Friday, August 19, 2016

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር


‹‹አስተርእዮ›› ሥርወ ቃሉ ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በደብረ ታቦር›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በታቦር ተራራ መገለጥ›› ወይም መታየት የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን ይህም ከእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ጋር የተያያዘ እንደዚሁም ከምሥጢረ ሥጋዌና ከነገረ ድኅነት ጋር የተሳሰረ ታላቅ ምሥጢርን የያዘ መገለጥ ነው፡፡
ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ ‹እግዚአብሔር› በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለፍጡራኑ ተገልጧል፡፡ በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሣፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ መቅሠፍቱን በመላክ ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

Monday, July 4, 2016

                                                 ክረምት


          በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በዕለተ ረቡዕ የተፈጠሩት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ቀን ለመቁጠር፣ዘመንን፣ ወራትን፣ በዓላትንና አጽዋማትን ለማወቅ ወሳኝ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ ዘፍ.14-19፣ ዘዳ.12፡1፡፡

እንደ ቤተ ክርስቲያናችን አቆጣጠር አንድ ዓመት በፀሐይ አቆጣጠር 365 1/4 ቀናት፡፡ በጨረቃ አቆጣጠር 354 ቀናት፡፡ በከዋክብት አቆጣጠር ጸደይ፣በጋ፣መጸውና ክረምት የተባሉ አራት ወቅቶች አሉ፡፡

ወቅት እንዲፈራረቅ በዘመን ላይ የተሾሙ ዓመቱን በአራት ክፍለ ዘመን የሚገዙት አራት ከዋክብት ሲሆኑ በእያንዳንዱ ወር ላይ የሰለጠኑ ከአራቱ ከዋክብት ሥር እንደ ወታደር የሚያገለግሉ ሦስት ሦስት ወታደሮች በድምሩ 12 ከዋክብት አሉ፡፡ እነዚህ ከዋክብት ወቅቶቹ ሥርዐታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ የሚያደርጉና የእግዚአብሔር ጸጋ ለፍጥረቱ እንዲደርስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

ዓመቱን ለአራት ወቅቶች የሚከፈሉትና የሚመግቡት ከዋክብት የሚከተሉት ናቸው፡-
ምልክኤል፡-
በጸደይ የሰለጠነው ኮከብ ምልክኤል ሲሆን በሥሩ ያሉት ሦስት ከዋክብት/ወታደሮች/ ሚዛን በመስከረም ወጥቶ 30 ዕለት ከ 10 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ሚዛን ነው፡፡ አቅራብ በጥቅምት ወጥቶ 29 ዕለት ከ40 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ጊንጥ ነው ፡፡ ቀውስ በኅዳር ወጥቶ 29 ዕለት ከ28 ኬክሮስ የሚታይ መልኩ እንደ ቀስት ነው፡፡ (ኬኪሮስ ማለት ረጅም መስመር ማለት ሲሆን የቀንና የሌሊት ሰዓቶች ክፍል ነው፡፡ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ተዘርግቶ 60 ክፍሎች አሉት፡፡ ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ሁል ጊዜ እየሄዱበት በየቀኑ አንድ ጊዜ ያልፍበታል፡፡ 5 ኬክሮስ 1 ሰዓት ነው፡፡)

Friday, July 1, 2016

                   አባ ሙሴ ጸሊም 




ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቅዱሳንን ከተለያየ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡
በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ከተመለሱ ቅዱሳን መካከል አንዱ የኾኑትን በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ ፳፬ ቀን የሚዘከረዉን የአባ ሙሴ ጸሊምን ታሪክ በአጭሩ እናቀርብላችኋለን፡፡

Thursday, June 9, 2016

     ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 
            ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
                                                                                ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

           የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቍጥር ፻፷፬ በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የዘንድሮዉን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ድረ ለዐሥራ ስድስት ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

