Monday, January 18, 2016




                         እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
 

                                    ገሃድ/ ጾመ ድራረ ጥምቀት

    
ገሃድ የቃሉ ትርጉም መገለጥ መታየት ነው፡፡ በጥምቀት መገለጥ መባሉ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ 30 ዓመት እድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲህ ሰው የሆነበት፣ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኃላ 30 ዓመት እድሜው በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ አብ በደመና ሆኖ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› በማለቱ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ይሰቀላል ይሞታል ይነሳል ብለው የተናገሩለት መሲሕ እርሱ መሆኑ ተገልጦአልና እንዲሁም ሦስቱ አካላት በአንድ ጊዜ ታይተዋልና ምስጢረ ሥላሴ የተገለጠለት በመሆኑ ገሃድ ይባላል፡፡(ማቴ 313-17)
ይህን በማሰብ የምንጾመው ጾምየገሃድ ጾምይባላል፡፡ ቀኑም ጥር 10 ቀን 11 አጥቢያ ነው፡፡ስለዚህ ጥር 10 ቀን ሰባቱ አጽዋማ አንዱ የሆነው የገሀድ ጾም ነው ማለት ነው!



አንድም ይህ ጾም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት በማሰብ
የጥምቀትን ዋዜማ መጾም ነው፡፡ ይህም ማለት በጥምቀት
ዋዜማ ከምግብ መከልከል ነው፡፡ የሚቆርብ ሰው አክፍሎ
የሚያድር ስለሆነም የጥምቀትን ድራር መጾም ነው፡፡ ሐዋርያት
«ልደት ጥምቀት ዓርብ ረቡዕ ቢውል በሌሊት ቀድሰው ሥጋውን
ደሙን ይቀበሉ፤ ከሌሊቱ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጹሙ ብለው
አይፍረዱ» ብለዋል /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15/፡፡ የልደትና
የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዓርብ ቀን ቢሆን በበዓለ ሃምሳ
የሚበላውን የጥሉላት ምግብ በጠዋት በመብላት ምእመናን
በዓሉን እንዲያከብሩ ታዟል፡፡
ይህም እነዚህ ሁለቱ ታላላቅ የእግዚአብሔር በዓላት በመሆናቸው
ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በረቡዕና በዓርብ በሚውልበት ጊዜ
በረቡዕና በዓርብ ፈንታ ማክሰኞንና ሐሙስን በመጾማችን ሁለት
ሥራ ይፈጸምልናል፡፡ በዚህም የጾምና የበዓል ማክበር ሥራ
ይከናወናል፡፡ የጥምቀትን ዋዜማ ጥሉላት መባልዕትን መተው
ነው፡፡ ይህንንም እንደ ዘይቤው ገሀድ ይለዋል፣ መገለጫ፣
ግልጥ፣ ይፋ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ጋድ ይለዋል፣
ለውጥ፣ ልዋጭ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ረቡዕ ዓርብ ሲውል በዚያ
ለውጥ ማክሰኞ ሐሙስ ይጾማልና ጋድ አለው፡፡ እንዲሁም አንድ
ጊዜ ሲጾም አንድ ጊዜ ሲቀር እንዳይረሳና ቅዳሜ ወይም እሑድ
በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ አይቻልም፣ ነገር ግን እህል ውኃ እንጂ
ጥሉላት ከመብላት መጠበቅ ይገባል፡፡

                         ከተራ ምንድን ነው?
   ከተራ ከበበ ካለው የግእዝ ግሥ የወጣ ነው፡፡ ፍችው ውኃ መከተር፣ መገደብ ማለት ነው፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል፡፡ ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል፡፡ የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሄድ ይገደባል፡፡
በበዓለ ጥምቀት የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በዋዜማው የመኼዱ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱ የጌታችን፣ምሳሌ ሲኾን ካህናቱ የመጥምቁ ዮሐንስ ምሳሌ ሲኾን መዘምራኑና ሕዝቡ ደግሞ ዮሐንስ ያጠመቃቸው ሕዝቦች ምሳሌዎች ናቸው፡፡
በባሕረ ጥምቀቱ ላይ በሚንሳፈፍ ነገር መብራት መደረጉ በርግብ አምሳል ለወረደው መንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡
"የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት። " ኢያሱ 3:3


No comments:

Post a Comment