Sunday, February 15, 2015

ዐቢይ ፆም እና የዐቢይ ፆም ሳምንታት ስያሜ /ክፍል አንድ/






ከቃሉ ስንነሳ ‹‹ዐቢይ ፆም›› ማለት ዋና ፆም፣ የአፅዋማት ሁሉ የበላይ ፆም ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስያሜውን ያገኘው ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፵(አርባ) መዓልት ፵(አርባ) ሌሊት የፆመውን ፆም በማሰብ የሚጾም ስለሆነ ነው(ማቴ ፬፥፩)፡፡ ፆሙን አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ብቻ ስለምን አደረገው ቢሉ ቀድሞ አባቶቻችን ነቢያት አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ፁመዋልና ከዚያ አትርፎ ቢጾም አተረፈ፤ ቢያጎድል አጎደለ የአባቶቻችንንም ሥርዐት አፈረሰ ብለው አይሁድ  ሕገ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ (አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉት ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ንዋይ ናቸው) ድል አድርጎበታል፡፡አንድም ሙሴ በአርባ ዘመኑ ለዕብራዊ ረድቶ ግብፃዊውን ገድሎ በኆፃ ቀብሮታል፡፡ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ ዕብራዊ የአዳም፤ ግብፃዊው የዲያብሎስ፤ ኆፃ የመስቀል ምሳሌ  አንድም የሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ምሳሌ ነው፡፡ ሙሴ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጹሞ ህገ ኦሪትን ሠርቷል
እርሱም አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጹሞ ወንጌልን የሚሠራ ነውና ነው፡፡ ሙሴ አርባ ዘመን በምድያም ኑሮ ከግብፅ አውጥቷቸዋል እነርሱም አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጹሞ ነፍሳትን ነፃ የሚያወጣ ነውና ነው፡፡ እናንተም ብትጾሙ እስራኤል ከግብፅ ወጥተው ምድረ ርስትን እንደወረሱት ርስተ መንግስተ ሰማያትን ትወርሳላችሁ ሲል ይህንን አስተማረን፡፡

በተጨማሪም ኤልያስ አርባ መዓልትና ሌሊት ፆሞ ብሔረ ህያዋን ገብቷል፡፡ እናንተም ብትጾሙ ገነት መንግስተ ሰማያት ትገባላችሁ ለማለት ሕዝቅኤል በፀጋ ማይ ጐኑ አርባ ቀን ተኝቶ ስድስት መቶ ሙታን አስነስቷል እናንተም ብትፆሙ በትንሳኤ ዘለክብር ትነሳላችሁ ለማለት ሌሎችንም አብነት በማድረግ ምስጢሩን ሊነግረን ሊያስተምረን ስለወደደ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በገዳመ ቆሮንቶስ አሳለፈ፡፡ ይህም ሥራውን ሰርቶ ስሩ አለ እንጂ ‹‹ባልዋጁበት ጣት የዘንዶ ጉድጓድ ይለኩበት›› እንዲሉ ሳይሠራ እኛን ሥሩ አላለንም፡፡ በዚህም ምክንያት ዐቢይ ፆም ብለን እንጾመዋለን፡፡


ታዲያ እርሱ የፆመው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ነው ነገር ግን በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ቀናቱ ሃምሳ አምስት ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆን ቢሉ በመጀመሪያ ንጹሐ አእምሮ ያለው ሰው ፆም ለእኛው ጥቅም ሲባል የተሰራ ስራ ሲሆን አብዝተን ብንፆም የምንጠቀመው እኛ እንጂ ለእግዚአብሔር የምንጨምርበት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ስለዚህ አብዝቶ መፀለይ፣ ቀኑን ጨምረን መፆም ጥቅማችንን እያበዛልን የሚሔድ በመሆኑ ይህንን ከግንዛቤ ባናስገባው ይመረጣል፡፡ ነገር ግን መልሱ የሚሆነው በመጀመሪያ የፆሙ ጊዜ ሃምሳ አምስት ቀን ነው ማለት ሁሉም ቀናት ላይ ተፁሞ ይዋላል፤ ይታደራል ማለት አይደለም፡፡ ከእነዚህ ሃምሳ አምስት ቀናት(አንድ ወር ከ ፲፭ ቀናት) ቅዳሜ እና እሁድ ተፁሞ ስለማይዋልባቸው በእነዚህ ሃምሳ አምስት ቀናት ያሉትን ቅዳሜና እሁዶች ስናወጣቸው አርባ ቀናት ብቻ ይቀሩናል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ፆሙ በትክክል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማስተማር የፆመው ፆም ምሳሌ ነው ማለት ነው፡፡                                  

