Friday, March 13, 2015

በቅዳሴ ጊዜ የሚደረጉና የማይደረጉ ነገሮች


በቅዳሴ ጊዜ ስለሚደረጉና ሰለማይደረጉ ነገሮች  ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንደሚከተለው ያዛል!

በቅዳሴ ጊዜ የሚስቅ ሰው ቅዱስ ባስልዮስ በጻፈው በ፸፪ኛው አንቀጽ ካህን ቢሆን የሚያቀብል ነውና ሥጋ ወደሙን ከተቀበለና ካቀበለ በኋላ ወጥቶ አንድ ሱባዔ ይቀጣ ይጹም ይስገድ፣ የሳቀው ሕዝባዊ ቢሆን ግን ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል ያን ጊዜ ፈጥኖ ይውጣ ይላል። ምነው ፍርድ አበላለጠ ካህኑን ተቀብሎ ወጥቶ ይቀጣ አለ፤ ሕዝባዊውን ሳይቀበል ወጥቶ ይሂድ አለ ቢሉ ካህኑ የሚቆመው ከውስጥ ነው ሲስቅ የሚያየው የለም። ካህኑ በቅዳሴ ጊዜ ቅዳሴውን ጥሎ ወጥቶ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ቄስ እገሌ አባ እገሌ በመሥዋዕቱ ምን አይተውበታል ብለው መሥዋዕቱን ሳይቀር ይጠራጠሩታል፤ ስለዚህ ነው። ምዕመኑ ግን ሲስቅ ሁሉ ያየዋልና ለሌላ መቀጣጫ እንዲሆን፤ በቤተ መቅደስ የማይወደድ ሌላ ነገር አይናገር፤ በቤተ መቅደስ ጭንቅ፣ ደዌ ሳያገኘው አንዱን ስንኳ ምራቁን እንትፍ አይበል። ነገር ግን ደዌ ቢያስጨንቀው ድምፅ ሳያሰማ ምራቁን በመሐረቡ ተቀብሎ ያሽሸው።

በቤተ ክርስቲያንና በቅዳሴ ጊዜ ማንም ማን ዋዛ ፈዛዛ ነገር የሚናገር አይኑር፣ ቤተ ክርስቲያን በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነው የሚጸልዩባት
የጸሎት ቦታ ናትና ቅዳሴው ሳይፈጸም አቋርጦ መውጣት አይቻልም፣ አይፈቀድም፣ በጣም ጭንቅ ምክንያት ወይም በሕመም ምክንያት ከሆን ግን ክቡር ወንጌል ከተነበበ በኋላ ሊወጣ ይችላል። በቅዳሴ ጊዜ ካህናት የሚቀድሱባቸው አልባሳት ነጫጭ ይሁን ነጭ ልብስ ደስ እንዲያሰኝ በሥጋ ወደሙ የተገኘ ክብርም ደስ ያሰኛልና፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ባህርየ መለኮቱን በገለጸ ጊዜ ልብሱ እንደበረድ ነጭ ሆኗል። መላእክትም ወርኃ ሰላም ወርኃ ፍስሐ ነው ሲሉ የልደት፣ የትንሣኤ፣ የዕርገት ነጫጭ ልብስ ለብሰው ታይተዋል።

አንድ ሰው እንኳ ጫማ አድርጎ ከቤተ መቅደስ አይግባ ልዑል እግዚአብሔር የምትቆምባት ደብረ ሲና የከበረች ናትና ጫማህን አውልቅ ብሎ ለሙሴ ተነግሮታልና። /ዘጸአት -/

በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥዖውን የማያውቅ ደግሞ በአንክሮ፣ በተዘክሮ፣ በአንቃእድዎ፣ በንጹሕ ልቡና፣ በሰቂለ ሕሊና ሆኖ ሕሊናው ወደ ዓለማዊ እንዳይወስደው መቆጣጠር አለበት።

