Showing posts with label ስብከት. Show all posts
Showing posts with label ስብከት. Show all posts

Wednesday, January 18, 2017

                      አስተርእዮ


‹‹አስተርእዮ›› የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ መገለጥ፣ መታየት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡

Friday, December 16, 2016



የገና ዛፍ
የገና ዛፍ ከየት መጣ ከእፅዋት ሁሉ የጽድ ዛፍ ብቻስ
ለምን ሆነ ?
የጌታችንና የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርሰረቶስ
የልደት በዓል ሲከበር ዘውትር እያየናቸው ካሉና የበዓሉ አንድ
አካል እየሆኑ ከመጡ ነገሮች መሀከል ዋነኛው የገና ዛፍ ነው።
ይህን የገና ዛፍ አብዛኞቻችን ዝም ብለን ከማድረግ ባለፈ መቼቱ
የት እንደሆነ ምን አይነት ምስጢር እንዳለው የምናውቅ
አይመስለኝም ነገር ግን የቤተክርስቲያን ታሪክ ወደኋላ መለስ
ብለን ስናይ ምንጩ ከወዴት እንደሆነ ይነግረናል የመጀመሪያዎቹ
ክርስቲያኖችና ሐዋርያት በነበሩበት ዘመን ራሳቸውን የእውቀት
ባለቤት አድርገው የሚቆጥሩ በክርስትና ላይ የመጀመሪያውን
የምንፍቅና ትምህርት ማንሳት የጀመሩ  ግኖስቲክስ የሚባሉ
ሃሳውያን ነበሩ የስማቸው ትርጉም በግሪክ ቋንቋ ጠቢባን
አዋቂወች ማለት ነው። መሪያቸው ስምኦን መሰሪ ይባላል ይህ
ሰው በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ሐዋርያትን የመንፈስ ቅዱስን ፀጋ
በገንዘብ እንዲሸጡለት ጠይቋቸው የነበረ ደፋር ሰው ነው።
ታዲያ እነዚህ እርሱ የሚመራቸው እራሳቸውን ጥበበኞች ብለው
የሚጠሩ መናፍቃን ከፍልስፍና ሃይማኖታቸው ብዙ
አስተምህሮዎች መካከል ዋነኛው ሁለት አምላኮች አሉ
ብለው የሚያምኑት ነገር ሲሆን እነዚህ አማልክት አንዱ ክፉ
አንደኛው ደግሞ ደግ ናቸው ይላሉ።መልካም የሆኑና ጥሩ ናቸው

Saturday, December 10, 2016


                        ጾመ ነቢያት

 

እንኳን ለፆመ ነቢያት በሰላም ና በጤና አደረሳችሁ!፡፡ ፆሙ የሰላም የፍቅርና የደስታ ይሁንልን፡፡ ለብርሃነ ልደቱም በሰላም ያድርሰን!፡፡

          

     ዘመኑ ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡
ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር «የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡

Monday, July 4, 2016

                                                 ክረምት


          በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ቀን ለመቁጠር፣ዘመንን፣ ወራትን፣ በዓላትንና አጽዋማትን ለማወቅ ወሳኝ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ዘፍ.14-19፣ ዘዳ.12፡1፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቆጣጠር አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር 365 1/4 ቀናት፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር 354 ቀናት፡፡ በከዋክብት አቆጣጠር ጸደይ፣በጋ፣መጸውና ክረምት የተባሉ አራት ወቅቶች አሉ፡፡

ወቅት እንዲፈራረቅ በዘመን ላይ የተሾሙ ዓመቱን በአራት ክፍለ ዘመን የሚገዙት አራት ከዋክብት ሲሆኑ በእያንዳንዱ ወር ላይ የሰለጠኑ ከአራቱ ከዋክብት ሥር እንደ ወታደር የሚያገለግሉ ሦስት ሦስት ወታደሮች በድምሩ 12 ከዋክብት አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት ወቅቶቹ ሥርዐታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ጸጋ ለፍጥረቱ እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዓመቱን ለአራት ወቅቶች የሚከፈሉትና የሚመግቡት ከዋክብት የሚከተሉት ናቸው፡-
ምልክኤል፡-
በጸደይ የሰለጠነው ኮከብ ምልክኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት/ወታደሮች/ ሚዛን በመስከረም ወጥቶ 30 ዕለት ከ 10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ሚዛን ነው፡፡ አቅራብ በጥቅምት ወጥቶ 29 ዕለት ከ40 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጊንጥ ነው ፡፡ ቀውስ በኅዳር ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ቀስት ነው፡፡ (ኬኪሮስ ማለት ረጅም መስመር ማለት ሲሆን የቀንና የሌሊት ሰዓቶች ክፍል ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተዘርግቶ 60 ክፍሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ሁል ጊዜ እየሄዱበት በየቀኑ አንድ ጊዜ ያልፍበታል፡፡ 5 ኬክሮስ 1 ሰዓት ነው፡፡)

Thursday, January 29, 2015

ወእሙሰ ተአቅብ ኩሎ ዘንተ ነገረ ወትወድዮ ውስተ ልባ



/እመቤታችን ግን ይህን ሁሉ ነገር ታስተውለው፤ በልቡናዋም ትጠብቀው ነበር፡፡/ሉቃ  ፪፥፶፩

/ ታደለ ፈንታው
ጥር ፳፩ ፳፻፯ .

 መግቢያ

አስቀድመን መሪ ኃይለ ቃል አድርገን የተነሣንበት አንቀጽ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ላይ አድሮ የተናገው ቃል ነው፡፡  የእመቤታችን ፍቅር በውስጡ ጥልቅ መሆኑ፣ ነገረ ማርያም የገባው መሆኑ የተገለጠበት ፍካሬ ቃል ነው፡፡ የእርሷስ ፍቅር በሌሎች ሐዋርያትም ላይ አለ፤ በጎላው በተረዳው ለመናገር ያህል ነው እንጂ፡፡
በድርሳነ ኡራኤል ላይ እንደተገለጠው እመቤታችን በቤተ ዮሐንስ ሳለች ወንጌላዊው ከሚያስተምርበት ውሎ ሲመለስ እንደምን ዋልሽ አላት፤ እርሷ ግን አልመለሰችለትም፡፡ የጌታዬ እናት ለምን ዝም አለችኝ ብሎ አርባ ቀን ሱባዔ ያዘ፤ በአርባኛው ቀን መልአኩ ቅዱስ ኡራኤል ተገልጦ እመቤታችንን የልጅሽን ወዳጅ ዮሐንስን ለምን ዝም አልሺው አላት፤ እርስዋም ልጄ ወዳጄ ሰማያዊውን ምሥጢር እያሳየኝ አላየሁትም ነበር አለችው፡፡ የወንጌላውያን ነገር እጅግ ያስደንቃል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ከተነናገረው ገጸ ምንባብ አንዱን ቃል ብቻ ወስደን ብንመለከት ነገረ ማርያም ሊደረስበት የማይችል ሩቅ፣ ሊመረመር የማይችል ረቂቅ፣ ጥልቅ ሰማያዊ ምሥጢር የተቋጠረበት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሉቃስን ወንጌል ከተመለከቱ በኋላ የእመቤታችን የአሳብ ልዕልና  የተገለጠበት ወንጌል መሆኑን መስክረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አንዱን ሐረግይህንን ሁሉ ነገርየሚለውን እንመልከት፡፡

ነገር ምንድንነው?

ነገር ብዙ ነገርን ያመለክታል፤ መጻሕፍት ነገር ሲሉ ልዩ ልዩ ምስጢራትን ያመለክታል፡፡ ለዓብነት ያህል የሚመለከተውን መመልከት ይገባል፡፡

1. ነገር ምስጢር ነው፡፡

ለብዙ ሰው የማይነገር፣ አንድ ሰው በኅሊናው የሚይዘው፣ በልብ የሚደመጥ በአዕምሮ የሚነከር፣ ልመና፣ ርዳታ፣ ምሥጢር፣ ምሥክርነት፣ የርኅራኄ ሁሉ ቃል፣ ይህንና የመሳሰለው ሁሉ ነገር ይባላል፡፡ የአገራችን ሰው «አንድ ነገር አለኝ´ ሲል ሽምግልና ሊሆን ይችላል፤ ተግሳጽ ሊሆን ይችላል፤ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ መልስ ሊሆን ይችላል፤ ቁጣ ሊሆን ይችላል፤ ምሕረት ሊሆን ይችላል፤ ቸርነት ሊሆን ይችላል፤ ይህንንና የመሳሰለው ሁሉ መደቡ ነገር ነው፡፡ ነገር ሰውየው በያዘው መጠን ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልቡና ውስጥ ያስቀመጠው ነገር ብዙ ነውና፡፡

1. ገር በሰውልቡና ውስጥ ያለ አሳብነው

የአገራችን ሰው አተያይን አይቶ፤ አካሄድን መርምሮ ይሄ ሰው ነገር ፈልጎኛል ይላል፡፡ ባለው ግንኙነት ላይ ተመሥርቶ ብቀላ ይሁን፣ ጥላቻ፣ መርገም ይሁን፣ ስጦታ፣ ወይም ሌላ፤ ባለው የፍቅር ግንኙነት ላይ ተመሥርቶም ይሁን ከዚህ ውጭ በአንድ ቋንቋ ተጠቃልሎ ነገር ብሎ ይጠራዋል፡፡
የቅዳሴ ማርያም ደራሲ አባ ሕርያቆስ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ በማለት ድርሰቱን ይጀምራል፡፡ በጎ ነገር በቅዳሴ ማርያም ውስጥ ተጠቃልሎ የቀረበ ነው፡፡ በዚያ ቅዳሴ ውስጥ ምን አለ? ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውኅዶ፡፡ ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ ለድንግል አኮ በአንኆ በቃለ ዝንጋዔ አላ በአኅጽሮ ወአነ አየድዕ እበያቲሃ ለድንግል፡፡  እኔም የድንግልን ገናናነነቷን እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሣነስ ቃል እንጂ ብሎ ነገረ ማርያምን፤ ወእቀውም ዮም በትሕትና  ወበፍቅር  በዛቲ ዕለት ቅድመ ዝንቱ ምስጢር  ብሎ ምስጢረ ቁርባንን፤ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ  እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ የሕይወት መብልን የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና ከፍ ከፍ እናደርግሻለን በማለት /ምስጢረ ስጋዌን / ነገረ ቅዱሳንን፣ ተልእኮ ሐዋርያትን፣ ምልጃ ጳጳሳትን፣ ነገረ ሊቃውንትን፣ ሃይማኖተ ሠለስቱ ምእትን፣ ሃይማኖታቸው የቀና ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግልን፣ መነኮሳትን መኳንንትን መሳፍንትን፣ በቀናች ሃይማኖት ያረፉ አበውንና እመውን፣ የሃይማኖት አርበኞችን አዳምን፣ አቤልን፣ ሴትን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን ሴምን፣ አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴን፣ አሮን ካህንን፣ ጌዴዎንን፣ ኢያሱ መስፍንን፣ እሴይን፣ አሚናዳብን፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስን፣ ኤልሳዕ ነቢይን፣ ኢሳይያስን፣ ዳንኤልን፣ ዕንባቆምን፣ ሕዝቅኤልን፣ ሚክያስን፣ ሲሎንዲስን፣ ናሖምን፣ ዘካርያስን፣ ያነሣበትን ቃል በመጠቅለል ነገር በማለት ይጠራዋል፡፡ በዚህ የቅዳሴ ቃል ምስጢረ ሥላሴ አለ፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም አስቀድሞ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ ነበረ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክብርና አሳር፣ ስለ ፍቅርና ጥላቻ፣ ስለ ዘላለም ጽድቅና ኩነኔ፣ ስለ ክፋትና በጎነት፣ ስለ መልካምነትና ክፋት፣  ስለ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን ምሥጢረ ትንሣዔ ሙታን፣ ሁሉ ተጠቅልሎ ቀርቧል ይህ ሁሉ ምሥጢር በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር ይባላል፡፡

2. ነገር ታሪክ ነው፡፡

መጽሐፍት ነገር ሲሉ ታሪክ ማለታቸው ነው፡፡ ነገረ ማርያም፣ የእመቤታችን ታሪክ የተጠቀለለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ነገረ ክርስቶስ የክርስቶስን ነገር የሚናገር፤ ነገረ ሥላሴ የሥላሴን ነገር የሚናገር፣ ነገረ መላእክት፣ እንዲህ እያልን የምንናገረው ነገር ታሪክን የሚናገር ነው፡፡

