Monday, February 15, 2016

ተረፈ ካም

ካም ከሦስቱ የኖህ ልጆች ሁለተኛው ነው፡፡ ሴም ታላቅ ወንድሙ ያፌት ደግሞ ታናሹ፡፡ የጥፋት ውሃ ጎድሎ ምድርም ፈጽማ ከደረቀች በኋላ “አኀዘ ኖህ ይትገበራ ለምድር”  ኖህ ምድርን ይኮተኩታት ይቆፍራት ያርማት ጀመር፡፡ የወይን ሐረግም ተከለ፡፡ ከዚያው ከተከለው ወይን ጠጥቶ ሰከረ፡፡ በድንኳኑ ውስጥም ታራቆተ ፡፡


" ወርእዮ ካም አቡሁ ለከነዓን ዕርቃነ አቡሆሙ ሰሐቀ ወወፅአ ወነገሮሙ ለክልኤሆሙ አኃዊሁ በአፍአ" (የከነዓን አባት) ካምም የአባታቸውን ዕርቃን አይቶ ሳቀ፤ ተሳለቀ፡፡ ወደ ውጭ ወጥቶም ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው፡፡ 

"ወነሥኡ ሴም ወያፌት ልብሰ ወወደዩ ላዕለ ዘባናቲሆሙ ወሖሩ ድኅሪተ ወከደኑ ዕርቃነ አቡሆሙ" ያፌትና ሴም ልብስ ወስደው ሁለቱም በትከሻቸው ላይ አደረጉ፡፡ የኋሊት ሄደው የአባታቸውን ዕርቃን ሸፈኑ፡፡ በዓይኖቻቸው የአባታቸውን እራቁትነት ለማየት እንኳን አልደፈሩም፡፡

"ወገፆሙ ድኅሬሆሙ አግብኡ ወኢርእዩ ዕርቃነ አቡሆሙ" ይላል፡፡ ፊታቸውን ወደ ኋላ አዙረው ወጡ፡፡ የአባታቸውን እርቃን አላዩም፡፡

ከዚህ በኋላ የወይን ስካር ፈጽሞ አእምሮ አይነሳምና ኖህ ከስካሩ ነቃ  ታናሹ ልጁ ካም እንደዘበተበት፤ ያፌትና ሴም ልባሳቸውን እንዳለበሱት ባወቀ ጊዜ በታናሹ ልጁ ካም አዘነበት፤

"ርጉመ ለይኩን ከነዓን (ካም) ገብረ ወነባሬ ይኩን ለአኃዊሁ"
ከነዓን (ካም) የተረገመ ይሁን ለወንድሞቹም ተገዥ አገልጋይ ይሁን ብሎ ረገመው፡፡ ሴምና ያፌትን ግን መረቃቸው፡፡ የሴም ፈጣሪ ይመስገን ከነዓንም አገልጋዩ ይሁነው፡፡ እግዚአብሔር የያፌትን ሀገር ያስፋ፡፡ በሴም ቤትም ይደር፡፡ ከነዓንም አገልጋዩ ይሁን ብሎ ደግሞ ደጋግሞ ካምና ትውልዱን ረገመ፡፡ የአባት ርግማን ጽኑዕ ነውና ካምን የወንድሞቹ ባሪያ አደረገው፡፡ እስከ አሁንም ድረስ ነገደ ካም በወንድሞቹ እየተገዛ ይኖራል፡፡

ይህ ታሪክ ለኛ ትምህርት ተግሣፅ ይሆነን ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት ፱፡ ፳-፳፯ ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን አሁንም የካምን ግብር ተከትለው በጸጋ አባት የሆኗቸውን ብፁዓን አበው ላይ የሚሳለቁ ተረፈ ካም በዝተዋል፡፡ ለቤተክርስቲያን ጠበቃ ነን ከኛ በቀር ቅዱስ ከኛ በቀር ክርስትና ላሳር ብለው የሚያስቡ ዝንጉ የቤተክርስቲያን ልጆች (የካም ትራፊ ትርፍራፊዎች) በአባቶች ላይ ይሳለቃሉ፤ ይዘባበታሉ፤ የስድብን ቃል ይናገራሉ፡፡

የመሪዎቹን የአባቶቹን ገበና እኳን መደበቅ የማይችል ልበ ወንፊት አፈ ክፍት ትውልድ፡፡ በውዳሴ ከንቱ እኔ ብቻ ክርስቲያን የኔ ጽዋ ማሕበር ብቻ ቅዱስ እኔ ብቻ አዋቂ እኔ ብቻ የቤተክርስቲያን ጠበቃ ብሎ የሚያስብ ሞኝ ትውልድ፡፡ ስለ እውነት የማህበረ ቅዱሳን ተቆርቋሪ ነን ለማህበሩ ዘብ እንቆማለን ብለው በሚያስቡ ሰዎች ስለ ፓትሪያርካችን የተሰጡትን ያልታረሙ ጋጠወጥ መጣጥፎችን በተመለከትኩ ጊዜ እጅግ አዘንሁ፡፡ ይህንንም እንድጽፍ ተገድጃለሁ፡፡

እውነት አቡነ ማትያስን የስድብ መማሪያ የትችት አፍ መፍቻ አረጋችኋቸው፡፡ ሰላም ለኪ ለማለት አፋቸው ኪስ ውስጥ እንደገባ ኢርፎን የሚቆላለፍ የአብነት ትምህርት ዲዳዎች የኔ ቢጤ መሃይማን አባ ወአቡነ ብለን የተቀበልናቸውን፣ እግዚአብሔር በአንድም በሌላም መንገድ ቅብዓ ሲመቱን ቀብቶ  በቤተክርስቲያን ላይ  የሾማቸውን፣ በመንበሩ ያከበራቸውን አባቶች ለመዝለፍ አንደበታቸው ይከፈታል፡፡ ትችት ለመሰንዘር ምላሳቸው ይቀለጥፋል፡፡ መሪር አፉሆሙ ወምሉዕ መርገመ እንዳለ የአባቶቻቸውን ዕርቃን ለአላፊ አግዳሚ እየጠቆሙ በመረረ አፋቸው የጸጋ ወላጆቻቸውን ይረግማሉ፡፡ ያንጓጥጣሉ፡፡  "እስመ በክብረ አቡሁ ይከብር ሰብእ"  ልጅ በአባቱ ክብር እርሱ ራሱ የሚከብር ሰለሆነ የሚለውን የመጽሐፉን ቃል አያስተውሉምና፡፡ ስለዚህም ዝንጉዎች እንላቸዋለን፡፡

“አክብር አባከ ወእመከ” የምትለዋ ሕገ ኦሪት በእነርሱ ዘንድ አትታወቅም፡፡ ክርስቲያኖች ነን ይላሉ፡፡ ክርስትና ግን አልገባቸውም፡፡ ክርስትና ሴምና ያፌት ናት፡፡ የአባቶቿን እርቃን፤ የልሒቃንን ገመና ተሸሽጋለች፡፡ አደባባይ አውጥታ አትሳለቅበትም፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አንዳንድ ጀሌዋች ክርስትና ግን የካም መንገድ የተዓብዮ ፍኖት ናት፡፡አባቱን የሚያቃልል ትውልድ ትርፉ መርገም ብቻ ነው፡፡ ከሌሎች ወንድሞቹ ስር ባርያ አድርጎ ያኖረዋል፡፡ በካም መንገድ ሂዷልና የካምን መርገም ይቀበላል፡፡

ብጹዓን ጳጳሳት ወሊቃነ ጳጳሳት ሳይደቁኑ ተካን ሳይዳሩ አገባን በሚሉ ዘመነኞች፣ አብነት ጉባዔያትን እንደ ፈረንጅ እየዞሩ ከመጎብኘት በቀር የወንበር ጣዕሙን የማያውቁ የዘመድ ባዳዎች፤ ቅኔ ማኅሌቱ ገደል ቤተመቅደሱ ዋሻ በሆነባቸው የአውደምሕረት ከዋክብት የሰንበት ትምህርት ቤት ጥርቅምቃሚዎች አይዘለፉም፡፡ ነውር ነው! አባቶች ቢስቱ እንኳ እኛ ልጆች ልንጸልይላቸው ነው የሚገባ፡፡ ዕርቃን መሁናቸውን ብናውቅ እንኳ እንደ ሴምና ያፌት ከልብሳችን ልናርዛቸው፣ ኀፍረታቸውን ልንሸፍን እንጂ እንደ ካም ልንዘብትና ለሌሎች አሳልፈን ልንሰጣቸው ፈጽሞ አይገባንም፡፡ የእንርሱ ክበር የኛ ክብር የእነርሱ ውርደት የኛው ውርደት መሆኑን የተገነዘብን አይመስለኝም፡፡

አንዳንዶች “ወልድየ ጹር ርሥአኒሁ ለአቡከ፤ ወኢታሕዝኖ በሕይወቱ፡፡ ወእመኒ ልሕቀ ወኀጥአ ልበ ኦሆ በሎ፡ ወአክብሮ በአምጣነ ትክል  ወኢታስተኣክዮ “ አባትህ ቢያረጅ አእምሮውን ቢያጣ ፈቃዱን ለመፈጸም እሺ በለው፤ ግን እንደሚቻልህ አክብረው፤ ባረጀም ጊዜ አባትህን አትናቀው… የምትለውንውን የሲራክ ምክር አያውቋትም፡፡ አልተማሩትምና፡፡ ቢማሩትም ዓይኖቻቸው በ ዘረኝነት ሻሽ ስለታሰሩ ጆሮቻቸው በጎጠኝነት ጭቃ ስለተመረጉ ሊያስተውሉ አይችሉም፡፡ ወረግዓ ልቦሙ ከመ ሐሊብ እንዳለ ዳዊት  ልባቸው በዘረኝነት ፖለቲካ ረግቷልና አያስተውሉም፡፡ የእነርሱ ትኩረት ሳቅና ስላቅ፤ ጽዋ ማህበራትና ጎጠኝነት እንጂ የቤተክርስቲያን እና ቤተክርስቲያንን የሚመሩ አባቶች አይደሉም፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ ትችት በአቡነ ማትያስ ላይ የሚወርደው  የሰንበት ትምህረትቤት ማደራጃ ስር ያለ ጊዜ ያነሳው ማኅበርን ለመወገን  መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ማኅበሩ በይፋ የፓትርያርኩን ስም ባያጠፋም (ይህን ማድረግ አይችልም፤ ስልጣኑም የለውም አደርጋለሁ ቢልም መዘዙ ብዙ ነው) የማህበሩ አባላት ነን ለማህበሩ እንቆረቆራለን ከሚሉ ጎጠኞች የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በጥቂቱ የማኅበሩን ውሳጣዊ አመለካከት ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ፖለቲካዊ አመለካከት ግላዊ ነው፡፡ ማንም ሰው የፈለገውን የፓለቲካ መስመር መከተል ይችላል፡፡ ፖለቲካዊ ተቃውሞውንም ህገ መንግስቱ በሚፈቅድለት መንገድ መግለጽ ይችላል፡፡ ተደራጅቶ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መታገልም ይችላል፡፡  ሆኖም በሃይማኖት ስም የግል ጥላቻውንና ዘረኝነትን ያማከለ የፖለቲካ ተቃውሞ ማኅበሩላይ ተፈጥጦ  መስበክ ግን  ያስቀጣል፡፡ ማኅበሩም የግል ጥላቻቸውንና የፖለቲካ ጥማቸውን ለማርካት የሚወዱ አስመሳይ ክርስቲያን ነን ባዮችን ሊለይ ይገባዋል፡፡ ሃይማኖት የዘርና የፖለቲካ ዓውድ ሊሆን አይችልም፡፡ በሃይማኖት ካባ ፓለቲካንና ዘረኝነትን ማስፋፋት ወንጀል ነው፡፡ ማኅበሩን ያስጠይቀዋል፡፡ ዘረኝነትን ተንተርሶ የሚጻፉ አባቶችን ከምእመናን ምእመናንን ከአባቶች የሚለዩ ጽሑፎችንም ሊያወግዝ ይገባል፡፡

ያም ሆነ ይህ ቅዱስ ፓትርያርኩ በነገረ ሰሪዎች ምክር ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ ሰው ናቸውና፡፡ ተሳስተው ከሆነም ሊያርሟቸው የሚችሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ስልጣን ያለው ቅዱስ ሰኖዶስ በአጠገባቸው እያለ የኛ የልጆቹ አለ አግባብ አፍ መክፈት ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሲባል ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያለቸው አመለካከት ፈጽሞ የተሳሳተ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማኅበሩ የወጣቶች ስብስብ እንጂ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የቅዱሳን፣ የጻድቃን የፍጹማን ስብስብ አይደልም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ ለቤተክርስቲያን እያደረጉ ያሉት መልካም ስራዎች የሚመሰገኑ ቢሆንም ከእነርሱም ዘንድ ብዙ ስህተት ይኖራል፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን እንደ መልአክ ቤተ ክህነቱን እንደ ሰይጣን አድርጎ መመልከት የተሳሳተ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በቅዱስ ሲኖዶስ እና ቤተ ክህነት ውስጥ ባሉ አበው እንጂ በጽዋ ማኅበራትና ሩጠው ባልጠገቡ ህፃናትና ወጣቶች አይደልም፡፡

ለማንኛውም  እራሳችንን እንመርምር ያለዕውቀት ሳይገባን አባቶችን መዝለፍ የካምን  መርገም ያመጣብናልና እንጠንቀቅ፡፡ አባቶችንም በመዝለፍ አንኩራራ መጽሐፍ “ኢትትመካህ በአስተሐቅሮ አቡከ እስመ ኢይከውነከ ምክሐ አስተሐቅሮ አቡከ” አባትህን መናቅ ማቃለል መመኪያ አይሆንህምና አባትህን በመናቅ አትመካ ሲራ. ፫፡፲፩ ይልብናልና፡፡ በአንጻሩ “ዘያከብር አባሁ ይትፌሣሕ በውሉዱ በዕለተ ጸሎቱ ይሰምኦ”…አባቱን የሚያከብር ልጅ በልጁ ደስ ይለዋል በለመነበትም ቀን ጸሎቱን ፈጣሪው ይሰማዋል  የሚለው የመጽሐፉ ቃል በእኛ ላይ እንዲገለጥ የሴምና የያፌትንም በረከት እንድናገኝ እንትጋ፡፡

እግዚአብሔር የይስጥልን





No comments:

Post a Comment