Tuesday, April 12, 2016

ሚያዝያ 6 ቀን የቅዱስ አዳም እና የቅድስት ሔዋን ዓመታዊ የዕረፍት መታሰቢያ በዓላቸው ነው!!! በረከታቸው በኛ ላይ ይደርብንና እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ከፈጠረለት በኋላ በስድስተኛው ቀን ዐርብ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ፈጠረ። እግዚአብሔር ሲፈጥረውም በእራሱ መልክ እና ምሳሌ ፈጠረው፤ በምድር ላይ ለሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ገዢ አደረገው። እግዚአብሔርም አዳም ብቻውን በመሆኑ ከጎኑ አጥንትን ወስዶ ሔዋንን ፈጠራት። በተፈጠሩበት ምድር አዳም አርባ ቀን ፣ ሔዋን ደግሞ ሰማንያ ቀን ከቆዩ በኋላ ወደ ኤዶም ገነት አስገባቸው። ይህን መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወንዶች በተወለዱ በአርባ ቀናቸው ፣ ሴቶች በተወለዱ በሰማንያ ቀናቸው ተጠምቀው የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ታደርጋለች። እግዚአብሔርም በገነት መካከል ያሉትን ፍሬዎች እንዲበሉ ፈቀደላቸው። ነገር ግን ዕፀ በለስ ተብላ የምትጠራውን ፍሬ እንዳይበሉ አዘዛቸው። ከዚህች ፍሬ ብትበሉ የሞት ሞትን ትሞታላችሁ ብሎ አስጠነቀቃቸው። አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ አክብረው ለ7 ዓመት ያህል ገነት ኖሩ። ሰይጣን ዲያብሎስ በእባብ በኩል የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ እንዲያፈርሱ ፈተና አመጣባቸው። ዲያብሎስ በእባብ አድሮ ወደ ሔዋን ቀርቦ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት። እሷም ዕፀ በለስን ብትበሉ ትሞታላችሁ እንደተባሉ ነገረችው። እባብም ለሔዋን ሞትን አትሞቱም ከእርስዋ በበላችሁ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር ትሆናላችሁ ብሎ በሀሰት አታለላት። ሔዋንም የእባብን ሽንገላ ሰምታ እውነት እንደ እግዚአብሔር የሚሆኑ መስሏት ለመብላት ወሰነች። ከፍሬውም ወሰደችና ከባልዋ ከአዳም ጋር አብረው በሉ። በበሉም ጊዜ ጸጋቸው ተገፈፈ፣ የክብር ልብሳቸውን አጡ፣ እነርሱም ዕራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ፤የበለስን ቅጠል ሰፍተው ለበሱ። የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ ስናፈርስ ጸጋችን ይገፈፋል፤ እግዚአብሔርም ያዝንብናል። አዳምና ሔዋንም የእግዚአብሔርን ድምፅ ሲሰሙ ፈርተው በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ። እግዚአብሔርም አዳምን ጠርቶ፦ ወዴት ነህ? አለው። እርሱም በገነት ድምፅህን ሰማሁ ዕራቁቴንም ስለ ሆንሁ ፈራሁ፥ ተደበቅሁም አለው። እግዚአብሔርም ዕራቁትህን እንደ ሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን? ሲለው አዳምም ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርስዋ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ አለው። እግዚአብሔርም ሁላቸውንም በጥፋታቸው ምክንያት ረገማቸው። እግዚአብሔርም እባቡን ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ፣ ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ በሆድህም ትሄዳለህ፥ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ ብሎ ረገመው። ሔዋንንም በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ በጭንቅ ትወልጃለሽ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል ብሎ ረገማት። አዳምንም እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍ በልተሃልና ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና ብሎ ረገመው። እግዚአብሔርም በበደላቸው ምክንያት ከረገማቸው በኋላ ከ ገነት አስወጣቸው፥ አዳምም የተገኘባትን መሬት አርሶ መብላት ጀመረ። አዳምና ሔዋን ከገነት ከወጡ በኋላ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ በማጣታቸው በሰሩት ኃጢአት ተጸጽተው እግዚአብሔር እንዲምራቸው ሱባኤ (ጸሎት) ያዙ። እግዚአብሔር ጸሎታቸውን እና ልመናቸውን ተመልክቶ እንደሚምራቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው። ቃል ኪዳኑም “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ከ5500 ዘመን በኋላ አድንሃለሁ” የሚለው ነበር። ቅዱስ አዳም ሚያዝያ 6 ቀን በ930 ዓመቱ ዕድሜ ጠግቦ አረፈና በቀራንዮ ተቀበረ። እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልቀረም ከእናታችን ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳምን ከእነ ልጅ ልጆቹ አዳነን። በአጠቃላይ ከአዳምና ሔዋን ታሪክ የምንማረው አታድርጉ የተባልነውን ነገር ማድረግ እንደለለብን ፤እሱን አልፈን ግን ብናደርግ እስከ ሞት ድረስ መከራ ሊያመጣብን እንደሚችል መረዳት አለብን። እግዚአብሔር ደግሞ የይቅርታና የምሕረት አምላክ እንደሆነ እንረዳለን። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ መታዘዝ ይኖርብናል።