Friday, February 10, 2017

               የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ

 የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ሲባል ምን ማለት ነው? የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም የከበረ በመሆኑ እንደተገኘ የሚጠሩት፣ እንደአጋጠመ የሚናገሩት አይደለም፡፡ ይልቁንም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ በትሕትና ሆነው ሊጠሩት የሚገባ ክቡር ስም ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም ያለአግባብ በነገራቸው ሁሉ ውስጥ ሲያስገቡት፣ ሥፍራም ጊዜም ሳይመርጡ እንደፈለጉት ሲጠሩት ይስተዋላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች እምነትና ፊሪሃ እግዚአብሔር አላቸው ለማለት አያስደፍርም፤  

ከዚህ ቀጥለን ሰዎች ስሙን በከንቱ የሚጠሩባቸውን ሁኔታዎች ባጭር ባጭሩ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

.መሐላ- መሐላ ስመ እግዚአብሔር በከንቱ ከሚጠራባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡በዘመነ ብሉይ የአምልኮ ጣዖትን ከንቱነት ለመግለጥ እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቡ በስሙ እንዲምሉ ያዝ ነበር(ዘዳ 6:13ኢሳ 45:23)፡፡በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በእግዚአብሔር መማል ብቻ ሳይሆን መሐላ በጠቅላላው የተከለከለ መሆኑን መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ይህ የሐዲስ ኪዳን ዘመን አረማዊነት ና አምልኮ ጣዖት ጠፍቶ ወንጌል የተሰበከበት፣ክርስት ና በዓለም ሁሉ የታወቀበት ነውና መማል አላስፈለገም፡፡ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ #ከቶ አትማሉ፤ቃላችሁ አዎን፣አዎን ወይም አይደለም፣አይደለም ይሁን፣ከዚህም የወጣ ከክፉው ነው$በማለት መሐላን ከልክሏል (ማቴ 5:34-37)፡፡ስለሆነም በየሰበቡ የእግዚአብሔርን ስም፣የቅዱሳንን ስም፣የመላእክትን ስም ሁሉ እየጠሩ መማል የተከለከለ ነውና ከዚህ መቆጠብ ይገባል፡፡በተለይም በየአጋጣሚው ስመ እግዚአብሔርን እየጠሩ መማል የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት መሆኑንበሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