ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እነዳስተማሩት
ከዲን. በረከት ሐጎስ
ጾምን ጹመው የጾምን በረከት የማያገኙ ከጾም ጥቅምም የማይካፈሉ በከንቱ ይጾማሉ፡፡
ወርኃ ጾም የጥልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ጊዜ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ለእግዚአብሔር ያለንን ታላቅ ፍቅር
የምናስመሰክርበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ጥልቅ ፍቅረ እግዚአብሔር የተነሳ አንድ ጿሚ በስጋዊ አካሉ ላይ ይሰለጥናል፡፡ ከምድራዊ ምኞቶችና
ስስቶች በላይ ይንሳፈፋል፡፡ ሰማይዊውን ያጣጥማል፡፡ ጾም ወደ አምላካችን የምንቀርብበት፣የምናውቅበት ብሎም ሰውነታችንን ስለ እግዚአብሔር
የምንቀድስበት ዘመን ነው፡፡ ጾም የነፍስ እረፍት፤ የመንፈስ እርካታ የምናገኝበት ዲያቢሎስንም የምንዋጋበት የተቀደሰ ጊዜ ነው፡፡
የጾም ጊዜያት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለመንፈሳዊ ኃይል የተሰጡ ናቸው፡፡ ገበሬ በመኸር ወራት አዘመራውን ሰብስቦ ከፊሉን
ለገበያ ከፊሉን ለወርኃ ክረምት መቆያ እንደሚያከማች ሁሉ ክርስቲያኖችም በወርኃ ጾም በድካምና ጻማ የሚዘሩትን መንፈሳዊ አዝመራ
የሚሰበስቡበት ወቅት ነው፡፡ የሚጾም ሰው በጾም ወራት መንፈሳዊ ኃይልና ብርታትን ከአምላኩ ይቀበላል፡፡ በእነዚህ የተቀደሱ
ወራት የሚጎናጸፈው ኃይልም በፍስግ ቀናት ምርጉዝ ፣ ምቅዋም ይሆነዋል፡፡