Saturday, March 21, 2015

፮ተኛ ሳምንት ገብርኄር



ገብርኄር ማለት ቸር አገልጋይ ማለት ነው፡፡ ይህንንም  በ ማቴ 25 ፥ 14-30 ላይ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌልን አደራ በምሳሌ እንዳስተማረ እንረዳለን፡፡ ትምህርቱ አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ ወደሩቅ ሀገር ለመሄድ ባሰበ ጊዜ አገልጋዮቹን ጠርቶ ከመንገዱ እስኪመለስ ድረስ ይሰራለት ዘንድ ለአንዱ አምስት፣ ለሁለተኛው ሁለት፣ ለሶስተኛው አንድ መክሊት (ታለንት) ሰጣቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት መክሊት በማትረፍ አስር መክሊት አደረገው፤ ሁለት መክሊት የተቀበለው  ወጥቶ ወርዶ እጥፍ አትርፎ  አራት አደረገው፡፡ ባለ አንዱ ግን ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት በልቡ ውስጥ ስጋት፣ ጥርጣሬ፣ ፍርሀትንና አለማመንን ስላነገሰ ብሰራበት ቢጠፋብኝስ? ቢሰርቁኝስ? ቢቀሙኝስ? እያለ በማሰብ እሰራለሁ ብዬ ያለኝን ከማጣ ለምን ደብቄ  አስቀምጬ በመቆየት ሲመጣ የሰጠኝን አልመልስም ብሎ መክሊቱን  ቆፍሮ ቀበረው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ባለንብረቱ መጣና አገልጋዮቹን ይተሳሰባቸው ጀመር፡፡


በቅድሚያ፡- አምስት የወሰደው መጣና ጌታዬ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር ይኸውና ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ ብሎ አስር መክሊት ለጌታው ሰጠ፤  “ጌታውም መልካም አደረግህ” አንተ መልካም አገልጋይ (ገብርኄር) በጥቂቱ ስለታመንህ በብዙ ላይ ስለምሾምህ ና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

ሁለተኛው፡- ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አራት መክሊት ብሎ እጥፍ ማትረፉን ገልጾ ለጌታው አስረከበ፤ እንደ  አምስቱ “መልካም አደርግህ ቸር አገልጋይ ነህ በጥቂቱ ስለታመንክ በብዙ ላይ እሾምሀለሁ” ተባለ፡፡

ሶስተኛው፡- ሰነፍ ቃሉም መራራ ነው የሰነፍ አካሉ ብቻ ሳይሆን አእምሮውም ሰነፍ ነው፡፡ ጌታው ገንዘቡን ሲጠይቀው ጌታ ሆይ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንክበት የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንክን አውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁ ሄጄም መሬት ቆፍሬ መክሊትህን ጉድጓድ ውስጥ ቀበርኩት ገንዘብህ ይኸውልህ ውሰድ፡፡ ጌታውም ይህንን ያህል ጨካኝ እንደሆንኩ ካወቅህ ንብረቴን ከነወለዱ ልትመልስ ይገባህ ነበር፤ ገንዘቤን ልትሰራበት ሲገባህ ለምን ቀበርከው ብሎ መክሊቱን ወደእርሱ ወስዶ ለባለ አምስቱ ጨምሩለት ላለው ይጨመርለታል ይትረፈረፍለትማል፤ ለሌለው ግን ያው ያለው ይወሰደበታል ይህንን የማይረባ አገልጋይ ግን ልቅሶ ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጽኑ የፍርድ ቦታ ውሰዱት አለ ይላል በምሳሌ የተሰጠው የመድኃኒታችን ትምህርት፡፡ የትምህርቱም ትርጉም እንደሚከተለው ነው፡፡

የንብረቱ ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ሶስቱ አገልጋዮች ልዩ ልዩ ጸጋ ተሰጥቷቸው ያሉ ህዝበ ክርስቲያን ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ስጦታው በአኃዝ (በቁጥር) ሲታይ ልዩነት መኖሩ፣ አንዱ ጸጋ ከሌላው ጸጋ የሚለይ መሆኑን ያሳያል፡፡


የአገልጋዮቹ ባህርይ ምን ይመስላል?    
የመጀመሪያውና የሁለተኛው  አገልጋዮች መንፈስ ሁለቱም ሠርቶ ማግኘት እንደሚቻል የሚያምኑ ፣ ለጌታቸው ታማኞች፣ በሥራ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግር በማሰብ ጊዜያቸውን የማያጠፉ ናቸው፡፡ ሁለተኛው አገልጋይም እንደ መጀመሪያው አገልጋይ ለምን አምስት አልተሰጠኝም ብሎ ያለኩርፊያ በተሰጠው የሚሰራ ነው፤ ባለ አምስቱ አምስት ቢያተርፍ ባለ ሁለቱም ሁለት በማትረፍ ተመሳሳይ ትጋት የታየባቸው አገልጋዮች ናቸው፡፡ ዋጋቸውንም እኩል ነው ያገኙት ለሁለቱም የተሰጠው የክብር ስም አንድ ነው “ገብር ኄር” (ቸር አገልጋይ) የሚል የገቡበትም የክብር ስፍራ አንድ ነው ያም “የጌታቸው ደስታ” ነው  ሁለቱም በጥቂቱ የታመኑ ነበሩ፡፡ ከሰጪውም አንጻር ሲታይ የባለ አምስቱም እንደ ባለ ሁለቱ የባለ ሁለቱም እንደ ባለ አምስቱ ጥቂት ነበር  ሰው በተሰጠው ሳያንጎራጉር ፈጣሪውን ቢያገለግል ክብር ያገኛል ፡፡ ለሰው ልጅ የሚጠውመው ችሎታውን ፣ ጸጋውን መቁጠር ሳይሆን በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ነው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች በእውነት፣ በፍቅር፣ በእምነት የሚያገለግሉ የቤተ ክርስቲያኑን አገልጋዮች ያመለክታሉ፡፡

