Friday, December 16, 2016


              

     ሕልመ ሌሊት
 በጠለቀ
እንቅልፍ ላይ ሳሉ የሚከሠት ሕልመ ሌሊትን እንደ ኃጢአት እንዲቆጠርና እንዳይቆጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ:: ስለዚህ ሕልመ ሌሊትን በጥቅሉ ኀጢአት ነው ወይም አይደለም ማለት አይቻልም:: ነገር ግን እንደ ኀጢአት እንዲቆጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎችን በመጠኑ መዘርዘር ይቻላል::
/. አጋንንት የሰውን ልጅ በተኛበት ክፉ ክፉ ሕልም በማሳየት ይፈትኑታል:: አንድ ጊዜ የተራቆተ የሴት ገላ; በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ወንድና ሴት አለሌና ባዝራ እየሆኑ ሲጨዋወቱና ሲደራረጉ በምትሐት ያሳዩታል:: በዚህ ጊዜ እርሱም በዝሙት ሐሳብ ይሳብና በሕልሙ ዝሙት ሲፈጽም ያድራል:: በዚህ መልኩ የተከሠተ ሕልመ ሌሊት "ጸዋግ" ወይም "ኅሡም" ሕልም ይባላል:: ክፉ
ወይም ጥፉ ሕልም ማለት ነው::
በዚህ መልኩ አጋንንት ሰውን እንደሚዋጉት
በመጽሐፈ መነኮሳት እንዲህ ተጽፏል:: "ይትቃተልዎ ሰይጣናት በመዓልት
በሕሊናት እኩያት ወበሌሊት በአሕላማት ኅሡማት" በአማርኛ "ሰይጣናት
የሰውን ልጅ ቀን ቀን ክፉ ሐሳብ በማሳሰብና በማሠራት በሌሊት ደግሞ ዝሙት የሞላበት አስጸያፊ ሕልም በማሳየት ይዋጉታል"
ማለት ነው:: በዚህ መልኩ ሰይጣናት ያቀረቡለትን ረቂቅ ፈተና ከመቃወም ይልቅ ደስ እያለው
የሚያጣጥም ማለትም ከመጸጸትና ከመቆጨት ይልቅ በደስታ ስለ ዝሙት
የሚያሰላስል; የሚዳራ; የሚዛለል; ወደ ዝሙት ከሚያመሩ ማናቸውም ነገሮች
የማይሸሽ ሰው እነዚህ ነቅቶ ሳለ ያልተቃወማቸውን ተግባራት በሕልሙ
በሚፈጽማቸው ጊዜ በተግባር እንደፈጸማቸው ያህል ኃጢአት ሆነው
ይቆጠሩበታል:: ይህን የሚያስረዳ እንዲህ የሚል የመጻሕፍት ቃል ይገኛል::
"ዘይትቄበል በመዓልት ስሕተታተ ፍትወት ውስተ ልቡ ወኢይከሥታ ወለዝንቱ
ሕሊናቲሁ ወአሕላማቲሁ ወፍትወታቲሁ ርኩሰት ትትሐሰብ ሎቱ ኃጢአተ"
ይህም "በቀን ነቅቶ ሳለ ኃጢአትን ወዶ የሚቀበልና ገልጾ የማይናዘዛት ለዚያ
ሰው የረከሰች ሐሳቡ; ሕልሙ ኃጢአት ሆና ትቆጠርበታለች::" ማለት ነው::
ከሥራ ብዛት ሕልም እንደሚታይ ጠቢቡ ሰሎሞን "ሕልም በሥራ ብዛት
ይታያል" በማለት የተናገረው ቃል ያስረዳል:: መክ.5:3:: እንደዚሁም ሁሉ
ከምኞት ብዛትም ሕልም ሊከሠት ይችላል:: ክፉ ምኞት በሕልምም ቢሆን
ማርከሱ አይቀርም:: ሐዋርያው ይሁዳ "እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ" በማለት
የጻፈው መልእክት እዚህ ቦታ ላይ ሊጠቀስ ይችላል:: ይሁዳ 1.8::
እንደሚታወቀው ነፍስ እንደ ሥጋ አትተኛም እንቅልፍም በእርሷ ዘንድ የለም::
ስለዚህ ነፍስ በእንቅልፍ ልቤ ነው በማለት ማመካኘት አትችልም:: ነፍስ በረከሠ ሕልም ምክንያት ከተጠያቂነት ነፃ መሆን የምትችለው ሥጋ ከእንቅልፍ ውጭ በሚሆንበት ጊዜ ተግባረ ዝሙትን በመቃወምና በመጥላት ከእግዚአብሔር ጋር መሆኗን ስታስመሰክር ብቻ ነው::
/. ሌላው ሕልመ ሌሊትን እንደ ኃጢአት የሚያስቆጥረው ሁናቴ አብዝቶ
መመገብ ነው:: ጾም ለጽድቅ ሥራ ሁሉ መሠረት እንደሆነ እንደዚሁ አብዝቶ
መመገብም የኃጢአት ሁሉ መሠረት ነው:: "እኅልም ጉልበትን ያጠነክራል"
ተብሏልና:: ሰው ሁሉ ለቁመተ ሥጋ ያህል መመገብ ያሻዋል:: መዝ.103:15
ሆኖም ለልዩ ልዩ የምግብ ዓይነቶች መጐምጀትና ከዚያም አልፎ አብዝቶ
መመገብ ነፍስን ለሥጋ ማስገዛት ነው:: ይህ ደግሞ ገዥዋን ተገዥ ማድረግ በመሆኑ ግፍ ነው:: ሊቀ ጳጳስ ለዐቃቢት እንደመገዛት ያህል ነውና:: ወጣቶች ይልቁኑም በዝሙት ሥራና ሐሳብ በእጅጉ የሚፈተኑ ሰዎች በሚገባ መጾም አለባቸው:: በሰውነት ላይ የዝሙት ፆር ጸንቶ ሳለ አብዝቶ መመገብ የሚቃጠል
