Thursday, March 10, 2016

አርጋኖን

የመዝሙር መሳሪያዎች በተነሳ ቁጥር ይሄ አርጋኖን የተሰኘ የዜማ እቃ በቤተክርስቲያን አባቶችና አንዳንድ ሰዎች ዘንድ ልዩነት እየፈጠረ እስከአሁን ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የአሜሪካው "ሲኖዶስ" ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቡነ መልከጼዴቅ አርጋኖን/ኦርጋን ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የምስጋና ዕቃ እንዲሆን  አውጀዋል፡፡ እንዲህ ነው አንዲያ ነው ከማለት በፊት የአርጋኖንን ጥነተ ነገሩን ጥንተ መሠረቱን መመርመር ተገቢ ነው፡፡

ኦርጋኖንአርጋኖን የግሪክ ቃል ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ መሣርያ ማለት ነው፡፡ ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ አሪስቶትል (አሪስጣጣሊስ) ኦርጋኖን የሚለውን ቃል የስነ አመክንዮ መሳሪያ ወይም የሐሳብ መግለጫ መንገድ ዘዴ በማለት ቃሉን ተጠቅሞታል፡፡ነገር ግን በ3ኛው መ/ክፍለ ዘመን ቅ.ል.ክ ክቲሲቢዮስ ዘእስክንድርያ የተባለ ግሪካዊ ተመራማሪና መሐንዲስ ሃይድሮሊስ (የውሃ ኦርጋን) የተሰኘ የዜማ መሣሪያ ከፈለሰፈ በኋላ ኦርጋኖን የሚለው ቃል የዜማ ዕቃ/መሣሪያ የሚለውን ትርጉም ጨምሮ ወርሷል፡፡ ይህ የሙዚቃ መሣርያ በጥንት ዘመን የአደባባይ መዝናኛ በዓላት ማድመቂያ በመሆን በሰፊው  አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር በታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቧል፡፡ በተደረጉ የአርኪዮሎጂካል ቆፋሮዎችም ይህ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ አመት ገደማ ያስቆጠረ ጥንታዊ መሳሪያ ከተቀበረበት ወጥቶ በአውሮፓ ሙዚየሞች ለእይታ በቅቷል፡፡ ነገር ግን ከ 5ኛው ክፍለ ዘመን ድ.ል.ክ በኋላ ተቀባይነቱ ቀንሶ በሌሎች እርሱን መሰል የተሻሻሉ መሳሪያዎች (ፓይፕ ኦርጋን፣ ሪድ ኦርጋን፣ ቸርች ኦርጋን) ተተክቷል፡፡ ይህ ሃይድሮሊስ ወይም ኦርጋኖን የተባለ የዜማ መሣሪያ አሁን ኦርጋን ለተሰኙት ባለቁልፍ ሙዚቃ መሣሪያዎች ቅድመ አያታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ኦርጋኖን/አርጋኖን በዘመናችን ኦርጋን የሚለው ቃል ይተካዋል፡፡ አርጋኖንን በገና ብለው የተረጎሙ አሉ፡፡ ይህ ማለት ግን አርጋኖን በገና ነው አያሰኝም፡፡በገና የክር መሰሪያ ሲሆን አርጋኖን ደግሞ ከቁልፍ መሣሪያዎች ጎራ የሚመደብ ነው፡፡ አርጋኖን ኦርጋን አደለም ብሎ መሟገትም አያዋጣም፡፡

እንግዲህ ስለ አርጋኖን አመጣጥ ይህን ካልን፡፡ ሊቃውንት ቤተክርስቲያን ስለ አርጋኖን ምን እንዳሉ እንመልከት፡፡ አርጋኖን የሚለውን ቃል ቅዱስ ያሬድ በዜማ ድርሰቶቹ ጠቅሶታል፡፡
ሰባኬ ወንጌል ዮሐንስ አርጋኖነ ትንቢት ዘይደምጽ ለቤተ ክርስቲያን…ወንጌልን የምትሰብክ ዮሐንስ ለቤተክርስቲያን ሰናይ ድምጽን የምታሰማ የትንቢት አርጋኖን ነህ በማለት ቅዱስ ያሬድ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድን በድጓው አወድሷል፡፡ በተጨማሪም በማክሰኞ አርያሙ  ከመ ዝብጠተ መሰንቆ አርጋኖን ስብሐቶሙ ለእሙንቱ ካህናት…የካህናቱ ምስጋና መሰንቆ አርጋኖን ሲመታ እንደሚያወጣው ሰናይ ድምጽ ጣፋጭ ነው ባሏል፡፡

ቅዱስ ያሬድ የካህናትን ጥዑም ድምጽ፣ የሐዋርያትን ስብከት ከአርጋኖን ጋር መስሎ  ይህን ሲል በሁለት መንገድ ልንተነትነው እነችላለን፡፡  አንደኛው  አርጋኖን የሰኘውን የዜማ መሣሪያ ቅዱስ ያሬድ በነበረበት ወቅት አገልግሎት ላይ ስለነበር የመሣሪያውን መልክና ቁመና እንዲሁም ድምጹን ያውቀዋል፤ ሁለተኛው  ደግሞ ቅዱስ ያሬድ ከመጻሕፍት አግኝቶ ለድርሰቱ ውበት ተጠቅሞታል፡፡ ያም ሆነ ይህ አርጋኖን የተባለውን የዜማ መሣርያ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ከመሰንቆ፤ ከእንዚራ ጋር አስተባብሮ ቅዱሳንን ለማመስገን መስሎ አቅርቦታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በነበረበት ዘመን አርጋኖን አግልግሎት ላይ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም ቅዱስ ያሬድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዜማን ሲደርስ ወደ አርያም ተነጥቆ ካያቸውና ከሰማቸው  የዜማ ዕቃዎች አንዱ ኦርጋኖን/ኦርጋን እንደነበር ገድለ ያሬድ ይተርካል፡፡

ወሰምዐ በህየ ቃለ እንዚራ ወቃለ አርጋኖን ወቃለ መሰናቅው እንዘ ይሴብሕዎ ወይዌድስዎ ወየአኵትዎ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር በስብሐት ወበማኅሌት…በዚያም የእንዚራን፣ የአርጋኖንን፣ የመሰንቆን እንዲሁም ሰማይና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔርን በስብሐትና በማኅሌት ሲያመሰግኑት ሰማ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም የቅዱስ ያሬድን የምስጋና ፈለግ ተከትሎ እመቤታችንን በአርጋኖን በመመሰል ብዙ የውዳሴ ድርሰቶችን ለቤተክርስቲያን አበርክቷል፡፡

እንግዲህ ሊቃውንቱ አርጋኖንን እንደ ምሳሌ ከመጠቀም ያለፈ ነገር አልተናገሩም፡፡ የኢትዮጽያ ቤተክርስቲያን አባቶችም ይህ አርጋኖን የተሰኘ የዜማ እቃን ተጠቅመው ሲያመሰግኑ በታሪክ ተመዝግቦ አላገኘንም፡፡ ሆኖም በኦርጋን የሚደርስ ምስጋና የረከሰ እግዚአብሔር የማይቀበለው፤ በዋሽንትና ክራር የሚደረግ ግን የተቀደሰና እግዚአብሔር የሚቀበለው እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ግን የተሳሳተ ነው፡፡ መቃወማችን እግዚአብሔር በአርጋኖን/ኦርጋን አይመሰገንም ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ምክንያቱም የዜማ ዕቃዎች ሁሉ ሰው ሰራሽ ናቸው፡፡ ከሰማይ የወረደ በገና፤ ከሰማይ የወረደ ከበሮ፤ ከሰማይ የወረደ መሰንቆ የለንም፡፡ ኦርጋንን የሰራው ሰው ነው  በገናውም የሰው ፈጠራ ነው ያውም የመጀመሪያ አላማው ለዘፈን ነበር ዘፍ. 4፡ 21 ፡፡ ዋሽንቱም ብትሉ ጣዖት ማጀቢያ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል ዳን 3፡ 5-7፡፡ ሰው ባለው ባገኘው እንደየባሕሉ ማመስገን ይችላል፡፡ለሰይጣን ንብረት የለውም፡፡ ቁም ነገሩ አጠቃቀማችን ላይ ነው፡፡ ግዴታ በመሰንቆና ዋሽንት ካልሆነ አይባልም፡፡ እግዚአብሔር በከበሮና ጸናጽል በክራርና ዋሽንት ብቻ ካላመሰገናችሁኝ አልቀበልም አላለም፡፡  

ኧረ ለመሆኑ ክራርና ቤስ ክራር እያቀላቀሉ በያሬዳዊ መዝሙር ስም ጆሯችንን ያደነቆሩት ዘማሪዎቻችንን አሜን ብለን ተቀብለን ይኸው በየታክሲው በየመዝሙር ቤቱና በየመሸታ ቤቱ ስናስጮቸው አይደል የምንውለው? የሲኖዶሱ ቀኖናስ ከተሻረ አልሰነበተም ወይ? በየትኛው የሲኖዶስ ጉባዔ ወይም በየትኛው ሐዋርያዊ ቀኖና ነው ክራርና ቤዝ ክራር የመዝሙር መገልገያ ዕቃ ሁነው የተመዘገቡት? አቡነ መልከጼዴቅ በዚህ ነገር ልክ ብለዋል፡፡ ክራሩን ተቀብለን የኦርጋን ነገር ሲነሳ የሚያስነጥሰን ከሆነ ችግር ነው፡፡

ነገር ግን ይህን ሲባል ኦርጋን ቤተክርስያናችን ይግባ ለማለት አይደለም፡፡ ይህን መወሰን የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶሱ ብቻ ነው፡፡ ዲያቆን እገሌ፣ ቄስ እገሌ መምህር እገሌ ስለተናገረ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ስልጣኑ የቅዱስ ሲኖዶሱ እና የቅዱስ ሲኖዶሱ ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በኦርጋን እንድናመሰግን አልፈቀደም፡፡ በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ኦርጋንና ሌሎች ዘመነኛ የዜማ ዕቃዎች አያስፈልጓትም፡፡ ያሉት የዜማ ዕቃዎች በቂ ናችው፡፡  ስለዚህ ስርአተ ቤተ ክርስቲያንን ከማስጠበቅ አንጻርና ወደፊት ኦርጋንን ተከትሎ ከሚመጣ ስርአት አልበኝነትና ጋጠወጥነትን እስቀድሞ ከመከላከል ረገድ ኦርጋንና ሌሎች ዘመናዊ የዜማ መሣሪያዎችን ከቤተክርስቲያን ማራቁ ተገቢ ነው፡፡

ሐዋርያት በየትኛውም የዜማ መሳሪያ ተጠቅመው ሲያመሰግኑ አልተመዘገበም፡፡ በዘመነ አበው የነበሩ እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ፣ አውሳቢዮስን የመሰሉ  ታላላቅ የቤተክርስቲያን አባቶችም የዜማ መሳሪያን ተጠቅመን የአምልኮ ሥርዓት እንድንፈፅም አላዘዘኑም አላስተማሩንምም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የሐዲስ ኪዳን አማኝ የሆንን እኛ ክርስቲያኖች ከዜማ መሳሪዎች ርቀን በልባችን እንዚራ በአንደበታችን መሰንቆ ብቻ ማመስገን እንደሚገባን ሰብከዋል፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

No comments:

Post a Comment