Saturday, March 21, 2015

መጾም

ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እነዳስተማሩት
ከዲን. በረከት ሐጎስ

ጾምን ጹመው የጾምን በረከት የማያገኙ ከጾም ጥቅምም የማይካፈሉ በከንቱ ይጾማሉ፡፡
ወርኃ ጾም የጥልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ጊዜ ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት ለእግዚአብሔር ያለንን ታላቅ ፍቅር የምናስመሰክርበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ጥልቅ ፍቅረ እግዚአብሔር የተነሳ አንድ ጿሚ በስጋዊ አካሉ ላይ ይሰለጥናል፡፡ ከምድራዊ ምኞቶችና ስስቶች በላይ ይንሳፈፋል፡፡ ሰማይዊውን ያጣጥማል፡፡ ጾም ወደ አምላካችን የምንቀርብበት፣የምናውቅበት ብሎም ሰውነታችንን ስለ እግዚአብሔር የምንቀድስበት ዘመን ነው፡፡ ጾም የነፍስ እረፍት፤ የመንፈስ እርካታ የምናገኝበት ዲያቢሎስንም የምንዋጋበት የተቀደሰ ጊዜ ነው፡፡

የጾም ጊዜያት ከወትሮው በተለየ መልኩ ለመንፈሳዊ ኃይል የተሰጡ ናቸው፡፡ ገበሬ በመኸር ወራት አዘመራውን ሰብስቦ ከፊሉን ለገበያ ከፊሉን ለወርኃ ክረምት መቆያ እንደሚያከማች ሁሉ ክርስቲያኖችም በወርኃ ጾም በድካምና ጻማ የሚዘሩትን መንፈሳዊ አዝመራ የሚሰበስቡበት ወቅት ነው፡፡ የሚጾም ሰው በጾም ወራት መንፈሳዊ ኃይልና ብርታትን ከአምላኩ ይቀበላል፡፡   በእነዚህ የተቀደሱ ወራት የሚጎናጸፈው ኃይልም በፍስግ ቀናት ምርጉዝ ፣ ምቅዋም ይሆነዋል፡፡
ለምሳሌ ዐቢይ ጾምን በምንፈሳዊ ትጋትና ተጋድሎ ያሳለፈ አንድ ክርስቲያን ከትንሳኤ በኋላ ስግደትና ጾም በተወገዘባቸው ሐምሳ የፍስግ ቀናት የሚያገለግለውን የነፍስ ስንቅ የቋጥራል፡፡
መንፈሳዊ ጾምን ለመጾም የሚሻ ሁሉ የሚከተሉትን ነጥቦች በልቡ ማኖር ይጠበቅበታል፡፡

1.    የጾም ዓላማና ምክንያት ፍጹም መንፈሳዊ መሆኑን መረዳት፣
ጾም በትዕዛዝ፣ በግዴታ ወይም በልምድ የሚፈፀም አይደለም፡፡ ለውዳሴ ከንቱም መጾም የለበትም፡፡ እገሌ ጾሟልና እኔስ ከማን አንሳለሁ ፣እገሊት ጾማለችና እኔም መጾም አለብኝ  በሚል ስጋዊ ምኞትና ፉክክር የሚደረግ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስላወጀች ብቻ እንደ ግዴታ  መጾምም የጾምን መንፈሳዊነት ያናጋዋል፡፡
ማንም ክርስቲያን ሲጾም መንፈሳዊ ትርጉሙ ገብቶትና ተረድቶት መሆን አለበት፡፡ የጾም ጊዜ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፍቅር  ከስጋዊ፣ አካለዊና ቁሳዊ ነገሮች አስበልጦ ስጋውን በማስገዛት ነፍሱን የሚያሳድግበት ነው፡፡

2.   ጾም የንስሐ እና የንጽሐተ ልቡና  ወቅት መሆኑን መገንዘብ፣
የጾም ጊዜ ከወትሮው በተለየ መልኩ አብዝተን በቅድስና ሕይወት የምንመላለስበት ነው፡፡ በሰውም ሆነ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሰራናቸውን  በደሎች ተጸጽተን ራሳችንን ለካህን የምናስመረምርበት፣ ከቅድሳት ምስጢራት ተካፋይ የምንሆንበትና በረከተ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምናደርግበት  ወቅት ነው፡፡

3.   ጾም ጽኑዕ መንፈሳዊ የጊዜ ሰሌዳን ተከትሎ መንፈሳዊ እድገት የሚገኝበት መሆኑን ማወቅ፣
በምንጾም ጊዜ ከስጋዊ አካሎቻችን በአንፃሩ መንፈሳዊ አካላችንን (ነፍሳችንን) እናገዝፋለን፡፡ ትኩረታችንን ከስጋ ይልቅ ነፍስ ላይ ማኖር ይጠበቅብናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከጮማና ቅቤ መራቅ ብቻ ዋጋ አያሰጥም፡፡ ራስን ለእነዚህ የተቀደሱ ጊዜያት ለይቶ የተቀደሰውን ማድረግ እነጂ፡፡ መጾም ወደ ነፍስ ጥንካሬ ይመራል፡፡ የነፍስ ጥንካሬም ወደ ጾም ይመራል፡፡

በጾም ጊዜያት ጎልተው የሚዘወተሩ ተግባራት
የጾም ወቅት ሥጋችንን አቅልለን፣ ከእንቅልፍ ሰዓታችን ቆርሰን፣ ለጸሎት የምንተጋበት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የምናነብበት መሆን አለበት፡፡ መንፈሳዊ ንባብ በራሱ ወደ ጸሎትና ተመስጦ ይመራልና፡፡ ይህም ጸሎታችን በኃይል እንዲሞላ ያደርገዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከግል ጸሎታችን ጎን ለጎን  በቤተክርስቲያናችን በማሕበር የሚደረጉ የጸሎት ስርዓቶች ላ ይ መሳተፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከወትሮው በበለጠ ኪዳን ማድረስን፣ ቅዳሴ ማስቀደስን፣ በምሕላ ጸሎት መሳተፍን ማዘውተር ይገባናል፡፡

ለዚህም ነው በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በወርኃ ጾም ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ ሁኔታ የአገልግሎት አድማሱ ሰፍቶ የሚታየው፡፡ ያለማቋረጥ ስብሐተ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ በየገዳማቱ ዘወትር ሰዓታት ይቆማል፡፡ በየአድባራቱ ስብሐተ ነግሕ ይደረጋል፡፡ ቅኔ እነደ ጅረት ይፈሳል፡፡ የቤተክርስቲያናችን ብርሃን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ከደረሳቸው አምስት የዜማ መጻሕፍት ሁለቱ (ምዕራፍና ጾመ ድጓ) በዋነኝነት በዐቢይ ጾም ለአገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡

ጾምን ስናነሳ ስግደትንም ማሰብ ግድ ይለናል፡፡ ሁለቱ የማይነጣጠሉ ናቸውና፡፡ ሁለቱም ወደ ትህትና መንገድ ይመሩናል፤ የተሰበረ ልብ እነዲኖረንም ይረዱናል፡፡ ሥጋዊ አካላችንን በጾምና በስግደት ማድከምና ማዋረድ ነፍሳችንን በትህትና ኃይል እንድትበረታ ያደርጋታል፡፡  

የጾም ምክንያታዊነትና ከጾም ጋር ሕብረት ያላቸው ምግባራትን መፈጸም
ጾመ ሐዋርያትን የጌታ ደቀ መዛሙርት መንፈሳዊ አገልግሎት ከመጀመራቸው አስቀድመው ኃይልና ብርታት ይሆናቸው ዘንድ ጾሙት፡፡ የነነዌ ሰዎች ከኀጢአታቸው ብዛት ለመዓት የተዘረጋችውን የእግዚአብሔር  እጅ በንስሐ ጾም መለሱ፡፡ እንደ አስቴር ያሉ ደግሞ ወገናቸውን በጾም ወልታ ከመቅሰፍት ታደጉ፡፡  እኒህ ከላይ የጠቀስናቸው አጽዋማት በሙሉ በውስጣቸው  ፍቅርን፣መስዋዕትነትን፣ መንፈሳዊ ህብረትንና ሌሎች ሰናይ ትሩፋትን ያቀፉ ናቸው፡፡