ክርን ሰም እንደ መመገብ(መቀባት) ነው:: ሰም ክሩን የበለጠ እንደሚያቀጣጥለው አብዝቶ መመገብም የዝሙት ፍላጐትን የበለጠ እንዲበረታ ያደርገዋል::
መጽሐፈ መነኮሳትም ይህን ሲገልጽ "መብዝኀ መባልዕትኒ ምስለ ኃይለ ውርዝውና ያስተዳልው ምጽአተ ሕማማት:: በኃይል አብዝቶ መመገብ ከወጣትነት ጋር የኃጢአት ሐሳብን በግድ እንዲመጣ
ያደርጋሉ" ይላል:: [ማር ይስሐቅ; አንደኛ መጽሐፈ መነኮሳት; አንቀጽ 20,
ምዕራፍ 1]. አብዝቶ መመገብና ለመብል መሳሳት የኃጢአት ምንጭ ከመሆናቸው ባሻገር በራሳቸው ኃጢአት ሆነው ይቆጠራሉ::
የሰዶም ኃጢአት አብዝቶ መመገብና ጠግቦ መብላት እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር:- "እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኃጢአት ይህ ነበረ; ትዕቢት; እንጀራን መጥገብ; መዝለልና
ሥራ መፍታት በእርስዋና በሴቶች ልጆቿ ነበረ::" ይላል:: "እንጀራን መጥገብ"
ኃጢአት መባሉን ተመለከትክ? ሕዝ.16:49 ስለዚህ በልክ ተመገብ እንጂ ለስስት አትሸነፍ:: ሳይጠነቀቅ ቀርቶ አብዝቶ ከመመገቡ የተነሣ ሕልመ ሌሊት
ያገኘው ሰው እንደ ኃጢአት ይታሰብበታል:: ምክንያቱም አብዝቶ መመገብ ኃጢአትን እንደሚወልድ እያወቀ ችላ ብሎ በመመገቡ ነው::
መጽሐፈ መነኮሳት አብዝቶ ከመመገብ የተነሣ ሕልመ ሌሊት ስለሚከሠትበት ሰው
እንዲህ በማለት ይተርካል:: "ወመንጸፈ ኅርትምናሁሰ ወልብሱ ወትፍግዕተ
ሥጋሁ ኩለንታሁ ርሱሕ:: በእንተ ብዝኀ ውኂዝ ርኩስ ዘይውኅዝ እም ሥጋሁ
ከመ ዐይነ ማይ አኮ በሌሊት ባሕቲቱ ዘይመጽእ ዝንቱ እስመ ሥጋ ያውኀዝ
ወትረ ወያረኩሶ ለሕሊና" ወደ አማርኛ ሲመለስ "ከሰውነቱ እንደ ምንጭ
የሚነቃ ርኩስ ዘር በዝቶ ስለ ፈሰሰ ጐስቈላ ምንጣፉ; ልብሱ; በዝሙት ደስ
የተሰኘ ሥጋው ሁለንተናው የረከሰ ነው:: ሥጋ ሁልጊዜ ያነቃዋልና ዘሩ
የሚፈሰው በሌሊት ብቻ አይደለም:: ሕሊናውንም ያረክሰዋል" ማለት ነው::
ይህም ለምግብ ከመሳሳትና አብዝቶ ከመመገብ የተነሣ የሚመጣ ሕልመ
ሌሊት እንዴት ሰውን እንደሚያረክስና ኃጢአት ሆኖ እንደሚቆጠርበት ያስረዳል::
[ማር ይስሐቅ; አንቀጽ 20; ምዕራፍ 2].
አንድ ሰው በንቁ ልቡና ሳለ ወደ
ኃጢአት የሚመሩትን ነገሮች ተግቶ እየተቃወመ ነገር ግን በተኛና ባንቀላፋ ጊዜ
ዝንየት ቢያገኘው በተራክቦ; ዘር በማፍሰስ ያያት ሕልሙ ዕዳ ሆና
አትቆጠርበትም:: መሐሪ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውዬው ተቃወማት
እንጂ ወዶ ወደ እርሷ እንዳልተሳበ ያውቃልና:: አንቀላፍቶ ሳለ ዘሩ ቢወርድ
ፈልጐ አላመጣውምና ዕዳ አይሆንበትም:: ነገር ግን ተቃውሞ ለማራቅ
አልተቻለውም::
 ለዘር የበቁ ወጣቶች ዘር የሚከፍሉት ወይም የሚወጣቸው በልዩ ልዩ መንገድ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ግን ተኝተው ሳለ
በጠለቀ እንቅልፍ ሆነው ሕልም በሚያልሙበት ወቅት ነው:: ይህ ሲሆን እንደ
ጤናማ የተፈጥሮ ሂደት ይቆጠራል:: የዚህ ዓይነቱን ሕልም መጽሐፈ መነኮሳት
በአንድ ስፍራ "ሕልመ ጽምረት" በሌላ ቦታ ደግሞ "መስቆርርት ሕልም" ሲለው
ይገኛል:: ሕልሙን ያየው ሰው ደግሞ "ዝንየት መታኝ" ወይም "ሕልመ ሌሊት"
አገኘኝ ይላል:: ይህ በቤተ ክርስቲያን ልጆች ዘንድ የተለመደና በቀላሉ
የሚያግባባ የቃል አጠቃቀም ነው::                                                                                                                                                                                

                                          

No comments:

Post a Comment