Saturday, February 21, 2015

ሁለተኛ ሳምንት - ቅድስት



የካቲት ፲፬ ፳፻፯ ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓትና በትውፊት የበለፀገች መሆኗ የታመነ ነው፡፡ ሰፊ ሥርዓትና ትውፊት ያላት እንደመሆኗ መጠን የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትጾመው ጾም፤ የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትቆመው ማኅሌት በቂ ታሪክ፣ ትውፊትና ሥርዓት አለው፡፡ ያለታሪክ ያለትውፊትና ሥርዓት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትጾመው ጾም፤ የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትዘምረውም መዝሙር የለም፡፡


በዚህ በያዝነው ወቅት የምንጾመው ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም እንደመሆኑ መጠን በዚሁ የጾም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዘመነ ሥጋዌው ለሠራቸው የተአምራትና የትምህርት ሥራዎች መታሰቢያ በዓል በማድረግ ለእያንዳንዱ ሰንበት ስም በመስጠት በስሙ አንፃር የበዓሉን ታሪክ በመከተል ታመሰግናለች፤ ትዘምራለች፤ ትፀልያለች፤ ትቀድሳለች፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዓቢይ ጾም ውስጥ  ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ሰርቶላቸዋል፡፡ በመዝሙራቱ ውስጣዊ ምስጢር መሠረትም እያንዳንዱ እሑድ ስያሜ ተሰጥቶቸል፡፡ በዚሁም መሠረት ያሳለፍነውን ሳምንት ከቅበላው ዋዜማ ጀምሮ ዘወረደ ብለን በቤተ ክርስቲያናችን አክብረናል፡፡ በቀደመው ጽሑፋችንም የስያሜውን ትርጓሜ አይተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ እንደእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ የቀጣዩን ሰንበት/ሳምንት (የሁለተኛውን ሳምንት) ስያሜና ምሥጢሩን እንማማራለን፡፡ 



        ለአባቶቻችን ለቀደምት አበው ምሥጢሩን የገለፀ አምላክ ለእኛም ማስተዋሉን ያድለን፡፡
      

 ሁለተኛ ሳምንት - ቅድስት

ቅድስት ማለት ልዩ፣ ጽኑዕ፣ ክቡር ማለት ነው፡፡ የዓቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ሲሆን ለጌታ ጾም/ጾመ አርባ/ የመጀመሪያ ሳምንት ነው፡፡ ያለትናንት ቀዳማዊ፤ ያለዛሬ ማዕከላዊ፤ ያለነገ ደሃራዊ፤ ለዘመኑ ጥንትና ፍጻሜ ለግዛቱ ዳርና ድንበር የሌለበት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ጾሙን የጀመረበት የመጀመሪያው ሳምንት ቅድስት ተብሎ የመጠራቱ ምክነያት ከዚሁ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ የአምላካችንን ቅድስና እና ሰንበት ቀድሶ በፈቃዱ እንደሰጠን እያነሣሣ ስለሚዘምር ነው፡፡ 
ጾመ ድጓውም እንዲህ ይለዋል፡-
           ዛቲ ዕለት ቅድስት ይዕቲ - ይህች ቀን የተቀደሰች ናት
            ሰንበትየ ቅድስትየ እንተ አዕረፍኩ - ያረፍኩባት ቅድስት ሰንበት ናት
            ቅዱሳነ ኩኑ እስመ አነሂ ቅዱስ አነ - እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ
            አብ ቀደሳ ለሰንበት - አብ ሰንበትን አከበራት ቀደሳት

ስያሜው ሰንበት የዕረፍት ቀን እንድትሆን በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔር የባረካት የቀደሳት ዕለት መሆኑዋን የሚናገርና እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ የፈጠረውም ሰውም ቅድስናን መያዝ የሚገባው መሆኑን የሚያሳስብ ነው፡፡ /ዘፍ ፪፥፫ ፤ ዘፀ ፳፥፰-፲፩ ፤ ዘሌ ፲፱፥፪-፫ ፤ ፩ ጴጥ ፩፥፲፭-፲፮/

