ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም: ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ሰምቶ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ አስፈልገህ ላክልኝ ብሎ ላከበት። ንጉሥ ድርጣድስ ደናግሉ ከተሰወሩበት አስፈልጎ አገኛት። እሱም የቅድስት አርሴማን መልከ ቀናነቷን አይቶ ይህችንስ አሳልፌ አልሰጥም ብሎ መሪያቸው አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት። እሷም አይሆንም ያልሁ እንደሁ ጸብ አጸናለሁ ብላ እሺ አለችው እሷን ግን ለመንግሥተ ሰማያት የታጨሽ ነሽና ይህ ዕልው እንዳያረክስሽ እወቂ ብላ ልቧን አስጨከነቻት። ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ ድንግል አርሴማን ያዛት። ኃይል መንፈሳዊ ተሰጥቷታልና ጎትታ ከመሬት ቀላቀለችው። እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለነበር በታናሽ ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ:: ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት:: ከዚህ በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው (እመምኔት) አጋታ ጋር በሰይፍ አስመትቷቸዋል። ሥጋቸውም በተራራ ጫፍ ላይ እንዲጣል ተደረገ:: ይህም የሆነው በመስከረም 29 ነው::
ሰማዕታት ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት: መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ:: ወዳጆቹም በዳነልን እያሉ ሲጨነቁ የታዘዘ መልአክ መጥቶ እኅቱን ከጎርጎርዮስ በቀር የሚያድነው የለም አላት። ንጉሥ ድርጣድስ የአርማንያውን ሊቀጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስን በሃይማኖት ምክንያት ተጣልቶ ከአዘቅት ጉድጓድ ውስጥ አስጥሎት ነበርና የሞተ መስሏቸው ደነገጡ። እርሱ ግን መልአኩ ለአንዲት መበለት ነግሮለት ምግቡን እየጣለችለት ይኖር ነበርና ምናልባት አምላኩ ጠብቆት ይሆናል ብለው ገመድ ቢጥሉ መኖሩን ለማሳወቅ ገመዱን ወዘወዘው። ቢጎትቱት በ15ዓመቱ ከሰል መስሎ ወጥቷል። የንጉሡ እኀት ወንድሜን አድንልኝ አለችው። ቅዱስ መጀመሪያ አጽመ ሰማዕታትን አሳዩኝ ብሎ አሳይታው ያን አስቀብሮ ካለበት ሄዶ ባድንህ በፈጣሪዬ ታምናለህን? አለው። ግዕዛኑን ፈጽሞ አልነሳውም ነበርና በአዎንታ ላሱን ነቀነቀ። የተደረገለትን እንዳይዘነጋ ከእጁ ከእግሩ የእርያ ምልክት ትቶ ጸልዮ አድኖታል። አመንኩ አጥምቀኝ አለው ለማጥመቅስ ሥልጣን የለኝም አለው። በአንጾኪያው ሊቀጳጳስ ተጠመቀ። እሱንም ሊቀጳጳስነት አሹሞት ብዙ ተግሳጻት ጽፎ ብዙ ድርሳናትን ደርሶ ብዙ የቱሩፋትን ሥራ ሠርቶ አርፏል። ዕረፍቱ ታሕሣስ 15 ቀን ነው።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን: እኛንም በእናታችን በቅድስት አርሴማ አማላጅነት በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን: በረከታቸውም ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ::
No comments:
Post a Comment