እኛም በምንጾምበት ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ሁኖ ሳለ በገዳመ ቆሮንቶስ ለእኛ ምሳሌ እንዲሆነን መጾሙን እያስታወስን በቅዱስ መንፈስ እንመላ ዘንድ ሰናይ ምግባራትንና ትሩፋትን አንግበን ልንጾም ይገባናል፡፡

ጾም በንስሐ መታጀብ አለበት
የጾም ቀናት የተቀደሱ ናቸው፡፡ የሰው ልጅም በቅድስና እነዲኖርባቸው ተሰርተዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት አዕምሮ፣ልብና አካል መቀደስ አለባቸው፡፡ ጾም ከኃጢአት ርቀን ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ጥረት የምናደርግበት የልምምድ ወቅት ነው፡፡
በመሆኑም ማንም ቢሆን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ቢወድ ራሱን በንስሐ ከኃጢአት እስራት ነፃ ማውጣት አለበት፡፡ ንስሐ ከኃጢአት ባርነት፤ ከሕሊና ወቀሳ ነፃ መውጫ መንገድ ናትና፡፡

በጾም ጊዜ ሥጋ ከምግብ ትከለከላለች፤ ነፍስም ከዓለማዊ ምኞትና መቋመጥ፤ ትታቀባለች፡፡ ሰው በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡ እራሳችንን እንመርምር፤ በፍኖተ ንስሐ እየተመላለስን ነውን?  ያለ ንስሐ እግዚአብሔር ጾማችንን አይቀበልም፡፡፡ በመሆኑም ወይ ከመንግስተ ሰማያት ወይ ከምድር ሳንሆን እንዲሁ ባክነን እንቀራለን! እግዚአብሔር ጾም ጸሎታችንን እንዲቀበል ከወደድን መጀመሪያ እራሳቸንን እንመርምር፤ ስለበደላችን ንስሐ እንግባ፤ ኃጢአትንም እንጠየፋት፡፡

በዚህ ጉዳይ የነነዌ ሰዎች ጾም ጥሩ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ "ከንጉሱና ከመሳፍንቱ የወጣ አዋጅ…ማንም ሰው ወይም እንስሳ…ምንም ነገር አይቅመስ፤ አይብላ ፤ ውሃም አይጠጣ፡፡ ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ፡፡" ዮናስ 3፡8 በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በቁጣው አላጣፋቸውም፡፡ መጽሐፉ ንስሐቸውን ተመለከተ ይላል እንጂ ማቅ መልበሳቸውን ተመለከተ አይልም፡፡ የጾማቸውም መሰረታዊ ዓላማ በፍጹም መፀፀት የቀደመ ርኵስ ተግባራቸውን በመጥላት የእግዚአብሔርን ቁጣ መመለስ ነበርና፡፡ እርሱም ርሑቀ መዓት ነውና ንስሐቸውን ተቀብሏል፡፡
በመጽሐፈ ኢዩኤልም እንዲሁ በንስሐ የታጀበ ጾምን እንመለከታለን፡፡ ጌታ በነቢዩ አንደበት እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡"አሁንም ቢሆን፣ በጾም፣ በልቅሶና በሐዘን፣ በፍጹም ልባችሁ ወደ እኔ ተመለሱ…ልባችሁን እነጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፡፡" ኢዩ. 2፡12-13
እንግዲህ በዚህ ቃል ጾም በልቅሶ፣ ፀፀትና ንስሐ ሊታጀብ እንደሚገባ በግልጽ ተነግሮናል፡፡ ስለዚህ ጾም ከምግብ መታቀብ ብቻ ሳይሆን በፍጹም ልብ እግዚአብሔርን መሻትም ነው፡፡
ነብዩ ዳንኤል በጾሙ የሕዝቡን ንስሐ ተናዝዟል፡፡ በመፀፀት እንዲህ ሲል ተማጽኗል፤
"እኛ ኃጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም ፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል…ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ…በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል፡፡" ዳን. 9፡5-8
ስለዘህ በጾም ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር እንታረቅ፡፡ ልበ አምላክ የተባለ ነብዩ ዳዊት  በመዝ. 13፡1 እንደተናገረው "አቤቱ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ?"  ሳይሆን "አቤቱ እስከ መቼ ፈጽሜ እረሳሃለው? እስከመቼስ ፊቴን ከአንተ እሰውራለሁ?" እንበል፡፡

