Tuesday, February 24, 2015

መንፈሳዊት ፍቅር


   ልዑል እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ከልዕልና ወደ ትህትና ወደዚህች ምድር መጥቶ የሰዎች ልጆችን ያዳነበት ምስጢር እጅግ ረቂቅ ጥልቅ ነው፡፡ አምላካችን ለኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠው ክብሩን በውርደት ለውጦ ነው፤ጠላቶቹ ስንሆን ነው የወደደን፡፡እንግዲህ በጥልቅ መንፈሳዊ ስሜት በእውነት ካስተዋልን አምላክ ሰው የመሆኑ ምስጢርና ለቤዛነት የመጣበትን ዓላማ በቃልና በድርጊት የፈፀማቸውን ስራዎች ስናስብ ልባችን በቅንነትና በማስተዋል የተመላ ከሆነ ዘወትር ይህንን ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን ለኛ ያለውን ወደር የማይገኝለትን ፍቅሩን ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡
 
 “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብፅሖ እስከለሞት” ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ
አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው ተብሎ እንደተፃፈ፡፡የሰዎች ልጆችን ከባርነት ወደ ነፃነት፣ከመከራ ወደ ደስታ፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ለመግባት ያስቻላቸው የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደር የማይገኝለት ታላቅ ፍቅሩ ነው፡፡ስደት እና መንገላታት ውረደት እና በጥፊ መመታት፤መናቅ በብረት መቸንከር እነ በጦር መወጋት ለሰባኪው እና ለሰሚዎች፣ለፀሀፊው እና ለአንባቢዎች ቀላል መስሎ ቢታየንም አምላካችን ስለኛ ብዙ መከራ ተቀብሎ ህይወትን ሰጥቶናል፡፡ከፍ ያለው ፍቅሩ በክብደት መለኪያዎች ተመዝኖ ይህን ያህላል አይባልም፡፡ወርድ እና ቁመቱም ግምቱም አይታወቅም፡፡

Sunday, February 22, 2015

ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮



ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮

በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋል፡፡



በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና፡፡
ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ መቶ ተነሥቶ ከዐረገና ከአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው፡፡


Saturday, February 21, 2015

ሁለተኛ ሳምንት - ቅድስት



የካቲት ፲፬ ፳፻፯ ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓትና በትውፊት የበለፀገች መሆኗ የታመነ ነው፡፡ ሰፊ ሥርዓትና ትውፊት ያላት እንደመሆኗ መጠን የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትጾመው ጾም፤ የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትቆመው ማኅሌት በቂ ታሪክ፣ ትውፊትና ሥርዓት አለው፡፡ ያለታሪክ ያለትውፊትና ሥርዓት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትጾመው ጾም፤ የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትዘምረውም መዝሙር የለም፡፡


በዚህ በያዝነው ወቅት የምንጾመው ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም እንደመሆኑ መጠን በዚሁ የጾም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዘመነ ሥጋዌው ለሠራቸው የተአምራትና የትምህርት ሥራዎች መታሰቢያ በዓል በማድረግ ለእያንዳንዱ ሰንበት ስም በመስጠት በስሙ አንፃር የበዓሉን ታሪክ በመከተል ታመሰግናለች፤ ትዘምራለች፤ ትፀልያለች፤ ትቀድሳለች፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዓቢይ ጾም ውስጥ  ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ሰርቶላቸዋል፡፡ በመዝሙራቱ ውስጣዊ ምስጢር መሠረትም እያንዳንዱ እሑድ ስያሜ ተሰጥቶቸል፡፡ በዚሁም መሠረት ያሳለፍነውን ሳምንት ከቅበላው ዋዜማ ጀምሮ ዘወረደ ብለን በቤተ ክርስቲያናችን አክብረናል፡፡ በቀደመው ጽሑፋችንም የስያሜውን ትርጓሜ አይተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ እንደእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ የቀጣዩን ሰንበት/ሳምንት (የሁለተኛውን ሳምንት) ስያሜና ምሥጢሩን እንማማራለን፡፡