Saturday, March 14, 2015

ደብረ ዘይት




ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ እንደምትገኝ ይነገራል፡፡ በዚህች ተራራ ሐዋርያት ስለ ዳግም ምጽአት ፣ ስለ ዓለም ህልፈት መቼና እንዴት እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ጌታን ጠይቀውታል፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ ሲቀርብ የሚታዩትን ምልክቶች በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ (ማቴ 24 ፥ 1) በዚህ ሰንበትም ይህ ታሪክ የሚዘከርበት በመሆኑ ሳምንቱ በተራራው ስም ተሰይሟል፡፡

እንግዲህ በብሉይ ኪዳን  ዘመን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ የደብረ ዘይትን ተራራ ዐቀበት እንደወጣ (2ኛሳሙ 15 ፥ 30) ላይ እናነባለን፡፡ቤተ ፋጌና ቢታንያ የሚባሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባ እናነባለን፡፡ ጌቴሴማኒ የሚባለው ጌታችን የጸለየበት ቦታ ከደብረ ዘይት ስር ይገኛል፡፡(ማቴ 26 ፥ 30-36) ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገው በደብረ ዘይት ላይ ነው(ሉቃ 24 ፥ 1-52 ፣ ግ.ሐዋ 1 ፥ 12)፡፡ እግዲህ እነዚህ ሁሉ በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ደብረ ዘይት የተነገሩ ናቸው፡፡ 
   

መድኃኒታችን በደብረ ዘይት በሰፊው አስተምሯል (ማር 13 ፥ 3)፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቅደስ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት  በሄደበት ሰዓት ደቀመዛሙርቱ አጠገቡ ቀርበው ዘሩባቤል ያሳነፀውን የመቅደስ ግንቦች እያሳዩት ሳለ እውነት እላችኋለሁ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም  አላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የኢየሩሳሌምን መፍረስ የእርሱንም መምጣት አስፍቶ አምልቶ ከነምልክቱ አስተማራቸው፡፡

ዳግም ምጽአት ስንል  ሁለተኛ ጊዜ መምጣት ማለት ነው፡፡ ይኸውም ዳግም ብሎ  ተናገረ ስለክርስቶስ ነው፡፡ “………..  በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጧል…….አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ ያድናቸው ዘንድ ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል፡፡” (ዕብ 9፥26-28) ሐዋርያው ከዚህ በላይ በተመለከትነው መልእክቱ መድኃኒታችን ለሁለት የተቀደሱ ዓላማዎች ወደ ዓለማችን ሁለት ታላላቅ ምጽአቶችን እንዳደረገ እና እንደሚያደርግ ያስገነዝበነናል፡፡

  • የመጀመሪያው ክርስቶስ ወደዚህች ምድር በማህፀነ ማርያም ተወስኖ ፣ተወልዶ  ሥጋ በመልበስ ለሰው መስዋዕት ሆኖ ሊያድን ለካሳ በፍጹም ትህትና የእኛን ውርደት ተቀብሎ የተገለጠው መገለጥ ሲሆን
  • ሁለተኛው (ዳግም ምጽአቱ) ግን የተለየ እና ዓለምን ለማሳለፍ እንደሚገለጥ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት በፍፁም ጌትነት በኃጥአን ( የመጀመሪያውን ምጽአቱን ባልተቀበሉት ላይ) ሞትን ሊፈርድ አይን ሁሉ እየተመለከተው በገህድ ይመጣል “እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፤” እንዲል መዝሙረኛው (መዝ 49 ፥ 3)፡፡ ለምዕመናን የሚሆነው ክብርም ያን ጊዜ ይገለጣል ኃጥእ ያፍራል ጻድቅ ይከብራል፣ ሞት ይሻራል፣ ሕይወት ይነግሳል ጻድቅ ሁለተኛ ላይሞት ይነሳል የምድር ሥርዓት ይሻራል ፍጥረት ሁሉ አንድ መንጋ ይሆናል በአንድ እረኛ  ይሰማራል፡፡
     
የዓለም መጨረሻ  የኢየሱስ ክርስቶስ መምጫ ምልክቶች

  • ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በክርስቶስ ስም ብዙዎችን ያስታሉ(ማቴ 24 ፥ 4-5)
  • የጦርነት ወሬ የዓለምን የዜና ጊዜ ያጣብባል በዓለም ዙሪያም ሰፊ ጦርነት ይደረጋል፣ የጦርነትም ወሬ ፍጥረት ሁሉ ይሰማ ዘንድ ግድ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ግን በዚህ ጊዜ የክርስቶስን መምጣት በናፍቆት ሊጠብቁ እንጂ ሊደነግጡ  አይገባም፡፡ (ማቴ 24 ፥ 6)

  • ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግስትም በመንግስት ላይ ይነሳል ሕዝብ እርስ በርሱ ይለያያል፡፡አንዱ መንግስት ሌላውን መንግስት ሊያምነው አይችልም፡፡ (ማቴ 24 ፥ 7)

  • ረሀብ ድርቅ ቸነፈር፣ የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡ እነዚህ የምጥ መጀመሪያ ናቸው፡፡(ማቴ 24 ፥ 8)

  • በዚያን ጊዜ በክርስቶስ የሚያምኑ ሰሰዎች ለመከራ ተላልፈው ይሰጣሉ፣ይገደላሉ፣ ስለስሙም በአሕዛብ ዘንድ የተጠሉ  ይሆናሉ፡፡ (ማቴ 24 ፥ 10)
  • ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት መምህራን ይነሳሉ ብዙዎቹንም ያስታሉ ዓመፃ ይበዛል የብዙዎችም ፍቅር ይቀዘቅዛል በዚያ ጊዜ ግን እስከመጨረሻው የፀና ግን እርሱ ይድናል፡፡ (ማቴ 24 ፥ 11-13)
  • ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆንባቸው በሰማያዊው ንጉስ ፊት ያለምክንያት ለፍርድ እንዲቆሙ የእግዚአብሔር ሕገ መንግስት በእስላም ቤት ሳይቀር ለሁሉም ይሰበካል፡፡ በዚያ ጊዜ መጨረሻው እየቀረበ ይመጣል፡፡ (ማቴ 24 ፥ 14)
  • በዚያ ሰዓት በነብዩ ዳንኤል እንደተባለው የጥፋት ሰው በጽድቅ ስፍራ የርኩሰት ሰው በተቀደሰው ሥፍራ ቁሞ ይታያል፡፡ ክፉ ዲያብሎስ በሐሳዊ መሲሕ  (በአውሬው ሰው) አድሮ የተቀደሰውን ያረክሳል የታነጸውን ያፈርሳል፡፡ (ማቴ 24 ፥ 115)


እንግዲህ ከላይ የተመለከትናቸው ምልክቶች እና ሌሎችም በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፉት በሙሉ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸው ናቸው፡፡ የሚገርመው ደግሞ በአሁኑ ሰዓት አብዛኛዎቹ ትንቢቶች መፈጸማቸው ነው፡፡ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ለሰው ልጆች ብሎ ሊሰቀል ወይም ሊገረፍ አይደልም የሚመጣው ለመፍረድ ነው፡፡ አቤቱ ያቺ ሰዓት ምን ያህል የምታስፈራ ናት? ምን ያህልስ የምታሰጨንቅ ናት? ወገኖቼ ክርስቲያኖች ሆይ የመድኃኒታችን ሁለተኛ መገለጥ ለእኛስ ለምን ይሆን? ለዘለዓለማዊ ህይወት ወይስ ለዘለዓለማዊ ሞት?
   
             ጌታ እግዚአብሔር ከሞት ያድነን፣ በሞት የማይሻረውን ሕይወት ይስጠን፡፡ አሜን!

1 comment:

Unknown said...

kale hiwet yasemalen

Post a Comment