Friday, December 16, 2016

                               ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ



      አቡነ ዜና ማርቆስ አባታቸው ዮሐንስ እናታቸው ማርያም ዘመዳ /ዲቦራ/ ይባላሉ፡፡ አባታቸው ዮሐንስ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የአቡነ ጸጋ ዘአብ ወንድም ናቸው፡፡ እናታቸው ደግሞ የአቡነ ቀውስጦስ እኅት ናቸው፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ብሥራት የተጸነሱ አባት ናቸው፡፡ እኚህ አባት በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው እሰግድ ለአብ እሰግድ ለወልድ እሰግድ ለመንፈስ ቅዱስ ብለው ሦስት ጊዜ ሰግደዋል፡፡
በ40 ቀናቸውም ሊጠመቁ ወደ ቤተክርስቲያን በወሰዷቸው ጊዜ ካህኑ በመጽሐፍ የሚያደርሱትን ሥርዓተ ጥምቀት እሳቸው በቃል አድርሰውታል፡፡ ሲያጠምቋቸውም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ ብለው ሦስት ጊዜ ሰግደዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውኃው ፈላ የ 72 ዓመት አጎታቸው እንድርያስ ይህን ተአምር ዐይተው ፈሩ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጡ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ምን አስፈራህ መላጣህን ተቀብተኸው ቢሆን ፀጉር ባበቀለ ነበር አላቸው እሳቸውም ተመልሰው ከውኃው ቢቀቡት ፀጉር አበቀለላቸው፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ 5 ዓመት በሆናቸው ጊዜ ወላጆቻቸው ወስደው ለመምህር ሰጣቸው በሦስት ዓመት ብሉይ ከሐዲስ አጥንተው በስምንት ዓመታቸው መዓረገ ዲቁና ለመቀበል ወደ አባ ቄርሎስ ሄዱ፡፡ ተቀብለው ሲመለሱ ሳይንት በምትባል ቦታ ላይ ሽፍቶች አግኝተዋቸው የእጃቸውን በትር ሳይቀር ነጠቋቸው አቡነ ዜና ማርቆስም አዘኑ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ በትራቸው እባብ ሆኖ ሽፍቶቹን ነደፋቸው፡፡
30 ዓመት በሆናቸው ጊዜ ቤተሰባቸው ማርያም ክብራ የምትባል ደግ ሴት አጭተው አጋቧቸው ልማደ መርዓዊ ወመርዓት ያድርሱ ብለው መጋረጃ ጥለውባቸው ሄዱ፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስም አንቺ እኅቴ ይህ ዓለም ኃላፊ ጠፊ ነው ምን ይረባናል ብለን እናደርገዋለን አሏት፡፡ እርሷም ብንተወው እወዳለሁ አለቻቸው፡፡ ኮብላይ ለልማዱ በሌሊት ይጓዛል እንዲሉ በሌሊት ወጥተው ሄዱ፡፡ ማርያም ክብራን መላእክት ጌተሴማኔ አድርሰዋት 7 ዓመት ኖራ ጥር 2 ቀን ዐርፋለች፡፡ በዛም አንበሦች ቀብረዋታል፡፡ ዋጋን የሚከፍል እግዚአብሔር አምላክም ስለተጋድሎዋ ሦስት አክሊላትን አቀዳጅቷታል፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስንም መልአክ እየመራቸው ሀገረ ምሑር አድርሷቸዋል፡፡ በዛም ብዙ ተአምራትን እያሳዩ ሀገረ ገዢውንና ሕዝቡን አሳምነው በሀገረ ምሑር 5 ዓመት ከቆዩ በኋላ ወደ ጉራጌ ሀገር ሄደው አስተምረው ሕዝቡን ወደ እምነት መልሰዋል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላ እኚህ ሁለቱ ቅዱሳን አባቶች ሲገናኙ ትሕትና ልማዳቸው የሆነ አቡነ ዜና ማርቆስ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን አገልግለዋቸዋል በአንድነት ሆነውም አረማዊውን ሀገረ ገዢ ድል አሰግድን በተአምራት አሳምነው አጥምቀውታል፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሊሄዱ በተነሱ ጊዜ መዓረገ ምንኩስና ሰጥተዋቸዋል፡፡ መንገድ ሲሄዱም ዛፉ ድንጋዩ ሁሉ በግራ ቀኝ እየተከተላቸው በቃላቸው ተናግረው በቦታቸው አድንቀዋቸው ሄደዋል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ እነዚህ ዛፎች እንደዘመሙ ይታያሉ፡፡
አቡነ ዜና ማርቆስ መዓረገ ምንኩስና ከተቀበሉ በኋላ ደብረ ብሥራትን ገድመው እያስተማሩ ሲኖሩ ብዙ ተአምራት አድርገዋል፡፡ በ200 አንበሦች በ200 ነብሮች ታጅበው በደመና ተጭነው ደቅ ደርሰው ተመልሰዋል፡፡ በሌላ ጊዜም ቅዳሴ ገብተው ሲያቆርቡ ሰው በዘባቸውና መሸ፡፡ ፀሐይም ልትገባ ሆነ፡፡ ጸልየው ልክ እንደ ኢያሱ አቀብለው እስኪፈጽሙ ድረስ ፀሐይ ባለችበት አቆይተዋታል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ በ8 እንጀራ 800 መነኮሳትን መግበው 103 መሶብ ተርፎ አንስተዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ብዙ ተአምራትን አድርገዋል፡፡
ከዚህ በኋላ በተስፋቸው ያመነ በቃልኪዳናቸው የተማጸነ ዋጋውን እንደማያጣ እግዚአብሔር አምላክ ነግሯቸው በተወለዱ በ140 ዘመናቸው ታኅሣሥ 3 ቀን ዐረፉ አምላካችን እግዚአብሔር ከአቡነ ዜና ማርቆስ ከበረከታቸው ከረድኤታቸው ያሳትፈን፡፡ የጻድቃን እመቤት ወላዲተ አምላክ ፍቅሯን ታሳድርብን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment