Showing posts with label ዜና_ቤተክርስቲያን. Show all posts
Showing posts with label ዜና_ቤተክርስቲያን. Show all posts

Monday, July 4, 2016

                                                 ክረምት


          በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ቀን ለመቁጠር፣ዘመንን፣ ወራትን፣ በዓላትንና አጽዋማትን ለማወቅ ወሳኝ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ዘፍ.14-19፣ ዘዳ.12፡1፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቆጣጠር አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር 365 1/4 ቀናት፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር 354 ቀናት፡፡ በከዋክብት አቆጣጠር ጸደይ፣በጋ፣መጸውና ክረምት የተባሉ አራት ወቅቶች አሉ፡፡

ወቅት እንዲፈራረቅ በዘመን ላይ የተሾሙ ዓመቱን በአራት ክፍለ ዘመን የሚገዙት አራት ከዋክብት ሲሆኑ በእያንዳንዱ ወር ላይ የሰለጠኑ ከአራቱ ከዋክብት ሥር እንደ ወታደር የሚያገለግሉ ሦስት ሦስት ወታደሮች በድምሩ 12 ከዋክብት አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት ወቅቶቹ ሥርዐታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ጸጋ ለፍጥረቱ እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዓመቱን ለአራት ወቅቶች የሚከፈሉትና የሚመግቡት ከዋክብት የሚከተሉት ናቸው፡-
ምልክኤል፡-
በጸደይ የሰለጠነው ኮከብ ምልክኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት/ወታደሮች/ ሚዛን በመስከረም ወጥቶ 30 ዕለት ከ 10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ሚዛን ነው፡፡ አቅራብ በጥቅምት ወጥቶ 29 ዕለት ከ40 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጊንጥ ነው ፡፡ ቀውስ በኅዳር ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ቀስት ነው፡፡ (ኬኪሮስ ማለት ረጅም መስመር ማለት ሲሆን የቀንና የሌሊት ሰዓቶች ክፍል ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተዘርግቶ 60 ክፍሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ሁል ጊዜ እየሄዱበት በየቀኑ አንድ ጊዜ ያልፍበታል፡፡ 5 ኬክሮስ 1 ሰዓት ነው፡፡)

Friday, July 1, 2016

                   አባ ሙሴ ጸሊም 




ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቅዱሳንን ከተለያየ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡
በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ከተመለሱ ቅዱሳን መካከል አንዱ የኾኑትን በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ ፳፬ ቀን የሚዘከረዉን የአባ ሙሴ ጸሊምን ታሪክ በአጭሩ እናቀርብላችኋለን፡፡

Thursday, June 9, 2016

     ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 
            ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
                                                                                ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

           የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቍጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የዘንድሮዉን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረ ለዐሥራ ስድስት ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

Monday, May 11, 2015

የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተጠናቀቀ



ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም.
ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በጸሎት የተጀመረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲካሔድ ቆይቶ  ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ተጠናቅቆ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

Thursday, May 7, 2015

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ያስገነባው መንበረ ጵጵስና እና ጽ/ቤት ተመረቀ


001deb002deb
የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በደብረ ብርሃን ከተማ ያስገነባው ለመንበረ ጵጵስና እና ለጽ/ቤት አገልግሎት የሚውል ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሚያዝያ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡

Monday, April 20, 2015


ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ መግለጫ ሰጠ
                   
ሚያዚያ 12/2007
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በሊቢያ በአሸባሪው አይሲስ እጅ በሰማዕትነት የተሠውትን ኢትዮጵያውያን በተመለከተ ዛሬ ጠዋት 5፡30 ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከውጭ ሀገር ጉዞ ቀርተው በመንበረ ፓትርያርኩ የቅዱስ ሲኖዶሱን መግለጫ የሰጡ ሲሆን ሌሎች የእምነት ተቋማትም ተመሳሳይ መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
መግለጫውን ተመልከቱት፡፡

Wednesday, March 4, 2015

ዜና;-የቅዱስ ፓትርያርኩ በዓለ ሲመት 2ኛ ዓመት ተከበረ





 001abune matyas 1የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 2ኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሲመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከበረ፡፡

