Saturday, March 7, 2015

፬ተኛ ሳምንት መጻጕዕ




መጻጕዕ ማለት ድውይ በሽተኛ  ማለት ነው፡፡ ሳምንቱ በዚህ የተሰየመበት ዋናው ምክንያት በ ዮሐ 5÷1-9 እንደተፃፈው ለሠላሣ ስምንት ዓመታት በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ይኖር የነበረ በሽተኛን ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ በተአምር የፈወሰበት  ሰንበት መታሰቢያ ስለሆነ ነው፡፡ይህ ድውይ የፀናበት ሰው በእብራይስጥ ቤተሳይዳ ወደምትባል መጠመቂያ ቦታ የሚወስደው ወገንና ዘመድ አጥቶ በመጠመቂያ አካባቢ   ለ38 ዓመት በአልጋው ላይ እንደተኛ ቆይቷል፡፡ ማዳን የባሕሪው የሆነው ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በአንድ ቃል  “ተነስና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎ ፈውሶታል፡፡ ነገር ግን “ተነስና ሂድ” ከማለቱ በፊት “መዳን ትወዳለህን?” ብሎ መልካም ምኞቱን ጠይቆታል፡፡ ለምን? መዳን ወዳለሁ ብሎ እንደሚመልስለት ያውቅ የለምን ስለምን እንዲህ ብሎ ጠየቀው? ይህም አላዋቂ የነበረን ስጋ እንደ ተዋሐደ ለማጠየቅ  እንዲህ ሲል ጠይቆታል፡፡ ድውዩም መዳን እወድ ነበር ነገር ግን ወደጸበሉ ተሸክሞ የሚያደርሰኝ የለም በማለት ብቸኝነቱን ተናግሯል፡፡ አባባሉም ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ በወቅቱ የሠላሣ ዓመት ወጣት ስለነበረ ተሸክሞ ወደ ጠበሉ ያደርሰኛል አልያም ብዙ ተከታዮች ስለነበሩት አንዱን ያዝልኛል ብሎ በማሰብ ነው፡፡ምክንያቱም አምላክነቱን ፣ ሁሉን ቻይነቱን አያውቅም ነበርና፡፡
ይሁን እንጂ ጌታችንም የአምነቱን ደካማነት ተመልክቶ ሊተወው አልወደደም ይልቁንም እርሱ ያላሰበውን ድንቅ ስራ አደረገለት እነጂ፡፡ ስለዚህ እኛም መዳን ትሻለህን ስንባል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአምላክነቱ አምነን ለመዳን የሚያስፈልጉትን እምነትና በጎ ምግባርን ይዘን አዎን ጌታ ሆይ ልንለው ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
ቤተክርስቲያናችን በዚህ ሳምንት የጸበልን ፈዋሽነት አብልጣ የምታሰተምርበት ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም ምንም እንኳ ያ ድውይ አጋዥ አጥቶ ለ38 ዓመታት በመጠመቂያ ዳር ቢቆይም በየቀኑ በጸበሉ ተጠምቀው በሽተኖች ይድኑ እንደነበር ተፅፎልናል፡፡(ዮሐ 5÷1-9 5) የሚድኑት ግን መልአኩ ከሰማያት ወርዶ ጸበሉን በባረከበት ቅፅበት ቀድሞ የሚገባ ሰው ብቻ ነበር፡፡ “እስመ መልአከ እግዚአብሔር በጊዜ ይወርድ ይትኀወክ ማይ ወዘይወርድ ቀዲሙ እምድህረ ሁከተ ማይ ወይትሐጸብ የሐዩ እምኵሉ ደዌ ዘቦ” እንዲል ( ዮሐ 5 ÷ 4) ፡፡ ይህም የሆነው በብሉይ ኪዳን ዘመን ፍጹም የሚባል ድኅነተ ስጋም ሆነ ድኅነተ ነፍስ ስላልነበረ ነው፡፡ምክንያቱም በአዳም በደል ምክንያት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ስለነበር ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ በዚህ ጥቅስ መናፍቃን ውኃ  የሚሉት “ጸበል” እኛ እንፈወስበት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጠን መልካም ስጦታ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ እንዲያውም ምህረት በሌለበት በዚያ ዘመን መልአከ እግዚአብሔር እየወረደ ይባርከው ከነበረ አሁን ሰው ከእግዚአብሔር እንዲሁም ከመላእክት ጋር በቤተልሔም ታርቀው ሐዲስ ኪዳን በተሰራባት በዚህች ዘመን እንዴት ይበልጥኑ መላእክት አይባርኩትም? ማስተዋሉን ለሁላችን ያድለን፡፡
በነገራችን ላይ ጸበል ውኃ ነው ለሚሉ እኛም ውኃ አይደለም አላልንም ነገር ግን እግዚአብሔር ለፈውስ የለየው መላእክትም ከሰማያት እየወረዱ የሚባርኩት ውኃ ነው፡፡በመሰረቱ እኛን ከአፈር ላይ አንስቶ የሰራ ጌታ በውኃ ላይ አድሮ ቢፈውስ ምን ይደንቃል? (ኦ ዝ መንክር ወእጹብ )አለ ሊቁ በድርሳኑ እግዚአብሔር ከክህደት ይጠብቀን፡፡


የዕለቱ ስርዓተ አምልኮ
ዘቅዳሴ                   
 ገላት          5፥1 - ፍ፡ጻ      “ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ እነሆ አኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ በህግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል………


 ያዕቆብ     5፥14- ፍ፡ጻ     “ ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት የእምነት ጸሎት ድውዩን ያድናል ጌታም ያስነሳዋል፤ ኃጢአትንም ሰርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል…….


 ግብ ሐዋ     3፥1 -12          “ ጴጥሮስና ዮሐንስም በጸሎት ጊዜ በዘጠኝ ሰዓት ወደ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሏት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ  የሆነ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ………….


  ምስባክ  መዝ 40፥3            እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዓራተ ሕማሙ፤
                          ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፤
                            አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፡፡


ዮሐ     5፥ 1 – 25     “ከዚህም በኋላ የአይሁድ በዓልም ነበረ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞች እና ዕውሮች፣አንካሶችም፣ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙህዝብ ይተኙ ነበረ አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶውኃውን ያናውጥ ነበርና፡፡እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር፡፡ በዚያም ከሠላሣ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፡፡…………………… ሙሉውን ያንብቡ 
  

ቅዳሴ       -      ዘእግዚእነ
 

No comments:

Post a Comment