ከላይ እንደገለፅነው እቀደስ አይል ቅዱስ፤ እከብር አይል ክቡር፤ እነግስ አይል ንግሥና የባህሪዩ የሆነ አምላክ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ፤ የጾምን ጥቅምና ሥርዓቱንም ሊያስተምረን መጾም የጀመረበት ሳምንት ይህ ነው፡፡ ይህ ሳምንት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባህሪይ ቅድስና የሚነገርበት ሳምንት ነው፡፡ ስለዚህች ቀን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ እስመ አማልክተ አሕዛብ አጋንንት፤ እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፤ ቅድሳት በዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ/የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፡፡ ምስጋናና ውበቱ በፊቱ፤ ቅድስናና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡/መዝ ፺፭፥፭/ በማለት ቅድስናና ክብር የባህሪዩ መሆኑን ተናግሯል፡፡
እኛ ከርኵሰታችን የምንቀደስበትንና የምንከብርበትን ሥርዓት ሊሰራልን አንድም አዳም በመብል ምክነያት ከክብሩ ተዋርዶ ነበርና በአዳም ምትክ ተተክቶ ካሳ ሊከፍልለት በገዳመ ቆሮንቶስ ጌታችን መጾም መጀመሩን በዲያብሎስ መፈተኑንና ዲያቢሎስንም ድል መንሳቱን ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ሳምንት ታስተምረናለች፡፡


በዚህች ቅድሰት በተባለች ሳምንት እሑድ የሚነበቡት የቅዳሴ ምንባባት የሚከተሉት ናቸው፡፡
መልዕክታት፡
      ፩ኛ ተሰሎቄ ፬፥፮-፲፫
      አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደመሰከርንላችሁ፣ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል፡፡ ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና       ጠርቶናልና፡፡እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ፡፡ እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ ከእግዚአብሔር ተምሯችኋልና ስለወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤ እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና፡፡ ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፣ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፣ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን፡፡ ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ተስፋ እንደሌላቸው እንደሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ አንቀላፍተው ስላሉት ታውቁ ዘንድ እንወዳለን፡፡
     ፩ኛ ጴጥሮስ ፩፥፲፫ - ፳፭
      ስለዚህ የልቦናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን እየኖራችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ፡፡ እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ፡፡ ዳሩ ግን ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡ ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ፡፡ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት በከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም       በወርቅ ሳይሆን ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደበግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ       ታውቃላችሁ፡፡ ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፣ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፣ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለእናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ፡፡ ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት በሌለበት    ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አጽንታችሁ እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፡፡ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፣ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር    ቃል ከሚይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡ ሥጋ ሁሉ እንደሣር ክብሩም ሁሉ እንደሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል፡፡ በወንጌል የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው፡፡

         ግብረ ሐዋርያት፡
      የሐዋ.ሥራ ፲፥፲፯ - ፴
      ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ፣ እንሆ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች ስለስምዖን ቤት ጠይቀው ወደ ደጁ ቀረቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው፡- ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን በዚህ እንግድነት ተቀምጦአልን? ብለው ይጠየቁ ነበር፡፡ ጴጥሮስም ስለራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ፣ መንፈስ፡- እንሆ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ ውረድ፣ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ አለው፡፡ ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ እንሆ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክነያት ምንድር ነው? አላቸው፡፡ እነርሱም፡- ጻድቅ ሰው እግዚአብሔርንም የሚፈራ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ የተመሰከረለት የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ወደ ቤቱ ያስመጣህ ዘንድ ከአንተም ቃልን ይሰማ ዘንድ ከቅዱስ መልአክ ተረዳ አሉት፡፡ እርሱም ወደ ውስጥ ጠርቶ እንግድነት ተቀበላቸው፡፡ በነገው ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፣ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ በነገውም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ወጣ፣ በኢዮጴም ከነበሩት ወንድሞች አንዳንዶቹ ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ በነገውም ወደ ቂሣርያ ገቡ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን በአንድነት ጠርቶ ይጠባበቃቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስም በገባ ገዜ ቆርኔሌዎስም ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት፡፡ ጴጥሮስ ግን ተነሣ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው፡፡ ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፣ ብዙዎችም ተከማችተው አግኝቶ፡- አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ፤ ስለዚህም ደግሞ ብትጠሩኝ ሳልከራከር መጣሁ፡፡ አሁንም በምን ምክንያት አስመጣችሁኝ? ብዬ እጠይቃችኋለሁ አላቸው፡፡ ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፡- በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፡፡
         
          ምስባክ
      መዝ ፺፭፥፭                             


እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ
አሚን ወሰናይት ቅድሜሁ
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ


ትርጓሜውም፡-
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፡፡
ምስጋናና ውበቱ በፊቱ
ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡


    
          ወንጌል
     ማቴ ፮፥፲፮ - ፳፭
     ስትጦሙም፣ እንደግብዞች አትጠውልጉ፤ እንደጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ስትጦም፣ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደጦመኛ ለሰዎች እንደ እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም ያስረክብሃል፡፡ ብልና ዝገት የሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚህ ይሆናልና፡፡ የሰውነት መብራት ዓይን ናት፡፡ ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይን አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡ ስለዚህም እላችኋለሁ ስለነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፣ ወይም ስለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፡፡
                 


 ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment