Friday, September 23, 2016

                                ደመራ                  


        ደመራ፣ ደመረ ጨመረ ካለው የግእዝ ቃል የመጣ ነው ትርጉሙ መጨመር (መከመር) ማለት ነው፡፡ኦሪታውያን ከመስከረም ፲፭-፳፪ ለስምንት ዕለታት በዓለ መጸለትን ያከብሩ ነበር፡፡(ዘሌ.፳፫፥፮) በዓሉን የሚያከብሩት በብዙ መንገድ ሲሆን፤ እንጨት እየሰበሰቡና እየከመሩ ማታ ማታ በእሳት እያቃጠሉ በመጫወት ያከብሩታል፡፡ ኋላ ግን ተሸሽሎ የእሳት ማንደጃ ቀን በመስከረም ፲፯ ላይ ቆሞአል፡፡
ያም በዓል ከዘመነ ሐዲስ ሲደርስ የመስቀል ደመራ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ ናፍቆትና አክብሮት ከሚያከብራቸው በዓላት አንዱ መስከረም ፲፮ ዕለት (በዋዜማው) የሚከበረዉ የደመራ በዓል ሲሆን በማግስቱ በመላ ኢትዮጵያ ብሔራዊ በዓል ሆኖ ጥንትም ሆነ ዛሬ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው የመስቀል በዓል ነው፡፡  

               የመስቀል በዓል ማክበር መቼ ተጀመረ?
የመስቀል ክብረ በዓል ከክርስትና እምነት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ከቁስጥንጥያ ተነሥታ ድሆች ክርስቲያኖችን ለመርዳትና አብያተ ክርስቲያናትን ለመሥራት በ፫፻፳፮ ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡
ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታች መስቀል ተአምራት እንዳያደርግ አይሁዶች በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ  በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል እስራኤላዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማጸን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ ተመለወሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከተ፡፡ እርሷም በምልክቱ መሰረት ብታስቆፍር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፡፡ የእርሱ መስቀል ለመሆኑ ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበራቱ፣ ጎባጣ በማቅናቱ ታውቋል፡፡ ይኽንንም ይዞ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ሰገደ ጢስ ብሎ በድጓው ጽፎት ይገኛል፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒ አብነት በማድረግ ነው፡፡
በተጨማሪም ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ባገኘች ጊዜ የደስታዋን መልእክት ለልጇ እንዲደርሰው ለማድረግ እንዳሁኑ ዘመን ስልክና ሬድዮ ስላልነበር በዚያን ጊዜ መልእክትን ሩቅ ሥፍራ ለማስተላለፍ ሲፈልጉ በየተራራው ቃፊሮችን (መልእክተኞችን) መድበው መልእክቱን ከሚተላፍበት አቅራቢያ ተራራ ላይ ያለው ቃፊር (መልእክተኛ) ችቦ በማብራት ከርሱ በኋላ ተራራ ላይ ላለው ቃፊር ምልክትን በማሳየት መልእክቱን ያስተላልፋ፤ ሌላኛውም ቃፊር ችቦን እያበራ ሌላኛው ምልክት በማሳየት መልእክቱ መድረስ የሚገባው ቦታ በዚህ መልኩ ያስተላልፋ ነበር፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ይህንን ዘዴ በመጠቀም የመስቀሉ መገኘት ወሬ (የምሥራች ዜና) ቁስጥንጥንያ እንዲደርስ አደረገች ልጇ ቆስጠንጢኖስም መልእክቱ እንደደረሰው ወደ ኢየሪሳሌም ሂዶ እናቱን አግኝቶ ብዙ ስጦታ አበርክቶላታል እርስዋም የቤተክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች የደመራ ማብራት ሥርዓት ከዚህ ሲያያዝ የመጣ ነው፡፡ የበረከት በዓል ያድርግልን፡፡

No comments:

Post a Comment