራ በወሬ እንደሚሰብኩት፣ ሃይማኖት ያላቸው የሚመስላቸው ነገር ግን አይደለም ሃይማኖት ሊኖራቸው ሃይማኖት ራሱ ምን ማለት እንደሆነ የማያውቁ እንደነዚህ ሰዎች የሚያደርግ ሳይሆን ጌታውን በመከራው፣ በሞቱ የሚመስለው ይህንንም ማንም አስተምሮት እና አሳውቆት ሳይሆን በልቦናው አንድ ጊዜ ስለተጻፈች ህግ እርሷንም ጥበብ በተሞላበት የዋህነቱ እና እምነቱ  ሞትን የሚመርጥ ስለሆነ ሰማዕትነት በፈቃድ የሚቀበሉት ታላቅ ምስጢር ማለት ነው፡፡
ሦስተኛው መከራ መቀበል ነው፡፡ እንግዲህ ሰው በተለያየ አይነት ሁኔታ መከራን ይቀበላል፡፡ እንደምናውቀው ቀደምት አበው በሃይማኖታቸው ምክንያት ህይወታቸው ራሱ በመከራ የተሞላ እንደነበር መጽሐፈ ገድለ ሰማዕታት፣ ገድለ ቅዱሳን ያስረዱናል፡፡ አበው ቅዱሳን እንዲሁም ሰማዕታት መከራን በስደት፣ በመታሰር፣ በመገረፍ፣ በመሰቀል፣ በመሞት ይቀበሉት ነበር የዚህ ሁሉ መከራ ፍጻሜ ደግሞ ሞት ነው፡፡ ስለዚህ ለእኛ ለምናምን ሰማዕትነት በሞት የሚገኝ ትልቅ የጽድቅ ስም ነው፡፡ ስለሃይማኖት በሰማዕትነት ከሚመጣ ሞት ጀርባ ያለው ክብር ግን ዋጋው በሰው ልጅ አእምሮ ፈጽሞ የሚገመት አይደለም፡፡ ልዑለ ባሕርይ የሆነው አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር የሚያዘጋጀው ዋጋ እንጂ፡፡ ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዋጋ የምታሰጠው በመከራ ውስጥ ከሆነ መከራን መቀበል አንዱ የሰማዕትነት ክፍል ነው ማለት ነው፡፡
እንግዲህ ሰማዕትነት አነዚህን ሶስቱን ነገሮች የያዘ ከሆነ ሰዎች የዚህችን ዓለም ጣዕም ከመጓጓት ይልቅ እንዴት አሸንፈው ለዚህ ክብር ይበቃሉ?
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ስለ ሰማዕታት ሲናገር  “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ስለ እግዚአብሔርም ደማቸውን አፈሰሱ ስለ መንግስተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ”(ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) ብሏል፡፡ በዚህ መሰረት ሰማዕትነት የሚጀምረው የዚህን ዓለም ጣዕም ከልብ ከመናቅ ይሆናል፡፡ የዚህን ዓለም ጣዕም ሲባል የሚበላውን ፣ የሚጠጣውን  አይደለም ይህማ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ጣዕም የተባለ ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት በስጋ ስሜት ሲቀበሉት ይጣፍጣልና ነው፡፡ በነፍስ ሲቀበሉት ግን እጅጉን ይመራል፡፡ የኃጢአት መራራነት በስጋ የሚታወቀው ሁሉ ነገር ካበቃ በኋላ ነው፡፡ ስናየው ጣፋጭ የመሰለንን በልተን ብዙውን ከጨረስነው በኋላ መራራነቱ ይገለጣል ነገር ግን መጀመሪያውኑ የሚጣፍጥ ነገር ኖሮት አይደለም ስጋዊ ስሜታችን ሰውሮብን እንጂ፡፡ ለዚህ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ የብዙ ሰዎች ታሪክ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ከእነዚህ አንዱ ይሁዳ ነው፡፡ ይሁዳ ክርስቶስን እስከሚሸጥባት ሰዓት ድረስ ለእርሱ ዋናው ነገር የሰላሳ ዲናር ጉዳይ ነበር ለዚህም ነው ክርስቶስ “ይሁዳ ልታደርግ የወደድከውን አድርግ” በሎ በግልጽ አሳልፎ የሚሰጠው እርሱ መሆኑን በነገረው ጊዜ እንኳ ይሁዳ አልነቃም፡፡ የሰራው ስራ ክፉ እነደነበር እና የተነገረው ትንቢት በእርሱ ላይ እንደተፈጸመ ያወቀው ሁሉ ነገር ሲያበቃለት ነበር፡፡ እንደዚህ አይነቱ ከንቱ ጸጸት ምን ይረባል? ምንስ ይጠቅማል? ሁለተኛው ነገር ደግሞ ሰማዕት በመሆን ደምን ማፍሰስ ስለእግዚአብሔር ብቻ ተብሎ የሚደረግ መሆኑ ነው፡፡ ስለ ስልጣን፣ ስለገንዘብ ወይም ስለሌላው ተብሎ አይደለም ስለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ “ስለእግዚአብሔር ብለው ሰውነታቸውን ለሰማዕትነት ሰጡ፡፡” (2 መቃብ 13፥8) እንዲል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ስለ መንግስተ ሰማያት ሲሉ መራራ ሞትን መቀበል(መታገስ) ነው፡፡ ሰማዕታት መራራውን ሞት የታገሱት ስለመንግስተ ሰማያት ብለው ነው፡፡ ምክንያቱም ከዓለም ይልቅ የመንግስተ ሰማያትን ኑሮ አጣጥመውታልና እንዴት? ምክንያቱም መንግስተ ሰማያት ማለት ወንጌል ስለሆነች በወንጌል ኖረው በወንጌል አልፈው የሚያገኟት ናትና አንድ ሰው በር ሳያንኳኳ ወደግቢ መግባት እንደማይችለው እንዲሁም ወንጌል ተንኳኩታ መንግስተ ሰማያት እንደምትገኝ ለመንግስተ ሰማያት መግቢያ በር የሆነችን ወንጌል ሰማዕታት አጣጥመው ያውቋታልና ነው፡፡           
ሰሞኑን በአህዛባዊው isis የተገደሉ (ሰማዕትነትን የተቀበሉ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ወንድሞቻችን በኩል የተመለከትነውም ይህንኑ ነው፡፡ ስለሰዎች ችግር ፣ ስለፖለቲካ ወይም ስለገንዘብ ወይም ባጠቃላይ ስለዓለም እና በዓለም ውስጥ ስላለው ነገር ብለው ሳይሆን ስለክርስቶስ እና በክርስቶስ ውስጥ ስላገኟት ስለ ክርስትናቸው ብለው ይህንን ታላቅ ተጋድሎ በድል ተወጥተው ሰማዕትነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በሚገባ አስተምረውናል፡፡ ብዙዎች የሚሰብኩትን ፣ ብዙዎች የሚሰሙትን ይህንን የእግዚአብሔር ቃል በፍፁም ጽናትና በሃይማኖት እንዲሁም በእምነት ተግብረው ያስተማሩን የዘመናችን መምህራን ናቸው፡፡
በአህዛባዊው isis የተሰዉት ወንድሞቻችን በኢትዮጵያዊነታቸው ሳይሆን በክርስትናቸው ምክንያት ይህንን መራራ ሞት ተቀብለዋል፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ግን ለመኖር አማራጭ አጥተው አልነበረም መኖር የሚችሉበት ምርጫም ቀርቦላቸዋል ነገር ግን በሰዎች ፈቃድ ለሰዎች አስተሳሰብ ከመገዛት ለሃይማኖት መሞትን የመረጡት ፈቅደው እና ወደው ነው፡፡ የቀደምት ሰማዕታት ዜናቸው የሚታፈርበት ታሪክ እየሆነ በመጣበት በዚህ ጊዜ የእውነተኞቹ ቅዱሳን ሰማዕትነት ዋጋ ያለው ሰማዕትነት መሆኑን፣ እውነት እንጂ ተረት አለመሆኑን በእውነት በዘመናችን ያስተማሩን ታላላቅ መምህራነ ወንጌል እነዚህ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ሳይሆን ክርስቲያን በመሆናቸው እንደ በግ የታረዱት እና እንደ አውሬ በጥይት የተገደሉት ወንድሞቻችን ሰማዕትነት ስለሃይማኖት ሲባል በፈቃድ ሞትን መቀበል መሆኑን ሰማዕትነትና መንግስተ ሰማያት በመዋት ድልድይ የሚገናኙ መሆናቸውን ሰማዕታት ሆነው አስተምረውናል፡፡

                                                     በረከታቸው ይደርብን፡፡

ይቆየን!