Saturday, March 21, 2015

፮ተኛ ሳምንት ገብርኄር


   ስያሜው የቅዱስ ያሬድ ሲሆን በዚህ ቀን ስለ ቅን አገልጋዮች ለአገልግሎት የሚያገለግሉበትን ጸጋ ለሰዎች ሁሉ የሚሰጥ “ወሀቤ ጸጋ” አገልጋዮቹን “ገብርኄር” እያለ ዋጋ የሚሰጥ አምላክ መሆኑ እየታሰበ ይመለካል፡፡


የእለቱ ስርዓተ አምልኮ
ዘቅዳሴ
በገባሬ ሰናይ ዲያቆን                                 2ጢሞ 2 ፥ 1-16
በንፍቅ ዲያቆን                                      1 ጴጥ 5 ፥ 1-12
በንፍቅ ቄስ                                          የሐዋ 1 ፥ 6-9

ምስባክ፡-
                                 ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፤
                                 ወሕግከኒ በማዕከለ ከርስየ፤
                                 ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡

አማርኛ ፡-                     አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለመናገር ወደድኩ                        
                                ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው
                                በታላቅ ጉባኤም ጽድቅህን አወራሁ (ተናገርኩ)፡፡

                                
ትርጉም፡-      አቤቱ አምላኬ ሆይ ፈቃድህን (ህግህን፣ ወንጌልህን) እናገር ዘንድ ወደደኩ ህግህ በልቦናዬ ተጽፎ ይኖራል፣ ቸርነትህንም በብዙ ጉባኤ ነገርሁ፡፡

ወንጌል፡-       ማቴ 25 ፥ 14-31

ቅዳሴ፡-         የባስልዮስ ቅዳሴ

    

መጾም

ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እነዳስተማሩት
ከዲን. በረከት ሐጎስ

ጾምን ጹመው የጾምን በረከት የማያገኙ ከጾም ጥቅምም የማይካፈሉ በከንቱ ይጾማሉ፡፡
ወርኃ ጾም የጥልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ጊዜ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ለእግዚአብሔር ያለንን ታላቅ ፍቅር የምናስመሰክርበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ጥልቅ ፍቅረ እግዚአብሔር የተነሳ አንድ ጿሚ በስጋዊ አካሉ ላይ ይሰለጥናል፡፡ ከምድራዊ ምኞቶችና ስስቶች በላይ ይንሳፈፋል፡፡ ሰማይዊውን ያጣጥማል፡፡ ጾም ወደ አምላካችን የምንቀርብበት፣የምናውቅበት ብሎም ሰውነታችንን ስለ እግዚአብሔር የምንቀድስበት ዘመን ነው፡፡ ጾም የነፍስ እረፍት፤ የመንፈስ እርካታ የምናገኝበት ዲያቢሎስንም የምንዋጋበት የተቀደሰ ጊዜ ነው፡፡

የጾም ጊዜያት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለመንፈሳዊ ኃይል የተሰጡ ናቸው፡፡ ገበሬ በመኸር ወራት አዘመራውን ሰብስቦ ከፊሉን ለገበያ ከፊሉን ለወርኃ ክረምት መቆያ እንደሚያከማች ሁሉ ክርስቲያኖችም በወርኃ ጾም በድካምና ጻማ የሚዘሩትን መንፈሳዊ አዝመራ የሚሰበስቡበት ወቅት ነው፡፡ የሚጾም ሰው በጾም ወራት መንፈሳዊ ኃይልና ብርታትን ከአምላኩ ይቀበላል፡፡   በእነዚህ የተቀደሱ ወራት የሚጎናጸፈው ኃይልም በፍስግ ቀናት ምርጉዝ ፣ ምቅዋም ይሆነዋል፡፡

Saturday, March 14, 2015

ደብረ ዘይት




ደብረ ዘይት ማለት የወይራ ዛፍ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ እንደምትገኝ ይነገራል፡፡ በዚህች ተራራ ሐዋርያት ስለ ዳግም ምጽአት ፣ ስለ ዓለም ህልፈት መቼና እንዴት እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ጌታን ጠይቀውታል፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ ሲቀርብ የሚታዩትን ምልክቶች በዝርዝር ነግሯቸዋል፡፡ (ማቴ 24 ፥ 1) በዚህ ሰንበትም ይህ ታሪክ የሚዘከርበት በመሆኑ ሳምንቱ በተራራው ስም ተሰይሟል፡፡

እንግዲህ በብሉይ ኪዳን  ዘመን ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ከአቤሴሎም በሸሸ ጊዜ የደብረ ዘይትን ተራራ ዐቀበት እንደወጣ (2ኛሳሙ 15 ፥ 30) ላይ እናነባለን፡፡ቤተ ፋጌና ቢታንያ የሚባሉት ታሪካውያን ቦታዎች ከደብረ ዘይት ግርጌ ይገኛሉ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባ እናነባለን፡፡ ጌቴሴማኒ የሚባለው ጌታችን የጸለየበት ቦታ ከደብረ ዘይት ስር ይገኛል፡፡(ማቴ 26 ፥ 30-36) ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገው በደብረ ዘይት ላይ ነው(ሉቃ 24 ፥ 1-52 ፣ ግ.ሐዋ 1 ፥ 12)፡፡ እግዲህ እነዚህ ሁሉ በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ደብረ ዘይት የተነገሩ ናቸው፡፡ 

፭ተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት





ስያሜው አንደቀደሙት ዕለታት ሁሉ የቅዱስ ያሬድ ስያሜ ሲሆን በዚህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሁለተኛ በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት (በመለኮታዊ ግርማው በሰው መጠን)  እንደሚመጣ የዓለምም ፍፃሜው እንዴት እንደሚሆን ለሐዋርያት በደብረ ዘይት ማስተማሩን እንዲሁም በክብር ያረገው ጌታን ለሚጠባበቁ ዋጋቸውን፣ ላልተቀበሉትም ፍዳቸውን ሊከፍል የምድርን ስርዓት ሊሽር ሰማይን እና ምድርን አሳልፎ ለወዳጆቹ መንግስቱን ሊያወርስ፣ የቅዱሳኑንም እንባ ከአይናቸው ሊያብስ ፣ ኃጥአንን ሊወቅስ ፣ ፃድቃንን ሊያወድስ (ቡሩካን ብሎ) መምጣቱን እያሰበች ቤተ ክርስቲያን ፈጣሪዋን ታመልካለች፡፡

Friday, March 13, 2015

ደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም


            

ደብረ ከዋክብት ዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንድነት ገዳም 1168 .. ታላቁ ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ በነበሩበት ጊዜ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ቅዱሳት በሆኑ እግሮቻቸው በመርገጥና በመባረክ በተራራው አናት ላይ በሚገኘው ውብና ማራኪ በሆነው ባሕር ውስጥ 1ዐዐ ዓመታት በመጸለይ ከዘለዓለማዊው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማይታበል ሕያው ቃል ኪዳን የተቀበሉበት 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ጽላታቸው የተቀረጸበት ቤተክርስቲያናቸው የታነጸበት በክቡር ስማቸው ገዳም የተመሠረተበት አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ብርሃነ ረድኤቱን በየጊዜው የሚገልጥበት በሀገራችን ኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት አንዱ ነው፡፡

የዚህን ታላቅ ገዳም አመሠራረትና ታሪክ እንዲሁም መልክአ ምድር አቀማመጡን በመጠኑ ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