የሶስተኛው አገልጋይ ባህርይ መልካም ጎኑ ስጦታው  አነሰኝ አለማለቱ ነው፡፡ በርግጥ ስንፍናውን ስለሚያውቅ ይሆናል፡፡ ይህ ሰው ከሥራ ይልቅ በሥራ ጊዜ የሚፈጠረው ችግር ቀድሞ ይታየዋል (የሰነፍ አርቆ አስተዋይ) ሲያተርፍ ሳይሆን ሲከስር ብቻ ይታየዋል፡፡አንዱን ሁለት ሲያደርግ ሳይሆን ያንኑ ያለውን ሲቀማ ያታየዋል፡፡ በጌታው ፊት እንደ ወንድሞቹ አይነቱን ትርፍ ይዞ ቀርቦ ሲሸለም ሳይሆን እይታውም ጠፍቶበት ለጌታው የሚመልሰውን ሲያጣ ይታየዋል፡፡ በመሆኑም ምንም መስራት አልቻለም፡፡ ኪሱንም አላምነው ብሎ መሬት ውስጥ ቆፍሮ ቀበረው፤ ባጠቃላይ በአለማመን የተያዘ ሰው ነው፡፡ በጌታው ፊትም ሲቀርብ በጎ አገልጋዮች ያልተናገሩትን ነው የተናገረው ጨካኝ መሆንክን ስለአወቅሁ ይጠፋብኛል ብዬ ብርህን አስቀምጬልሀለሁ ይኸውልህ ና ውሰድ ነው ያለው ሰነፍ የሚናገረው አያምር ተቀምጦም መአት ከማውራት ዝም አይልም፡፡

ዛሬም ቢሆን ተቀምጠው መአት የሚያወሩ የእግዚአብሔርን ጸጋ የቀበሩ ባስተምርስ መናፍቃን ተከራክረው ቢረቱኝስ? የማውቀውን እውነት ለመስበክ ስጀምር ቢያሳድዱኝስ፣ ክፉዎችን ብዘልፍ ቢያሳስሩኝስ?  በቤተ ክርስቲያን በህዝብ ገበያ በልዩ ልዩ የሥራ ቦታዎች ያሉትን በደለኞች ብቃወምስ፣ ጠላት ሆነው ቢነሱብኝስ ? ለምን ዝም ብዬ ደመወዜን ሳልሰራ አልበላም ብለው የሚኖሩ ስንት አገልጋዮች አሉ፡፡ የዚህ ሰው ችግሩ መክሊቱ አንድ መሆኑ  አይደለም በዚያው አለመስራቱ ነው፡፡ ሁሉም የተሰጠውን ጸጋ አምኖ በመቀበል ሊየገለግል ይገባዋል፡፡ ባለ ሁለቱ በባለ አምስቱ፣ባለ አንዱ በባለ ሁለቱ መቅናት አይገባውም፡፡ ሁሉም ባለ ራዕይ፣ ወንጌላዊ፣ ዘማሪ ፈዋሽ ሊሆን አይችልም፡፡ ለእያንዳንዱ ልዩ ልዩ ጸጋ አለው ሁሉም በጸጋው ቢያገለግል እኩል ዋጋ ያገኛል፡፡

እኛ አሁን ጸጋችን ምንድን ነው ? ጸጋችንን እናውቃለን?  እናገለግልበታለን? መቼም ክርስቲያን ሁሉ የክርስቶስ አንድ አካል ነው፡፡ የስራ ድርሻ የሌለው የአካል ክፍል ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ አንተም አንቺም የክርስቶስ አካል ነህ/ሽ፡፡ ስለዚህ አካሉ ከሆንሽ/ክ ደግሞ ጸጋ አለሽ/ህ፡፡ በመሆኑም እንደ ጸጋችን እናገልግል፤ ጸጋውን እንቀበለው፡፡ ሁሉም በተሰጠው ያገልግል፡፡ ሰባኪው ይስበክ፣ ዘማሪውም ይዘምር፣ ሀብታሙም ይመጽውት፣ ጸሓፊውም ይጻፍ፡፡ አንድ መክሊት እንደተቀበለው እንደ ሀኬተኛው ባርያ ጊዜ አናባክን፡፡ቃሉን በእዝነ ሰማእያን እንዝራው ይበቅልልናል፡፡ ገበሬ እንኳ “ከወፍ አእላፍ አብላኝ” ብሎ በእምነት የተለቀመውን ዘር ወደ ጫካ ጥሎ ምን እንደሚያመርት ያስተምረናል፡፡ ገበሬው የዘራሁት ባይበቅልስ፣ ወፍ ቢበላውስ ብሎ ቢያስብ ኖሮ ባልዘራው ምርትም ባላፈሰ ነበር፡፡

ዛሬም እኛ ቅን አገልጋዮችን በእምነት እምሰላቸው፣ በፍቅር በእምነት እናገልግል፣ ዋጋ እናገኛለን፡፡ እንደ ሰነፉ አገልጋይ ኪሳራችንን ሳይሆን ትርፋችንን፣ ሞታችንን ሳይሆን ህይወታችንን፣ ውርደታችንን ሳይሆን ክብራችንን እያሰብን ልናገለግልበት እንጂ ልንጨነቅበት የተሰጠን አገልግሎት የለምና  ሁላችንም በተሰጠን ጸጋ እንድናገለግል የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማለጅነት አይለየን፡፡

ይቆየን!!       

No comments:

Post a Comment