Wednesday, May 6, 2015

ስለትያትርና ኪነጥበብ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እነዳስተማረው

ከአቤል ተስፋዬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
…እንግዲህ (አብዝታችሁ) ብታነቡ የጌታችን ተከታይ ሆናችኋል፡፡ እርሱም ያነባ (ያለቅስ) ነበርና፤ በአልአዛር (መቃብር ላይ)፤ በከተማይቱ (ኢየሩሳሌምን) ላይ፤ ይሁዳም ባገኘው ጊዜ አብዝቶ አዝኖ ነበር፡፡ ብዙዎች ሲያዝን አይተውታል ነገር ግን ሲስቅም ሆነ ፈገግ ሲል ለቅጽበት ስንኳ በየትኛውም ጊዜ ያየው አንዳችም የለም፤ ከወንጌላውያኑ የትኛቸውም ይህን እንዳደረገ አልገለጹም፡፡ (ቅ.) ጳውሎስንም እንዲሁ፤ እንዳለቀሰ፤ ለሶስት አመታት ቀን ከሌሊት (ያለመቋረጥ) እንዳነባ ራሱም ገልጿል፤ ሌሎችም ስለርሱ ይህን መስክረዋል፤ እንደሳቀ ግን እርሱም የትም ቦታ ላይ አልጠቀሰም ከሌሎች ቅዱሳንም መካከል ይህን እንዳደረገ የተገለጸ ማንም የለም፤ ስለ ሳራ (የአብርሀም ሚስት) (እንደሳቀች) ተጠቅሷል ይኸውም (በሦስቱ መላዕክት) በተገሰጸችበት ወቅት ነበር፤ እንዲሁም የኖኸ ልጅ በተመሳሳይ ስለመሳቁ ተጽፏል፤ ይህን ባደረገበት ወቅት ግን (በአባቱ ተረግሟልና) ነጻነቱን በባርነት ለወጠ፡፡

እንዲህ የምላችሁ ሳቅ (ጨዋታ) የተባለን ሁሉ ለመኮነን አይደለም፤ አእምሯችሁ በከንቱነት እንዳይጠመድ ለማቀብ ነው እንጂ፤ እስኪ ልጠይቃችሁ በምቾት የምትንደላቀቁና በከንቱነት የተዘፈቃችሁ ሆናችሁ ሳለ በሚያስፈራው (የጌታችን) የፍርድ መንበር ፊት ቆማችሁ እዚህ (በምድር) ላይ ሳላችሁ ስለሰራችሁት ነገር አንድ በአንድ አትጠየቁምን? በእርግጥ እንጂ… ምክንያቱም አውቀን በድፍረት ስለሰራነውም ሆነ ከአቅማችን በላይ ሆኖብን ስለበደልነው በደል ምላሽ እንድንሰጥ እንጠየቃለንና… ‹‹ በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ (በሰማዩ) አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ይላልና ጌታ፡፡ አለጥርጥር ማናችንም ጌታን ወደን አንክደውምና አውቀንና ፈቅደን አናደርገውም፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን ከቅጣት አያድነንምና ይህንንም አስመልክቶ መልስ መስጠት ይኖርብናል፤ አውቀን ስለሰራነው ብቻ ሳይሆን ሳናውቅ የበደልነውም ጭምር ያስጠይቀናል፡፡ ‹‹ በራሴ አንዳች አላውቅም፤ ነገር ግን ይህ ምክንያት ሆኖኝ ከፍርድ አላመልጥም (አልድንም)›› ይላልና 1 ቆሮ 4፡4 ፤ደግሞም በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል ‹‹ ለእግዚአብሔር ቀናኢነት ያላቸው ናቸውና ይህን ቆጥሬላቸዋለሁ፤ ነገር ግን በእውቀት አይደለም›› ይሁን እንጂ ይህ በቂ ምክንያት ሆኖ አልተገኘም፡፡ ወደ ቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈበት ወቅትም ደግሞ (ሐዋ. ቅ. ጳውሎስ) እንዲህ ብሏል ‹‹ እባቡ ሔዋንን በረቂቅ ተንኮሉ እንዳሳታት ሁሉ በጌታችን ካለ ቅንነት አእምሯችሁን እንዳይበርዘው እፈራለሁ››


የምትጠየቁበት ነገር እጅግ ብዙ ሆኖ ሳለ ታዲያ እየሳቃችሁና ከንቱ ብልጣብልጥነት እየተናገራችሁ እንዲሁም ለድሎት ራሳችሁን እየሰጣችሁ ትቀመጣላችሁን? ‹‹ ይህን ማድረግ ትቼ ባዝንና ብተክዝ ምን ዋጋ አለው?›› የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እጅግ ክፍተኛ ዋጋ አለው እንጂ! ያለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ዋጋውን በቃላት መግለጽ ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም በምድራዊ ችሎት ፊት ልቅሷችሁ ምን ቢበዛ ከተፈረደባችሁ በኋላ ከቅጣታችሁ ልታመልጡ አትችሉም፤ ነገር ግን (በሰማያዊው ችሎት) በተቃራኒው ጥቂት ብትቆረቆሩ (ብታዝኑ) ፍርዳችሁ ተፍቆ ይቅርታን ታገኛላችሁ፡፡ ስለሆነም ክርስቶስ እንድናዝን (እንድንጸጸት) አብዝቶ ይሞግተናል፤ በሚስቁት (በሚያላግጡት) ላይ ግን ይፈርድባቸዋል፤ ይህ ( አለም) የሳቅ (ኮሜዲ) ቲያትር አይደለምና፤ የመጣነውም ለከት አልባ በሆነ ሁኔታ ልንስቅና ልንዝናና አይደለም፤ (በሐዘን) ልናቃስት እናም በሮሮ ብዛት (ሰማያዊውን) መንግስት እንድንወርስ ነው እንጂ፡፡ በንጉስ ፊት በምትቆምበት ጊዜ ጥቂት ፈገግታ ለቅጽበት ስንኳ በፊትህ ላይ እንዲታይ አትፈቅድም፤ ግን (ይህ ከሆነ) ታድያ የመላእክት ጌታ በአንተ ዘንድ አድሮብህ ሳለ በመራድና መንቀጥቀጥ እንዲሁም ራስህን በመግራት አደግድገህ ከመቆም ይልቅ በአንተ እንዳዘነብህ እያወቅህ ትስቃለህን? በበደልህ ካሳዘንከው ይልቅ ይህን በማድረግህ ይበልጥ እንደምታስቆጣው አታስተውልምን? እግዚአብሔር ከበደለኞች ፊቱን አይመልስምና፤ ነገር ግን በሐጢአታቸው የማይደነግጡትን (ይተዋቸዋል) ፡፡

በከንቱ ሀሳብ ከመጠመዳቸው የተነሳ ይህን ሁሉ ከተባሉ በኋላ እንኳ ‹እግዚአብሔር ከለቅሶስ በየትኛውም ጊዜ  ይሰውረኝ፣ በዘመኔ እንድስቅና እንድጫወት ያድለኝ እንጂ› የሚሉ አንዳንዶች አሉ፡፡ እንዲህ ካለው አእምሮ ይልቅ የጨቅላ አስተሳሰብ ሊባል የሚችል ሌላ ምን አለ? ምክንያቱም
እንድንጫወት የሚያበረታታን እግዚአብሔር አይደለም፤ ሰይጣን እንጂ፡፡ ሲጫወቱ የነበሩት እነማን እንደሆኑ እነሆ አድምጡ፤ እንዲህ ተብሏልና ‹ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ሊጫወቱም ተነሱ› በሰዶም የነበሩት እንዲህ ነበሩ፤ በጥፋት ውሃ ዘመን የነበሩት (ሰዎች) እንዲህ ነበሩ፡፡ ደግሞም በሰዶም ስለነበሩ ሰዎች እንዲህ ተብሏልና፤ ‹በመታበይ፣ በጥጋብና በዳቦ ምላትም ሆነው በዝሙት ፍትወት ተቃጠሉ›፡፡ በኖህ ዘመን የነበሩትም (ኖህ) መርከቡን ሲያበጅ ለብዙ ዘመናት እየተመለከቱት (እንኳ) ሊመጣ ያለውን (ጥፋት) ሳያስተውሉ በከንቱ ፌሽታ (ጭፈራ) ሆነው ኖሩ፡፡ ስለዚህም ምክንያት ደግሞ ማየ ዓይህ መጥቶ ጠራርጎ ወሰዳቸው፤ በቅጽበትም አለምን ሊያጠፋት በቃ፡፡

ስለዚህም ከዲያቢሎስ የምታገኟቸውን ነገሮች ከእግዚአብሔር አትጠይቁ፡፡ እግዚአብሔር የሚሰጠው የተጸጸተና የተሰበረ፣ የነቃና የደነገጠ ንስሐንና ወቀሳንም የተመላ ልብ ነው፡፡ እኒህ የእርሱ ስጦታዎች ናቸው፤ ደግሞም ለእኛ እጅጉን የሚያስፈልጉን እነርሱ ናቸው፡፡ አዎን! ብርቱ ጦርነት በእኛ ዘንድ ነው፤ ፍልሚያችን ከ‹‹ረቂቃን ኃይላት›› ጋር፣ ግድድራችንም ከአመጸኞች መናፍስት ጋር፤  ውጊያችን ደግሞ  ‹‹ከሥልጣናትና ከኃይላት ጋር›› ነውና፤ በማስተዋል፣ በሙሉ ንቃትና በዝግጁነት ሆነን ብንገኝ ይህን አውሬያዊ ሌጊዮን ለመቋቋም ያስችለናልና ለኛ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በማሽካካትና በቧልት ብንጸመድ ሁሌም ነገሮችን ንቀንና አቃለን እያየን (ብንቀመጥ) ፍልሚያው ገና ሳይጀመር በገዛ ስንፍናችን ፈጽመን እንሸነፋለን፡፡

አለማቋረጥ በመሳቅ ስጋችንን በማስደሰትና በድሎት መኖር ለኛ አይገባም፤ ይህ ግብር በየመድረኮች የሚታዩቱ፣ የአመንዝራ ሴቶች፣ ለዚህ ድርጊት (ራሳቸውን) የጸረቡት፤ ደም መጣጮችና ሸንጋዮች ይህ የነርሱ ግብር ነው፤ ለገነት የተጠሩት (ግብር) አይደለም፤ በሰማያት ወዳለችው ከተማ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው አይደለም፤ መንፈሳዊ እቃ ጦር የታጠቁት አይደለም፤ በዲያቢሎስ ወገን ራሳቸውን ያሰለፉት ነው እንጂ፡፡ እርሱ (ዲያቢሎስ) ነውና (ይህን ያደረገው)፤ አዎን በርግጥም የክርስቶስን ወታደሮች ያዳክም ዘንድ፣ የቀደመ ጥብአታቸውንም ይፈታ ዘንድ ይህን (ድርጊት) ጥበብ (አርት) እንዲሆን ያደረገው እርሱ ነውና፡፡ ለዚህ ዓላማው ሲል በከተሞች የቲያትር ቤቶችን ሰራ፣ እነዚህን አለሌዎችም (ዘፋኞችንና ተውኔተኞችን) አሰልጥኖ ሲያበቃ እነርሱ በሚያደርሱት እኩይ ተጽእኖ በመላው ከተማ እንደዚያ ያለ (የርኩሰት) ወረርሺኝ እንዲሰፍን፤ ቅ/ጳውሎስ እንድንሸሻቸው ያዘዘንን እነዚያኑ ነገሮች - ‹‹ከንቱ ንግግርና ቧልት ››- እንድንከተል (በዚህ መንገድ) ይገፋፋናል፡፡ ከዚህም በላይ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው የሚሳቅበት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚያ ባእድ የሆኑትን ድርጊቶች የሚተውኑት ተውኔተኞች የጽርፈትና የርኩሰት ንግግር ከአንደበታቸው በሚወጣበት ወቅት ከንቱነት ከተጠናወታቸው መካከል በርካቶች ይስቃሉ፣ ደስም ይላቸዋል፤ ሊወግሯቸው ሲገባም ያጨበጭቡላቸዋል፤ በመሳቃቸው ምክንያትም የጥፋት እሳትን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፡፡ ምክንያቱም የክፋት ንግግር ለሚናገሩ ሙገሳን የሚሰጡ (ሰዎች) እነዚህ ናቸው ከሁሉ ይልቅ ሰዎቹ ክፋትን እንዲናገሩ ምክንያት የሚሆኑት፤ ስለሆነም ለዚህ የተዘጋጀው ቅጣትና ፍርድ (ከተናጋሪዎቹ ይልቅ በአጨብጫቢዎቹ ላይ ይበልጡኑ) ሊበየንባቸው ይገባል፡፡ እኒህን (ርኩሰቶች) የሚያይ ተመልካች ባይኖር ኖሮ (ተውኔቱን) የሚተውንም ባልኖረ ነበርና፤ ነገር ግን ስራችሁን፣ መደብራችሁን፣ ገንዘባችሁን፣ ባጭሩ ያላችሁን ሁሉ ሰውታችሁ (እዚያ ለመገኘት) ስትቻኮሉ ሲመለከቱ፤ ይህን ድርጊት ለመፈጸም ከፍ ያለ ተነሳሽነት ይኖራቸዋል፤ በብርቱ ትጋትም (ተውኔቱን) ለማከናወን ይባትላሉ፡፡

ይህንን ያልኩት (ተዋንያኑን) ከወቀሳ ነጻ ላወጣቸው አይደለም፤ ለዚህ ስርአት አልበኝነት በዋነኝነት ምክንያትና ስር እየሆናችሁ ያላችሁት እናንተ እንደሆናችሁ ትረዱ ዘንድ ነው እንጂ፤ እለቱን ሙሉ በነዚህ ነገሮች ተጠምዳችሁ ጊዜያችሁን የምታጠፉ እናንተ፣ በትዳር ውስጥ በክብር የተጠበቁትን ነገሮች በማራከስ የምታራቁቱ፤ ታላቁን የተክሊል ምስጢር በአደባባይ ማላገጫ እንዲሆን የምታደርጉ (እናንተ ናችሁና)፡፡ እኒህን (ጸያፍ) ድርጊቶች የሚተውነው የናንተን ያህል ጥፋተኛ አይሆንም፤ በነዚህ ነገሮች እንዲቀልድ የምትገፋፉት እናንተ ናችሁና፤ እንዲያውም መገፋፋት ብቻ አይደለም ደግሞም በሁኔታው በመደሰትና በመሳቅ፣ የቀረበውንም ድርጊት በማሞካሸት፣ እነዚህ የዲያቢሎስ መደብሮች እንዲጠናከሩ በከፍተኛ ተነሳሽነት ትንቀሳቀሳላችሁ፡፡
እንግዲያው እስኪ ንገሩኝ? በዚያ (በቤተ-ተውኔት) ስትሰደብ (ስትነወር) ስታዩ (ቆይታችሁ) በምን አይናችሁ እቤት ያለች ስታችሁን ታይዋታላችሁ? ተፈጥሮ ራሷ እንዲህ በአደባባይ ስትነወር (ስትመለከቱ) እቤት ያለችውን (የህይወታችሁን) አጋር አስባችሁ እንዴት ልታፍሩ (ልትሸማቀቁ) አልቻላችሁም? የተፈጸመው ትወና (acting) እኮ ነው ደግሞ እንድትሉኝ አልወድም!፤ ይኸው ‹ትወና› ብዙዎችን ዘማውያን አድርጓልና፤ የብዙ ቤተሰቦችን ኑሮ አፍርሷልና፡፡

 እንዲህ እጅግ የከፋ የዝሙት ድርጊት (ተውኔቱ) ሲቀርብ (ርኩሰትነቱ ታውቆ) እንደሐጢአት ከመቆጠር ይልቅ በፉጨትና በጭብጨባ እንዲሁም በከፍተኛ ሳቅ የሚታጀብ በመሆኑ… ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ አብዝቼ አዝናለሁ፡፡ ምንን ትላላችሁ?! የሚደረገው ትወና ነውን? ሁሉም ህግጋት ሰዎች እንዲሸሹዋቸው የሚያዟቸውን እነዚህን ድርጊቶች አስመስለው ለመተወን ሲሉ በብርቱ ደክመዋልና ስለዚሁ ምክንያት (እኒህ ሰዎች) አስር ሺህ ሞት ይገባቸዋል፡፡ ድግጊቱ መጥፎ ከሆነ ይህንኑ ማስመሰልም ደግሞ መጥፎ ነውና፡፡ እኒህን የዝሙት ትዕይንቶች የሚተውኑ ግለሰቦች ምን ያህል ዘማውያንን በተውኔታቸው እንደሚያፈሩ፤ ታዳሚዎቻቸውን እንዴት በድርጊታቸው ደፋርና ፈሪሀ-እግዚአብሔርን የማያውቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርጓቸው… ገና ወደዚህ (ጉዳይ) አልደረስኩም፤ እንዲህ አይነት (አስነዋሪ) ድርጊቶችን ተቋቁማ ከምትመለከት አይን የባሰ አመንዝራነትንና ድፍረትን የተሞላ ነገር የለምና፡፡

አንተ ሴት ልጅ በገበያ… ኧረ እንደው በቤት ውስጥ እንኳ ልብሷን ተገፋ እርቃኗን እንድታያት አትወድም፤ ከባድ ድፍረት ነው ብለህ ትቆጣለህ እንጂ፡፡ ነገር ግን (መልሰህ) የወንዶችና የሴቶች ተፈጥሮ ላይ ልታላግጥ፣ አይንህንም ልታረክስ ወደቲያትር ትሄዳለህን? ‹ልብሷን የተገፈፈችው (እኮ) አመንዝራ ነች› በማለት (ምክንያት ልትደረድር) አይገባም፤ የአመንዝራይቷም ሆነ የነጻይቱ ሴት የተፈጥሯቸው ባሕርይ አንድ ነው፤ አካላቸውም አንድ ነው፡፡ ይህ ስህተት ካልሆነ ታዲያ ይኸው ድርጊት በገበያ ሲፈጸም ብትመለከት ራስህን ከዚያ ለማራቅና ነውሩን የፈጸመችውንም ሴት ልታርማት የምትፋጠንበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ወይስ ብቻችንን ስንሆን ድርጊቱ ነውር የሚሆን፣ አንድ ላይ ተሰባስበን ስንቀመጥ ደግሞ በዚያው ልክ የማያስነውር ይሆናልን? ፈጽሞ! ይህ በርግጥም ነውርና ውርደት እንዲሁም ፍጹም እብደት ነው፤ እንዲህ አይነት በደል ሲፈጸም ታዳሚ ከመሆን ይልቅ አይንን በጭቃና በረግረግ መቀባት ይሻላል፡፡ ሴት ልጅ እርቃኗን ሆና ከማየትና ዝሙት የተመላ ትእይንት ከመመልከት የበለጠ ጭቃው አይንን ፍጽሞ ሊጎዳ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ሲጀመር እርቃን መሆን የመጣበት ምክንያት ምን እንደሆነ አድምጥ፤ ይህ ውርደት የተከሰተበትን መንስኤ አንብበህ (ተረዳ)፡፡ በውኑ እርቃን መሆን እንዴት ሊከሰት ቻለ? የኛ መተላለፍ (መሳት)ና የዲያቢሎስ ምክር (ውጤት) ነው፡፡ እናም ከመነሻው ስንኳ አንስቶ ይህ የርሱ (የዲያቢሎስ) ሸር ውጤት ነው፡፡ ቢያንስ ግን (አዳምና ሔዋን) እርቃናቸውን በሆኑ ወቅት አፍረው ነበር፤ አንተ ግን በዚያ ትኮራለህ፤ ሐዋርያው እንዳለው ‹ክብርህ በርኩሰትህ ሆኗል›፡፡

በዚህ የክፋት ስራ ቆይተህ (ቤትህ) ስትመለስ ታዲያ ሚስትህ ከዚያ አንስቶ እንዴት ታይሃለች?  በአደባባይ የሴትነትን ተፈጥሮ እንዲህ አዋርደህ በአየኸውም ነገር የአመንዝራዎች ምርኮኛና ባርያ ሆነህ ስታበቃ በምን ሁኔታ ትቀበልሃለች? እንዴትስ ታናግርሃለች?

እኒህን ነገሮች በሰማህ ጊዜ ያዘንክ ከሆነ ላመሰግንህ እወዳለሁ፤ ‹‹ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? በእኔ ምክንያት ያዘነ ነው እንጂ›› (ይላልና)፡፡ ስለሆነም በድርጊቶችህ ማፈርና መጸጸትን አታቁም፤ እንዲህ ካሉ ነገሮች የሚመጣው ጥልቅ ሐዘን ላንተ ወደ መልካም ለመለወጥ መነሻ ይሆንሀልና፡፡ ለዚህ ምክንያት ስል፤ ጠለቅ አድርጌ በመብጣት እነርሱ ካሰከሩህ (የርኩሰት) መርዝ ነጻ አወጣህ ዘንድ እንዲቻለኝ፣ የተግሳጼን ቃላት ጠንካራ አድርጌያቸዋለሁ፤ ወደንጹሁ የነፍስ ጤንነት እመልስህ ይቻለኝ ዘንድ፤ እግዚአብሔር እንደፈቀደ ሁላችንም በተቻለን መጠን ከእርሱ በመቋደስ ለመልካም ምግባራት የተዘጋጁትን ሽልማቶች መቀዳጀት እንችል ዘንድ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ፍቅር፤ ክብር ወእዘዝ ለዓለመ ዓለም አሜን፡፡


ወስብሐት እግዚአብሔር!
ምንጭ፡- የማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜቅ/ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ ማቴዎስ 2፤1-2 ፤ ገጽ 64-67 ፤ Christian Classics Ethereal Library፤ New York: Christian Literature Publishing Co., 1886