ቅዱስ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ካህኑ ለሕዝቡ ተርጉሞ ይንገራቸው ያስተምራቸው እጁንም በሚታጠብበት ጊዜ የተጣላችሁ ሳትታረቁ፣ የሰው ገንዘብ የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ ሥጋ ወደሙን ብትቀበሉ ሥጋው እሳት ሆኖ ይፈጃችኋል ደሙ ባህር ሆኖ ያሰጥማችኋል። ነገር ግን የወሰዳችሁትን የሰው ገንዘብ መልሳችሁ፣ ከተጣላችሁት ታርቃችሁ ኃጢአት ብትሰሩ ንስሐ ገብታችሁ ብትቀበሉት ግን መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ይሆናችኋል። በረከተ ሥጋውን በረከተ ነፍሱን ያድላችኋል ብሎ ይንገራቸው ያስተምራቸው ይላል።

በቅዱስ ቁርባን ጊዜም አስቀድሞ ሊቃነጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ በቁምስና መዓርግ ያሉ መነኮሳት፣ ቀጥሎ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት ይቀበላሉ፤ ቀጥሎ ወንዶች በአርባ ቀን የሚጠመቁ ሕፃናት ከሁሉ አስቀድመው ይቀበሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና። ከነዚህ ቀጥሎ ከአርባ ቀን በኋላ እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉት ሕፃናት ትንሾቹ በፊት እየሆኑ እንደየዕድሜያቸው ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው /ክህነት የሌላቸው/ በድንግልና ኑረው የመነኮሱ ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው ሃያ፣ ሃያ ሁለት ዓመት የሆናቸው ደናግል ይቀበሉ፤ ከዚያ ቀጥለው በሹመት ያሉ ናቸውና ንፍቀ ዲያቆናት፣ አናጉንስጢሳውያን፣ መዘምራን ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

በሴቶችም በኩል ከሁሉ አስቀድሞ የተጠመቁ የሰማንያ ቀን ሕፃናት ይቀበላሉ የዕለት ሹማምንት ናቸውና በንጽሐ ጠባይእ መላእክትን ይመስላሉና፤ ከነዚያ ቀጥሎ ከሰማንያ ቀን እስከ ስድስት፣ ሰባት ዓመት ያሉ ሕፃናት እንደየዕድሜያቸው ሕፃናቱ አስቀድመው ታላላቆች ቀጥለው ይቀበላሉ፤ ከዚያ ቀጥለው አሥራ ሁለት፣ አሥራ አምስት የሆናቸው ደናግል ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የቀሳውስት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ኑረው የመነኮሱ እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያው ቀጥለው የዲያቆናት ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በንሰሐ ተመልሰው የመነኮሱ መነኮሳት እና መነኮሳይያትይቀበላሉ፤ ከነዚያ በኋላ የንፍቀ ዲያቆናት፣ የአናጉንስጢሳውያን፣ የመዘምራን ሚስቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው በሕግ ጸንተው ያሉ ሕጋውያን እናቶች ይቀበላሉ፤ ከነዚያ ቀጥለው የንስሐ ሕዝባውያን ሚስቶች በየመዓርጋቸው ይቀበላሉ።

ከዚህ በኋላ ካህኑ ሥጋ ወደሙን በፈተተበት እጁ ሕዝቡን ፊታቸውን ይባርካቸው። ቀሳውስት ግን እጅ በእጅ ተያይዘው እርስ በርሳቸው ይባረኩ። ቀዳሹ ካህን ቀሳውስትን ሲያሳልምየጴጥሮስን ሥልጣን ባንተ አለይበል፣ ተሳላሚው ቄስምመንግሥተ ሰማያት ያውርስህ ከሾመ አይሻርህይበል። ለዲያቆናትምልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ ይባርክህ፣ ለማስተማር ዓይነ ልቡናህን ያብራልህ፣ ምሥጢሩን ይግለጥልህእያለ ይባርካቸው። ለምዕመናንምልዑል እግዚአብሔር ያክብርህ፣ ይባርክህ፣ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልህእያለ ይባርካቸው። ለሴቶችምልዑል እግዚአብሔር ይባርክሽ፣ ያክብርሽ ገጸ ረድኤቱን ይግለጽልሽብሎ በእጁ ይባርክ።


 ይቆየን !

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 comment:

Post a Comment