Saturday, February 21, 2015

ሁለተኛ ሳምንት - ቅድስት



የካቲት ፲፬ ፳፻፯ ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓትና በትውፊት የበለፀገች መሆኗ የታመነ ነው፡፡ ሰፊ ሥርዓትና ትውፊት ያላት እንደመሆኗ መጠን የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትጾመው ጾም፤ የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትቆመው ማኅሌት በቂ ታሪክ፣ ትውፊትና ሥርዓት አለው፡፡ ያለታሪክ ያለትውፊትና ሥርዓት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትጾመው ጾም፤ የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትዘምረውም መዝሙር የለም፡፡


በዚህ በያዝነው ወቅት የምንጾመው ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም እንደመሆኑ መጠን በዚሁ የጾም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዘመነ ሥጋዌው ለሠራቸው የተአምራትና የትምህርት ሥራዎች መታሰቢያ በዓል በማድረግ ለእያንዳንዱ ሰንበት ስም በመስጠት በስሙ አንፃር የበዓሉን ታሪክ በመከተል ታመሰግናለች፤ ትዘምራለች፤ ትፀልያለች፤ ትቀድሳለች፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዓቢይ ጾም ውስጥ  ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ሰርቶላቸዋል፡፡ በመዝሙራቱ ውስጣዊ ምስጢር መሠረትም እያንዳንዱ እሑድ ስያሜ ተሰጥቶቸል፡፡ በዚሁም መሠረት ያሳለፍነውን ሳምንት ከቅበላው ዋዜማ ጀምሮ ዘወረደ ብለን በቤተ ክርስቲያናችን አክብረናል፡፡ በቀደመው ጽሑፋችንም የስያሜውን ትርጓሜ አይተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ እንደእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ የቀጣዩን ሰንበት/ሳምንት (የሁለተኛውን ሳምንት) ስያሜና ምሥጢሩን እንማማራለን፡፡ 


Friday, February 20, 2015

ቅድስት አርሴማ ሰማዕት ዘአርማንያ


የቅድስት አርሴማ ወላጆች አባቷ ቴዎድሮስ እናቷ አትናትያስ ይባላሉ:: በፈሪሃ እግዚአብሔር  በአምልኮ ጸንተው በሕጉ ተመርተው የኖሩ ደጋግ ሰዎች ናቸው:: ልጅ አጥተው መካን ሆነው ሲኖሩ ዘር እንዲሰጣቸው ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር:: እግዚአብሔርም  ጸሎታቸውን ሰምቶ ደም ግባቷ ያማረ መልከ መልካም የሆነች እንደ ጸሐይ የምታበራ ልጅ ሰጣቸው:: ቅድስት አርሴማ የነበረችበት ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ይባላል:: ዲዮቅልጥያኖስ የሮም ቄሳር ሆኖ የነገሰበት (እኤአ ከ284ዓ/ም - 305 ዓ/ም) : አብያተ ክርስቲያናት የተዘጉበትና አብያተ ጣኦታት ተከፍተው ክርስቲያኖች በክርስቶስ ስም ልዩ ልዩ መከራና ሰማዕትነት የሚቀበሉበት ዘመን ነበር::  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤  ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤  በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ” እንዳለ  ዕብ  11:35-37ከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ መልኳ ውብ የሆነ ብላቴና ድንግል ሊያገባ ፈልጎ ሔደው መርጠው ያመጡለት ዘንድ ሠራዊቱን በየሀገሩ ሰደደ። ይህች ቅድስት አርሴማ በሮሜ ሀገር በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ከሌሎች ማኅበረ ደናግል ጋር ነበረች:: እየፈለጉ ሲሄዱ እሷን አይተው ሥዕሏን ሥለው ወስደው ሰጡት። መልካም ብላቴና አግኝታችሁልኛል ሄዳችሁ አምጡልኝ አላቸው። እርሷም በመንፈስ አውቃ እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ እንጂ ከአረማውያን ጋር አንድነት የለኝም ብላ ከ39 ደናግል ጋር ወደ አርማንያ ተሰደደች::

ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ የከበረች አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም: ግን በአርማንያ አገር እንዳለች ሰምቶ ለአርማንያ ንጉሥ ለድርጣድስ አስፈልገህ ላክልኝ ብሎ ላከበት። ንጉሥ ድርጣድስ ደናግሉ ከተሰወሩበት አስፈልጎ አገኛት። እሱም  የቅድስት አርሴማን መልከ ቀናነቷን አይቶ ይህችንስ አሳልፌ አልሰጥም ብሎ መሪያቸው አጋታን አባብላ እሺ ታሰኝለት ዘንድ አዘዛት። እሷም አይሆንም ያልሁ እንደሁ ጸብ አጸናለሁ ብላ እሺ አለችው እሷን ግን ለመንግሥተ ሰማያት የታጨሽ ነሽና ይህ ዕልው እንዳያረክስሽ እወቂ ብላ ልቧን አስጨከነቻት። ንጉሡም ይዞ ወደ እልፍኙ ሊአስገባት ከአደባባይ መካከል ተነሥቶ  ድንግል አርሴማን ያዛት። ኃይል መንፈሳዊ ተሰጥቷታልና ጎትታ ከመሬት ቀላቀለችው። እርሱ ግን በጦርነት እጅግ የጸና አርበኛ ስለነበር በታናሽ ብላቴና ስለተሸነፈ ያን ጊዜ አፈረ::  ራሷንም በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና ቆረጧት:: ከዚህ በኋላ ደናግሉን ሁሉ ከእናታቸው (እመምኔት) አጋታ ጋር በሰይፍ አስመትቷቸዋል። ሥጋቸውም በተራራ ጫፍ ላይ እንዲጣል ተደረገ:: ይህም የሆነው በመስከረም 29 ነው::
ሰማዕታት ከተገደሉ በኋላ በንጉሡ ላይ ጋኔን ተጫነበት: መልኩም ተለውጦ እንደ እርያ ሆነ:: ወዳጆቹም በዳነልን እያሉ ሲጨነቁ የታዘዘ መልአክ መጥቶ እኅቱን ከጎርጎርዮስ በቀር የሚያድነው የለም አላት። ንጉሥ ድርጣድስ የአርማንያውን ሊቀጳጳስ ቅዱስ ጎርጎርዮስን በሃይማኖት ምክንያት ተጣልቶ ከአዘቅት ጉድጓድ ውስጥ አስጥሎት ነበርና የሞተ መስሏቸው ደነገጡ። እርሱ ግን መልአኩ ለአንዲት መበለት ነግሮለት ምግቡን እየጣለችለት ይኖር ነበርና ምናልባት አምላኩ ጠብቆት ይሆናል ብለው ገመድ ቢጥሉ መኖሩን ለማሳወቅ ገመዱን ወዘወዘው። ቢጎትቱት በ15ዓመቱ ከሰል መስሎ ወጥቷል። የንጉሡ እኀት ወንድሜን አድንልኝ አለችው። ቅዱስ መጀመሪያ አጽመ ሰማዕታትን አሳዩኝ ብሎ አሳይታው ያን አስቀብሮ ካለበት ሄዶ ባድንህ በፈጣሪዬ ታምናለህን? አለው። ግዕዛኑን ፈጽሞ አልነሳውም ነበርና በአዎንታ ላሱን ነቀነቀ። የተደረገለትን እንዳይዘነጋ ከእጁ ከእግሩ የእርያ ምልክት ትቶ ጸልዮ አድኖታል። አመንኩ አጥምቀኝ አለው ለማጥመቅስ ሥልጣን የለኝም አለው። በአንጾኪያው ሊቀጳጳስ ተጠመቀ። እሱንም ሊቀጳጳስነት አሹሞት ብዙ ተግሳጻት ጽፎ ብዙ ድርሳናትን ደርሶ ብዙ የቱሩፋትን ሥራ ሠርቶ አርፏል። ዕረፍቱ ታሕሣስ 15 ቀን ነው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን: እኛንም በእናታችን በቅድስት አርሴማ አማላጅነት በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን: በረከታቸውም ከሁላችን ጋር ይሁን አሜን ::

Tuesday, February 17, 2015

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሱዳን ካርቱም ያደረጉትን ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ተመለሱ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሱዳን ከምትገኘው የኢትዮጵያ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቷ ልዑካንና ሊቃነ ጳጳሳትን አስከትለው በሱዳን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የተገነቡ የሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያና የከፍተኛ ኪሊኒክ ሕንፃዎች መርቀው ሥራ ለማስጀመርና ወደፊት ለሚሠሩት ሁለት ታላላቅ ህንፃዎች የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሱዳን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዘምራንና ምእመናን በከፍተኛ የአቀባበል ሥርዓት ተቀብለዋቸዋል፡፡

Sunday, February 15, 2015

ዐቢይ ፆም እና የዐቢይ ፆም ሳምንታት ስያሜ /ክፍል አንድ/






ከቃሉ ስንነሳ ‹‹ዐቢይ ፆም›› ማለት ዋና ፆም፣ የአፅዋማት ሁሉ የበላይ ፆም ማለት ነው፡፡ ይህንንም ስያሜውን ያገኘው ራሱ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፵(አርባ) መዓልት ፵(አርባ) ሌሊት የፆመውን ፆም በማሰብ የሚጾም ስለሆነ ነው(ማቴ ፬፥፩)፡፡ ፆሙን አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ብቻ ስለምን አደረገው ቢሉ ቀድሞ አባቶቻችን ነቢያት አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ፁመዋልና ከዚያ አትርፎ ቢጾም አተረፈ፤ ቢያጎድል አጎደለ የአባቶቻችንንም ሥርዐት አፈረሰ ብለው አይሁድ  ሕገ ወንጌልን ከመቀበል በተከለከሉ ነበርና ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን አርእስተ ኃጣውእ (አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉት ትዕቢት፣ ስስት እና ፍቅረ ንዋይ ናቸው) ድል አድርጎበታል፡፡አንድም ሙሴ በአርባ ዘመኑ ለዕብራዊ ረድቶ ግብፃዊውን ገድሎ በኆፃ ቀብሮታል፡፡ሙሴ የወልደ እግዚአብሔር፤ ዕብራዊ የአዳም፤ ግብፃዊው የዲያብሎስ፤ ኆፃ የመስቀል ምሳሌ  አንድም የሦስቱ አርእስተ ኃጣውእ ምሳሌ ነው፡፡ ሙሴ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ጹሞ ህገ ኦሪትን ሠርቷል

Saturday, February 14, 2015

ቅዱስ ፓትርያርኩ ዐብይ ጾምን አስመልከቶ መልእክት አስተላለፉ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የ2007 ዓ.ም. ዐብይ ጾምን አስመልክቶ የካቲት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. መልእክት አስተላለፉ፡፡

ቅዱስነታቸው ያስተላለፉትን ሙሉ መልእክት ከዚህ በታች አቅርበነዋል፡-


ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት፡፡