የዐቢይ ፆም ሳምንታት ስያሜ

የመጀመሪያ ሳምንት - ዘወረደ


ቃሉ ወደ (‘ረ’ - ይላላል) ካለው የግዕዝ ግስ የመጣ ሲሆን ወደ (‘ረ’ - ይጠብቃል)፤ መውረድ የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ ታዲያ በዚህ በመጀመሪያው ሳምንት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት የሚደርሱት ፀሎቶች በሙሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከድንግል ማርያም መወለድ የሚያወሱ በመሆናቸው ለኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን ብርሃን የተባለ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ዘወረደ ብሎ ሰይሞታል፡፡"ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ" እንዳለው ሊቁ ድጓ በተሰኘው ድርሰቱ፡፡ ወደ አማርኛው ስንመልሰው - ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት ሁን ብሎ በቃሉ የማዳን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም ይለዋል፡፡

የአምላክ ሰው መሆን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ


W  ለምን አምላክ ተወለደ?
W  እንዴት ተወለደ?

ክርስቶስ ማለት ፈጣሪ እና ፍጡር አንድ ባሕሪይ በመሆን አንድ ሆነ ማለት ነው፡፡ ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ለዘለዓለም የሚኖር ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነውና ስለእርሱ ስንናገር ያልተፈጠረ ነው እንላለን፡፡ ክርስቶስ ተወለደ ስንል ስለኛ ባደረገው ተዋሕዶ ደካማ ባህሪያችንን ስለተዋሐደ ነው፡፡ ቃል ያልተፈጠረ ነውና ከሁሉ አስቀድሞ የነበረ ነው፡፡ በዘመኑም ሁሉ በእግዚአብሔር ሕልውና ያለ ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ነው ከተፈጠረውም ፍጥረት ሁሉ ምንም እርሱ ያልፈጠረው የለም(ዮሐ ፩፥፩-፲፩)፡፡

አዳም ባደረገው አመፅ ገነትን አጥቶ በምድር እየተቀጣ እንዲኖር የፈረደበት አምላክ ንስሐውን ተመልክቶ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ይህም ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚል ነው፡፡ ‹‹ሰማይና ምድር ያልፋል ቃሌ ግን አያልፍም›› ብሎ የተናገረ ጌታ ቃሉን ሳያጥፍ በድንግል ማኅፀን አደረ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንዋ ተሸከመችው፡፡ የሔዋን እርግማን በእርሷ የሌለባት ንፅህት ቅድስት ድንግል ማርያም በከብቶች በረት ወለደችው(ማቴ ፩፥፲፰ ሉቃ ፪፥፯)፡፡ እኛ የሰው ልጆች በፈቃዳችን የጠላታችንን የዲያብሎስን ማታለል በመቀበላችን ከህይወት ሞትን፤ ከተድላና ደስታ ኃሣርን መርጠን ወደን በሠራነው ኃጢአት ፍፃሜ ወደሌለው ወደዘለዓለም ኵነኔ በሚወስድ በሚጎዳ መከራ ውስጥ ወደቅን፡፡ ነገር ግን እርሱ ፈፅሞ አልተወንም በከሀሊነቱ ተቀበለን እንጂ በይቅርታው በቸርነቱ ብዛት ወደ እርሱ አቀረበን እንጂ /ኤፌ ፪፥፲፰/፡፡ በከበሩ በነቢያት ቃል አስቀድሞ እንዳናገረ ቀዳማዊ ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ስጋን ነስቶ ኃጢአታችንንም ደመሰሰልን፡፡በተጨማሪም የፍቅርን ህግ እና የወንጌልን ስርዓት እንድንጠብቅ ያስተምረን ዘንድ በፍፁም ፍቅሩ ሰውን በመውደዱ ካለመኖር ወደመኖር ያመጣውን የሰው ልጅ እንዳይጠፉበት በመፍቀዱ በድንግል ማኅፀን አደረ፡፡ ከድንግል ተወለደ እንደሕፃናትም አደገ ስለዚህ ፍቅሩን በማያልቅ የባሕሪይ የፍቅር ብዛት ገለፀልን፡፡

ስለዚህም የአምላክ ሰው መሆን የዓለምን ኃጢአት እንዳስተሰረየ ሁሉ አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ ሆነ ተብሎ የተነገረለት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዶ የሰውን ልጆች በደል ደመሰሰ አሁንም ‹‹በእንተ ልደትከ መሐረነ እግዚኦ›› እያልን ስለሰው ልጆች ስትል መከራን ለመቀበል የተወለድክ አምላክ ሆይ እኛንም ማረን፣ ይቅርም በለን፣ እራራልን እያልን የእርሱን መወለድ እያሰብን ያስተማረውን ትምህርት እየተገበርን እና የፆመውን ፆም እየፆምን ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን የምንለምንበት የፆም ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም በማስተዋል እና በፍቅር እንዲሁም በተረጋጋ አእምሮ ሆነን መፆም ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ይቆየን!!!              

3 comments:

Unknown said...

ቃለ ሕይወት ያሰማልን

Unknown said...

ቃለ ሕይወት ያሰማልን

Unknown said...

kalehiwot yasemalin

Post a Comment