1. ነገር ምስጢር ነው  

ምሥጢር ብዙ ወገን ነው፡፡ የሚነገርና የሚገለጥ አለ፤ የማይነገርና የማይገለጥ አለ በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር በማለት ይጠራል፡፡ ምሥጢር ለሁሉም ወገን አይነገርም፤ ለምሳሌ የሃይማኖት ምሥጢር በእምነት ለተጠሩ፣ ሰማያዊውንና መንፈሳዊውን ነገር ለሚረዱ፣ ከሥጋ ፈቃድና አሳብ በላይ ለሆኑ እንደ መንፈስ ፈቃድ ለሚመላለሱ ወገኖች እንጂ ለሁሉ ሰው የሚነገር አይደለም፡፡ ምሥጢር የማይነገረው በሚከተሉት ዓበይት ምክንያቶች ነው፡፡
. የሚሰጠው ጥቅም ከሌለ አይነገርም፡፡
. የሚቀበለው ሰው አቅም ከሌለው አይነገርም፡፡
. ተናጋሪውና ሰሚው በእርግጠኝነት የማይደርሱበት ከሆነ አይነገርም፡
ልደተ ወልድ እም አብ ምጽአተ መንፈስ ቅዱስ እም አብ ኢይትነገር አላ ይትነከር፡፡ የወልድ ከአብ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ ይደነቃል እንጂ አይነገርም፡፡ ይህ ሁኔታ በሊቃውንት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ይሄንን የሚመስል ሌላም ነገር አለ:: በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ  የቆጵሮስ  ሊቀጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሦስቱ በእግዚአብሔር የዝምታ ሸማ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢራት በማለት የሚገልጣቸው ነገሮች አሉ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና
2. አማኑኤል ጌታን መውለዷ
3. የማይሞተው አምላክ ሞት ናቸው፡፡
አስቀድመን ካነሣነው ነገር ተነሥተን የምንደርስበት ድምዳሜ አለ እርሱም በመጠን የሚነገር በመጠን የማይነገርና ፈጽሞ የማይነገር፣ መኖሩን ነው፡፡ ፈጽሞ የማይነገረው ነገር ምክንያቱ መጠኑና ልኩ ስለማይታወቅ ነው፡፡ በመጠን የሚነገር ያልነው በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልና የጌታ እናት በምትሆን በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል የነበረውን ዓይነት ነገር ነው፡፡ ቅድስት ድንግል መልአኩን ሴት ያለ ወንድ ምድር ያለ ዘር ታብቅል የሚለውን ጥያቄ ከየት አገኘኸው ብላ በጠየቀችው ጊዜ የቅዱስ ገብርኤል መልስ የተነገረው በመጠን ነው፡፡ እርሱም «ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለም>> የሚል ነው፡፡
መልአኩ ከዚህ በላይ መሄድ አልፈለገም፡፡ ሥጋዊ ባሕርይ ሌላ መለኮታዊ ባሕርይ ሌላ ነው፤ በሊቃውንት የሚተነተነው ነገር የሚደነቅ እንጂ የመለኮትን ባሕርይ የሚገልጥ አይደለም፡፡ የተሸፈነ ምሥጢር አለ ሰው ሊረዳው የማይችል፣ የማይገነዘበው ምሥጢር፣ እጹብ እጹብ በማለት የሚያደንቀው ምሥጢር፡፡ አሁን ወደ ዋናው ነገር እንምጣ፡-

እናቱም ይህን ነገር ሁሉ ትጠብቀው ነበር አለ ወንጌላዊው፡፡ ወንጌላዊው ይህን ሁሉ ነገር በማለት የተናገረው ነገር ምንድን ነው?

ይህን ሁሉነገር

  • ከቤተ መቅደስ ይጀምራል፡፡ አስቀድሞ በቤተ እሥራኤል ደናግል በቤተ መቅደስ የሚቀመጡበት ልማድ አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ ነቢይት በቤተ መቅደሱ ታዛ ነበረች፡፡ የነቢይቱ በቤተ መቅደስ መኖርና የአምላክ እናት በቤተ መቅደስ መኖር ይለያያል፡፡ ነቢይቱ በቤተ መቅደስ የነበረችው በራሷ ምርጫ ስለ ራሷ ኃጢአት ተገብታ ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በአምላክ ምርጫ ነው፡፡ ነቢይቱ በምናኔ ነው፤ እመቤታችን ግን ካህናቱ ተቀብለው መላእክት ምግቧን አቅርበው ነው፤ ስለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ ድንግል አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰየኪ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፡፡ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዊ  ዘሰተይኪ፤ አላ ስቴ ሰማያዊ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሐ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተገኘ ነው እንጂ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ነው አንጂ በማለት የሚያመሰግናት፡፡ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

  • ዐሥራ አምስት ዐመት ሲሞላት አይሁድ በምቀኝነት ከቤተ መቅደሳችን ትውጣልን አሉ፡፤ ልማደ አንስት በእርሷ እንደሌለ እያወቀች ንጽሕናዋን አልተከላከለችም፤አልተቃወመችም እኔ እንዲህ ነኝ፣ እንዲያ ነኝ አላለችም፡፡ቤተ መቅደሱን ለቃላቸው ወጣች ይህን ሁኔታ የሚያውቀው ወንጌላው ጥቅልል አድርጎ ይህንን ሁሉ ነገር በማለት ገለጠው፡፡
 
  • በድንግልና ተወስና አምላኳን ለማገልገል ቁርጥ ኅሊና ኖሯት ሳለ የዐሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል በትር ተሰብስቦ ተጸልዮ ዕጣው ለዮሴፍ ወጥቶ ወደ ዮሴፍ ቤት መሄዷን አልተቃወመችም፡፡ በኅሊናዋ ታሰላስለው ነበር፤ ጥያቄ አንስታ አታውቅም፤ ይህን ሁሉ ነገር  በአንክሮ ትከታተለው ነበር፡፡
 
  • የመልአኩ ብስራት ትጸንሲ ሲላት  በድንግልና ለመኖር የወሰነች ስለነበረች ይህ አንዴት ዓይነት ሰላምታ ነው ብላ አሰበች፤ መልአኩ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲነግራት እንደቃልህ ይደረግልኝ እኔ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ ያለችውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡
 
  • ከጸነሰች በኋላ ዮሴፍ  መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ ብሎ በጠየቃት ጊዜ መልአኩ ገብርኤል አክብሮ ከነገረኝ ነገር በስተቀር ሌላ እንደማላውቅ እግዚአብሔር ያውቃል  የሚለውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡
 
  • ከዚያም በኋላ በቤተልሔም አማኑኤል ጌታን ስትወልድ እንስሳት ሲያሟሙቁት፣ እረኞች ሲያገለግሉት፣ ነቢይቱ ሐና ስታመሰግነው፤ ስምዖን በቤተ መቅደስ ስለ ሕፃኑ ትንቢት ሲናገር ይህ ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ምልክት ሆኖ ተሾሟል፤ በአንቺም በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ሲላት ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡
 
  • በስደቱ ጊዜ የደረሰበትን መከራ፣ ረሃቡን፣ ጽሙን፣ ድካሙን በመንገዷ ሁሉ የፈሰሰውን የሕፃናት ደም እየተራመደች ልጇን ይዛ መሰደዷን በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ጉድ እንዴት እንዳወጣት በስደቷ ጊዜ የሽፍታ ባህታዊ አዘጋጅቶ እንዴት ልጇን ተቀብሎ እንዳሻገረላት፣ ደንጋዮች ታንኳ ሆነው እንዴት ባሕርን እንዳሻገሯት  ታስተለው ነበር:፡
  • ልጇን ልተተ ሕፃናት ፈጽሞ እንዴት እንዳደገ፣ በነፋስ አውታር በደመና ዐይበት ውኃ ቋጥሮ እንዴት እንዳገለገላት፤ ልጇ በፀሐይ በነፋስ አውታር እንዴት እንደተራመደ እየተመለከተች ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡
  • በዐሥራ ሁለት ዓመቱ በሊቃውንት መካከል ተገኝቶ ሲከራከር ሊቃውንቱን ሲያስደምም ታስተውለው ነበር፡፡ 
  • ከሊቶስጥራ እስከ ጲላጦስ አደባባይ ከዚያም እስከ ቀራንዮ አደባባይ የተፈጸመበትን ነገር ሁሉ ታስተውለው ነበር፤ ይህ ሁሉ ተጠቅልሎ ለእርሷ ነገር ነበር፡፡
ይሄንንና የመሳሰለውን ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እናቱም ይሄንን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር በማለት የገለጠልን:፡


ልመናዋክብሯ የልጇም ቸርነት ይደርብንአሜን፡