ነፍሳችንን እናጥራት፤ እንቀድሳትም፡፡ በእነዚህ ቀናት እግዚአብሔርን ለመቀበል እንዘጋጅ፡፡ ከእህል በመራቅ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በለልባችን እልፍኝ እንዲገባ፤ እንዲኖርም የተዘጋጀን እንሁን፡፡ በኃጢአት ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀን እየቦካን  የምንኖር ካለን በማየ ንስሐ ሰውነታችንን እንጠብ፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እንታረቅ፡፡ ከእግዚአብሔር የታረቅን  ከሆነም ለእርሱ ያለንን ፍቅር በመታመን እናጠንክር፡፡በጾም ወራት ርኵሰትን ተጠይፈናት እንደሆነ፤ በፍስክም ወራት እንዲሁ እናድርግ፡፡

ንስሐ በጾም  ወራት ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ በጾም ጊዜያት ይጠነክራል እንጂ፡፡ ሰው በእነዚህ ቀናት ልቡን ያነጻል ቅድስናንም ይለማመዳል፡፡ ይህን የንጽሕና መንገድ እንደ የሕይወት ዘይቤ ተጠቅሞ እስከ እለተ ሞቱ ጠብቆ ሊጓዝበት ይገባል፡፡ አለበለዚያማ የእርያ እጥበት፣ የውሻ ትውከት  ይሆንብናል፡፡ በጾም ቅድስና በፍስክ ርኵሰት ለክርስቲያን አይስማማውም፡፡

ከሁሉም በላይ ከዲያብሎስ ጋር ለመታገል የተዘጋጀን እንሁን፡፡ ኢያሱ ወልደ ሲራክ ወንድ ልጁን "እግዚአብሔርን ለማገልገል በተነሳህ ጊዜ እራስህን ለፈተና ማዘጋጀት ይኖርብሃል" ሲል መክሮታል፡፡

በመሆኑም ሰይጣን ጾም ጸሎታችንን፣ ንስሐችንን በተመተለከተ ጊዜ አብዝቶ ይቀናል፤ ይንገበገባልም፡፡ በዚህም ምክንያት የመንፈሳዊ ድካማችንን ዋጋ፣ ፍሬ እንዳናገኝ ይታገለናል፡፡ ለውድቀታችንም የሚሆን ጉድጓድ በየጊዜው ይቆፍራል፡፡ "ተስፋ እስክትቆርጥ ድረስ አልተውህም!" እያለም ያናፋል፡፡ እኛ ግን የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል እየዘከርን እንቃወመዋለን፡፡ "ጠላታቸሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሳ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል፡፡ በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ ተቃወሙት ፡፡"1ጴጥ. 5፡8

እንግዲህ ጾም የመንፈሳዊ ውጊያ ወቅት መሆኑን እናስተውል፡፡  በማቴዎስ 4 እንደተጻፈ ዲያብሎስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንኳ ከመፈተን አልቦዘነም፡፡ ይልቁንስ በክርስቶስ ለታመንን ለእኛ ክርስቲያኖች የጾም ወራት ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስን ከእግራችን በታች ቀጥቅጠን የድል አክሊል ተቀዳጅተን ከክርስቶስ ጋር አንድ የምን ሆንበት ጊዜ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን  

No comments:

Post a Comment