Monday, May 1, 2017


ስንክሳር ዘሚያዝያ ፳፫




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አምላክ አመ ዕሥራ ወሠሉሱ ለሚያዝያ በዛቲ ዕለተ ኮነ ፍጻሜ ስምዑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕት ዐቢይ ወክቡር ዘተሰምየ ፀሐየ ወኮከበ ጽባሕ፡፡
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሚያዝያ ሃያ ሦስት በዚች ቀን ፀሐይና የአጥቢያ ኮከብ የተባለ ታላቅና ክቡር የሆነ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ የምስክርነት ፍጻሜ ሆነ፡፡

የዚህም ቅዱስ አባቱ መስፍን ነው፡፡ ስሙም አንስጣስዮስ ይባላል፡፡ ከቀጰዶቅያ አገር ነው፡፡ የእናቱም ስም ቴዎብስታ ይባላል ከፍልስጥዔም አገር ናት ታናሽ ሆኖ ሳለ አባቱ ዐረፈ፡፡

Tuesday, April 11, 2017

                               ሰሙነ ሕማማት

የሰሙነ ሕማማት ሃይማኖታዊና ቱፊታዊ ክንዋኔዎች

                        
  በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሳዕና ጀምሮ እስከ ትንሳኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት የሚገኙበት ሳምንታት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ዕለታቱም የዓመተ ፍዳ፣ የዓመተ ኩነኔ መታሰቢያ ናቸው፡፡ በእነዚህ ዕለታት ውስጥ የተለያዩ ትውፊታዊ እና ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ክንዋኖዎች ውስጥ አለመሳሳም፣ አክፍሎት፣ ቄጤማ ማሰር፣ ጥብጠባ፣ ጉልባን እና ሕፅበተ እግር ይገኙበታል፡፡ ስለእነዚህ ክንዋኔዎች በቅድስት ቤተ ክስቲያን ስላለው ትውፊታዊ አፈፃፀም መዛግብት አገላብጠን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አለመሳሳም፡- በሰሙነ ሕማማት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መስቀል እንደማይሳለሙት ሁሉ መጨባበጥ፣ መሳሳምን የትክሻ ሰላምታ መለዋወጥን አይፈጽሙም፡፡ ሰላምታ የማንለዋወጥበት ምክንያት አይሁድ ጌታን ለመስቀል ሰኞ እና ማግሰኞ መከሩ አልሰመረላቸውም፡፡ ምክረቸው የተፈጸመው ረቡዕ ነው፡፡ ስለዚህ አይሁድ እያንሾካሾኩ እንሰቀለው ፤እንግለው ብለው ይማከሩ ነበር፡፡ በዘመነ ፍዳ ወቅት ሠላምና ፍቅር አለመኖሩን የሚገልፅልን በመሆኑ ያንን ለማስታወስ ስላምታ አንለዋወጥም፡፡ መስቀልም አንሳለምም፡፡ ሳምንቱ የክፋት ምክር የተመከረበት እንጂ የፍቅርና የደስታ ሳምንት የታየበት ባለመሆኑ ይህንን በማሰብ ሰላምታ አንለዋወጥም፡፡ አይሁዳ ጌታን በጠላቶቹ ለማስያዝ እኔ የምስመው እርሱ ነው ያዙት ብሎ በሰላምታው ምልክት ሰጣቸው ይህ ሰላምታ አምሐ ቅድሳት አይደለም ተንኮል የተሞለበት እንጂ፡፡ የዲያቢሎስም ሰላምታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሔዋንን ስላም ለኪ ብሎ ነው ያታለላት የይሁዳም ሰላምታ ሰይጣናዊ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ወቅትና ሁኔታ ለማሰብ በሰሙነ ሕማማት ሰለምታ ልውውጥ የለም፡፡ ዛሬ እየተስተዋለ ያለው ይኽው ሰላምታ ያለመለዋወጥ ሁኔታ ስርወ መሰረቱ ይህ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እዚህ ትውልድ ላይ ደርሷል፡፡ ይቀጥላልም፡፡

Friday, February 10, 2017

               የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ

 የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ሲባል ምን ማለት ነው? የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የከበረ በመሆኑ እንደተገኘ የሚጠሩት፣ እንደአጋጠመ የሚናገሩት አይደለም፡፡ ይልቁንም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በትሕትና ሆነው ሊጠሩት የሚገባ ክቡር ስም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ያለአግባብ በነገራቸው ሁሉ ውስጥ ሲያስገቡት፣ ሥፍራም ጊዜም ሳይመርጡ እንደፈለጉት ሲጠሩት ይስተዋላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እምነትና ፊሪሃ እግዚአብሔር አላቸው ለማለት አያስደፍርም፤  

ከዚህ ቀጥለን ሰዎች ስሙን በከንቱ የሚጠሩባቸውን ሁኔታዎች ባጭር ባጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

.መሐላ- መሐላ ስመ እግዚአብሔር በከንቱ ከሚጠራባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡በዘመነ ብሉይ የአምልኮ ጣዖትን ከንቱነት ለመግለጥ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡ በስሙ እንዲምሉ ያዝ ነበር(ዘዳ 6:13ኢሳ 45:23)፡፡በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በእግዚአብሔር መማል ብቻ ሳይሆን መሐላ በጠቅላላው የተከለከለ መሆኑን መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ይህ የሐዲስ ኪዳን ዘመን አረማዊነት ና አምልኮ ጣዖት ጠፍቶ ወንጌል የተሰበከበት፣ክርስት ና በዓለም ሁሉ የታወቀበት ነውና መማል አላስፈለገም፡፡ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ #ከቶ አትማሉ፤ቃላችሁ አዎን፣አዎን ወይም አይደለም፣አይደለም ይሁን፣ከዚህም የወጣ ከክፉው ነው$በማለት መሐላን ከልክሏል (ማቴ 5:34-37)፡፡ስለሆነም በየሰበቡ የእግዚአብሔርን ስም፣የቅዱሳንን ስም፣የመላእክትን ስም ሁሉ እየጠሩ መማል የተከለከለ ነውና ከዚህ መቆጠብ ይገባል፡፡በተለይም በየአጋጣሚው ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩ መማል የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት መሆኑንበሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