ቅዱስነታቸው በበዓሉ ላይ በሰጡት ቃለ ምእዳን “የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ጌታችን በሐዋርያት እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ ሐዋርያትም በበኩላቸው በተኳቸው ጳጳሳት እና ቀሳውስት ጠባቂነት ቤተ ክርስቲያን እንድትመራና እንድትጠበቅ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሐዋርያዊት፤ አንዲትና ቅድስት እንደመሆኗ መጠን ከመጀመሪያው አንስቶ መንፈሳዊውን ጥበቃ በጳጳሳትና በቀሳውስት ስታከናውን ኖራለች፡፡ አሁንም እያከናወነች ነው፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች” ብለዋል፡፡

ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጳጳሳትና ቀሳውስት የተሰጣቸውን የጠባቂነት ሚና አስመልክቶም “ይሁንና በዘመናችን እየተነሳ ያለው መሠረታዊ ጥያቄ የእግዚአብሔር መንግሥት ተጠሪ የሆኑት ጠባቂዎች ሓላፊነታቸውን በሚፈለገው ሁኔታ እየተወጡ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፋዊና የወቅቱ ጥያቄ ሆኖ ይገኛል፡፡ የእግዚአብሔር መንጋ የሆኑት ክርስቲያኖችን በባሕር ማእበል ሞገድ እንደሚናጥ መርከብ በጥርጣሬ እየተናጡ አጉል መንገድ ላይ እንዲቀሩ እያደረገ ነው፡፡ ከመንጋው ተነጥሎ እንደሚቅበዘበዝ በግ ባለማመን ማእበል እያንጓለሉት ነው፡፡ በጠባቂነት

ዜና:- በዝቋላ ገዳም ዳግም የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ





abune gebre menfes kidus 01 










በደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም በዛሬው እለት ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ በምሥራቅ አቅጣጫ በሚገኘው ደን ዳግም የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱ ከገዳሙ አባቶች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በትናንትናው እለት ተቀስቅሶ የነበረው እሳት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው እለት ተቀሰቀሰውን እሳት ለማጥፋት በገዳማውያኑ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት እሳቱ ደኑን እያወደመ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀጣጠለ እንደሚገኝ የገለጹት ገዳማውያኑ ከደብረ ዘይት አየር ኃይል ሄሊኮፕተር እንዲላክላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

Tuesday, February 17, 2015

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሱዳን ካርቱም ያደረጉትን ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ተመለሱ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሱዳን ከምትገኘው የኢትዮጵያ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቷ ልዑካንና ሊቃነ ጳጳሳትን አስከትለው በሱዳን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የተገነቡ የሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያና የከፍተኛ ኪሊኒክ ሕንፃዎች መርቀው ሥራ ለማስጀመርና ወደፊት ለሚሠሩት ሁለት ታላላቅ ህንፃዎች የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሱዳን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዘምራንና ምእመናን በከፍተኛ የአቀባበል ሥርዓት ተቀብለዋቸዋል፡፡

Saturday, February 14, 2015

ቅዱስ ፓትርያርኩ ዐብይ ጾምን አስመልከቶ መልእክት አስተላለፉ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን አስመልክቶ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. መልእክት አስተላለፉ፡፡

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን ሙሉ መልእክት ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡-


ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡

Thursday, January 29, 2015

/ዜና/ 50 የአቋቋም ደቀመዛሙርት ተመረቁ

 ጥር ፳፩ ፳፻፯ .

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ከተማ በደብረ ኃይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የአቋቋም ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ 50 ደቀ መዛሙርት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአብነት መምህራን እና ምእመናን የተገኙ ሲሆን፤ ደቀ መዛሙርቱ ከብፁዕነታቸው እጅ የአቋቋም ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ “አዝመራው ብዙ ነው ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው” በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተው ለተመራቂ ደቀመዛሙርቱ በተማሩት ትምህርት ወንበር ዘርግተው በማስተማርና ለምእመናን ትምህርት ወንጌልን በመስጠት በተለይም ለገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በመድረስ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ብፁዕነታቸው አያይዘውም “አሁን በዝታችሁ ትታያላችሁ፡፡ ነገር ግን በየቤተ ክርስቲያኑ ስትከፋፈሉ ቁጥራችሁ አነስተኛ ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ብቻ በዓመት ከ50 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናትን እንተክላለን፤ ለሁሉም እናዳርስ ብንል እንኳን በቂ አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየን አሁንም ብዙ መሥራት፣ መማር፣ ማስተማር እና የሊቃውንቱ ምንጭ እንዳይደርቅ ደቀመዛሙርትን ማፍራት ይገባል” ብለዋል፡፡

የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር መጋቤ አእላፍ ክቡር ጥላሁን ባስተላለፉት መልእክትም “እነዚህ ደቀ መዛሙርት ዛሬ ተመርቀዋል፤ ነገር ግን እየለመኑ ተምረው እየለመኑ መኖር የለባቸውም፡፡ በርካታ ደቀ መዛሙርት ከትምህርት ገበታቸው የሚሠደዱት ሥራ አላገኝም እያሉ ነውና እንደ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚመደቡበትን መንገድ ቢያመቻች ጥሩ ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ማኀበረ ቅዱሳን የሚያሰራውን G+2 ሕንፃ በተመለከተም መጋቤ አእላፍ ክቡር ሲገልጹ “ሕንፃው የማጠናቀቂያ ሥራ ብቻ ይቀረዋል፤ ማኅበሩ ከሕንፃው በተጨማሪ ለ40 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው በየወሩ የ100 ብር ድጋፍ ያደርጋል፤ ቤተ ክህነትም ለ30 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው 84 ብር በየወሩ ይደጉምልናል፡፡

ማኀበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ ዘመናዊ ቤት ሰርቶልናል ነገር ግን አሁንም ሠርከ ኀብስቱ እጥረት አሳሳቢ ስለሆነ ለተማሪው ፍልሰት ምክንያት እየሆነብን ነውና መፍትሄ እንሻለን፡፡ ደቀመዛሙርቱ የሚማሩት ከየሀገራቸው ትንንሽ ልጆችን እያስመጡ ልጆቹ በየመንደሩ በመንቀሳቀስ “በእንተ ስማ ለማርያም” ብለው ምግብ ያመጡላቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ እነዚህን ልጆች ያስተምሯቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ትምህርት ቤቶች ከዚህ በላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራት አለባት” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በሊቀ ብርሃናት ኤልያስ አድማሴ በዐብየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ወመርቆሪዎስ ቤተ ክርስቲያን የብሉያት መምህር ትምህርተ ወንጌል፣ በመምህር ጌዴዎን በርእሰ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ጉባኤ ቤት መምህር ቅኔ እና በደቀ መዛሙርቱ ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል፡፡

ጉባኤ ቤቱም በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ሲሆን፤ ለአብነት ያህል አለቃ ገብረ ሐና፣ መሪጌታ ሐሴት፣ መሪጌታ ገብረ ማርያም፣ መሪጌታ ገብረ ዮሐንስ፣ መሪጌታ አሚር እሸቱ፣ መሪጌታ ላቀው፣ መምህር ክፍሌ ወልደ ፃድቅ፣ መጋቤ አእላፍ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ቤቱ ከ200 ያላነሡ ደቀ መዛሙርት ይገኛሉ፡፡ በየዓመቱም የደቀመዛሙርቱ ምርቃት አይቋረጥም፡፡


Tuesday, January 27, 2015

በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር ዋለ

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ውስጥ ዛሬ፣ ጥር ፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከረፋዱ 4፡30 ላይ የተቀሰቀሰው እሳት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተገለጸ፡፡ቃጠሎው በቁጥጥር ሥር የዋለው ከቀኑ በ9፡00 ገደማ ሲኾን ይኸውም ከቤተ ክርስቲያኑ በግምት ከመቶ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ በደረሰበት ኹኔታ ነው ብለዋል – እሳቱን በማጥፋት የተራዱ የዐይን እማኞች፡፡
የዳጋ እስጢፋኖስን ጨምሮ ከሌሎች የደሴቱ ገዳማት የመጡ መነኰሳት፣ የአቅራቢያው ነዋሪዎች፣ ከባሕር ዳር ከተማ በጀልባ ተጓጉዘው የደረሱ አገልጋዮችና ምእመናን፣ የክልሉ መስተዳድር ተወካዮችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊዎች፣ የባሕር ዳር ዙሪያ ፖሊስና የምዕራብ እዝ ኃይሎች በጋራ ቃጠሎውን በማጥፋት ከፍተኛ የጋራ ርብርብ ማድረጋቸው ተገልጧል፡፡