Saturday, March 28, 2015

፯ተኛ ሳምንት ኒቆዲሞስ




ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ እና መምህር ነበረ “ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ መልአኮሙ ለአይሁድ” ዮሐ3÷1 እንዲል፡፡ ሳምንቱ (ሰንበቱ) በእርሱ የተሰየመበት ዋናው ምክንያት ይህ ሰው በሌሊት እየመጣ ምስጢረ ጥምቀትን፣ ዳግም ልደትን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ስር ቁጭ ብሎ የተማረበት ቀን መታሰቢያ ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም ትምህርቱ ጌታችን ዋና የሆነውን እና ሰው ከውሀ እና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት እንደማይገባ በግልጽ አስተምሮታል፡


ኒቆዲሞስ ከቀን ይልቅ በሌሊት መማርን ስለምን መረጠ? 


ኒቆዲሞስ ይህንን ያደረገው ስለሶስት ነገር እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ይናገራሉ ያስተምራሉ፡፡
፩. በአይሁድ ላለመነቀፍ ፈልጎ ፡- የአይሁድ አለቃ እና መምህር ስለነበረ እርሱ ራሱ ከመምህር እግር ስር ቆጭ ብሎ ማለትም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ  እግር ስር ተቀምጦ ሲማር አይሁዶች ቢያዩት ሳይገባው ነው መምህረ አይሁድ የሆነው ብለው እንዳይነቅፉት በመፍራት ነው፡፡ እርሱ ስለተቀመጠበት ወንበር ተጨነቀ እንጂ አምላኩ ለእርሱ ብሎ ከክብሩ በትህትና ዝቅ ዝቅ ማለቱን፣ ሰው መሆን የባህሪው ያልሆነ አምላክ ሰውነት ተስማምቶት ወደ ምድር መምጣቱን ግን አላስተዋለም ነበር፡፡  አሁንም ቢሆን ባለንበት ዘመን ባለኃብት ስለሆንን አልያም ባለስልጣን ስለሆንን ከመምህራን(ከሊቃውንተ ቤተክርስቲያን)  እግር ስር ቁጭ ብሎ መማር የሚያሳፍረን እንዲሁም የንቀት ስሜት የተጠናወተን ብዙዎች አለን፡፡ 


፪. በአይሁድ እንዳይከሰስ ፈርቶ፡- በጊዜው አይሁዶች የክርስቶስን ትምህርት የሚቀበል እርሱንም የሚከተል ከማኅበራችን ይለይ የሚል ህግ ነበራቸው ህጋችንን ስላላከበርክ ከማኅበራችን መወገድ አለብህ ብለው እንዳይከሱት እና እንዳያገሉት ፈርቶ በማታ መማርን መርጧል፡፡ አሁንም ቢሆን ከእድራችን፣ ከማኅበራችን፣ ከክልላችን፣ ከፓርቲያችን፣ ከድርጅታችን ትገለላላችሁ በማለት  ተሊወ እግዚአብሔርን ገንዘቡ አድርጎ የነበረን ምዕመን የሚያስፈራሩ አስፈራርተውም ከጽድቅ መንገድ ያወጡ ዳግማዊ አይሁዶች ይህንንም ፈርተው የእነርሱን ፍላጎት ለሟሟላት ሀይማኖታቸውን የካዱ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ እግዚአብሔር በቸርነቱ አይለየን፡፡


. አእምሮ ልቦናውን ሰብስቦ ለመማር ስለፈለገ፡- ቀን እንደሚታወቀው ብርሐን ስለሆነ ሰዎችም ከጨለማ ይልቅ ብርሐንን ለተለያዩ ስራዎቻቸው ስለሚመርጡ እና በዚህም ምክንያት ጫጫታ፣ ረብሻ፣ ጨዋታ የሚበዛ ስለሆነ ነገረ ሀይማኖትን በተረጋጋ አእምሮ መማር ያስቸግራል፡፡ በመሆኑም አብዛኛው ሰው እንቅልፍ በተኛበት ምድሪቱ ላይ ፀጥታ በሰፈነበት ሰዓት ሀሳብ የሚበትን ነገር ስለማይኖር አንድም ቀን ቀን የራሱ ስራ ነበረበትና ኒቆዲሞስ ከቀኑ ይልቅ ሌሊቱን  መርጧል፡፡


እንግዲህ ስለነዚህ ሶስት ነገሮች ብሎ ኒቆዲሞስ በሌሊት መማርን ቢመርጥም ከእርሱ የምንማረው ነገር ግን አለ፡፡ ይህም እምነትን እና ትህትናን ነው፡፡ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ካልሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ሊያደርግ የሚችል በውኑ አይኖርም” ዮሐ 3 ÷2 ይህ እምነት ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነቱን ባይረዳም በእግዚአብሔር ፈቃድ የመጣ መሆኑን አምኗልና፡፡ እርሱ የራሱ ማዕረግና ክብር ያለው አለቃና መምህር ቢሆንም የክርስቶስን ክብር አምኖ በእግሩ ስር ቁጭ ብሎ መማርን መምረጡም ትህትና ነው፡፡ እምነትን እና ትህትናን ገንዘብ በማድረጉ የኒቆዲሞስ ታሪክ በዚህ አላበቃም፡፡ በመጨረሻው ቀን ዮሴፍ ከተባለው ሰው ጋር የክርስቶስን ስጋ ከመስቀል አውርዶ በሽቱ ቀብቶና ገንዞ በአዲስ መቃብር ከቀበሩት ሁለት ሰዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡ ክርስትና የሚለውም ይኸው ነው፡፡ በመጀመሪያ በክርስቶስ አምላክነት ማመን ከመምህራን እግር መስቀሉ ድረስ መከተል ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ይህን በትክክል ፈጽሞታልና እውነተኛ ክርስቲያን ሊባል ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን እያሰብን መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ብዙዎቻችን ባለስልጣን ሌሎቻችንም ባለሀብት ስለሆንን ለገንዘባችን እንጂ ለእግዚአብሔር የሚሆነን ጊዜ አጥተናል፡ ቀሪዎቻችንም ቃለ እግዚአብሔርን ላለመማር የየራሳችንን ምክንያት እናቀርባለን፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ለመማር የሚከለክሉት ብዙ ነገሮች ቢኖሩትም ሁሉንም ተጋፍጦ ቃሉን ለመማር በመብቃቱ የክርስቶስን ስጋ ገንዞ ለመቅበር እና በታላቁ መጽሐፍ ተመዝግቦ በታሪክ ለመዘከር በቅቷል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችንም ሳምንቱን ኒቆዲሞስ ብላ ሰይማ በኒቆዲሞስ ታሪክ መነሻነት የእኛን ህይወት የሚቃኝ ትምህርት ታስተምርበታለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን!