Monday, March 30, 2015

ከሞት ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ /ክፍል ፩/



እንደምን ሰነበታችሁ ውድ ክርስቲያኖች? . . . እስቲ አንዲት ጥያቄ ልጠይቃችሁ?
ሞትን ታውቁታላችሁ?
እኔማ አሁን ባለፈው ዕለት እንዳጋጣሚ አገኘሁት እና እባክህ ቃለ መጠይቅ ላድርግህ ብዬ ብጠይቀው አሻፈረኝ አለ፡፡ ብለው ብሰራው . . . ወይ ፍንክች!!! "ኧረ ባክህ እንደው ለአጭር ሰዓት ላስቸግርህ?" እሱ መቼ ሰምቶኝ፡፡
በመጨረሻም "በዮሐንስ አፈወርቅ?" ብዬ ስለምነው "ያኔ አስራ ሁለት አመት ገትሮ አቁሞኛል፡፡ አሁን ደግሞ ሃያ አራት ዓመት ያደርግብኝ እንደሆነ መከራ ታሳየኛለህ፡፡" አለና እሺ አለኝ፡፡ እኔም የነገረኝን በማስታወሻዬ ፃፍኩት፡፡ ይኸው አሁን በክፍል በክፍል እንደሚሆን እንደሚሆን አድርጌ ለእናንተ እንደሚከተለው አቀረብኩት . . .

ጥያቄ፡-   ስለትውልድህ እና እድገትህ ብታጫውተኝ?

ሞት፡-    አያቴ ምኞት፣ አባቴ ቃየል፣ እናቴ ደግሞ ኃጢአት ይባላሉ፡፡ የተወለድኩት በ5500 ዓ.ም ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው፡፡ ከዚህ ወዲህ በመላው ዓለም እየተዘዋወርኩ የሰውን ልጅ ከዚህ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ሳጓጉዘው እኖራለሁ፡፡
ጥያቄ፡-   ለመሆኑ ሞት የሚለው ስምህ ትርጉሙ ምንድነው?
ሞት፡-     ትርጉሙ አንድ ብቻ አይደለም፡፡ እንደሰው ማንነት ይለያያል፡፡ ለግንዛቤ ግን ሦስት አይነት ትርጓሜዎችን ልንገርህ፡ - የመጀመሪያው በቅዱሳን ትርጓሜ "መንገድ" ማለት ነው፡፡ መቼም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንደተማርከው አለጠራጠርም፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ" በማለት ተናግሯል፡፡ "መንገድ" ያለኝ እኔን ነው፡፡ ምን ያህል እንዳቀለለኝ ተመልከት፡፡ ለቅዱሳን ከዚህ የመከራ ዓለም ወደሚወዱትና ወደሚወዳቸው አምላካቸው የሚጓዙበት መንገድ ነኝ! በቃ!
           በሁለተኛው ትርጓሜ ደግሞ "መገላገያ" እባላለሁ፡፡ ኑሮ የመረረው፣ አልሳካ ያለው፣ የደዌ ዳኛ፣ የአልጋ ቁራኛ ያሰቃየው "በገላገልከኝ" ይለኛል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች ይህን ከተናገሩኝ በኋላ ስመጣ ይፈሩኛል፡፡
           በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ “መቅጫ” የሚያደርጉኝ አይጠፉም፡፡ የዚህ ዓለም ደስታ፣ ፈንጠዝያ፣ ጭፈራ፣ ርካታ፣ ወዘተ… የማይጠገባቸው፣ አለሌ መለሌ እንደሆኑ መኖር የሚፈልጉ ሰዎች ቀጨኸን፣ ልትቀጨን ነው፣ ቀጨው ሲሉ እሰማቸውለሁ፡፡ ሌላም ሌላም ብዙ ትርጉም አለኝ ብቻ እዚህ ላይ ቢበቃኝ መልካም ነው፡፡
ጥያቄ፡-   ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚገርምህን ብትነግረኝ?
ሞት፡-     ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚገርመኝ ሞኝነቱ ነው፡፡ ተመራመርኩ፣ ዐወቅኩ፣ ጨረቃ ደረስኩ፣ እንደውም አሁን አሁንማ ነፍስ ልሰራ ነው እያለ የሚፎክረው ሰው ራሱን ሳያውቅ ቀርቶ መሞኘቱ ይገርመኛል፡፡ ከአጠገቡ ጓደኛውን  ስወስደው እኔ መኖሬ ትዝ የማይለው፣ በአጥቢያው የጌታ ደም ሲፈተት ልቀበል ብሎ የማያስብ፣ አምላክ እንዳለው የሚረሳ፣ በዓለም ሁሉ ወንጌል እየተሰበከ ሲያልፍ የማይነካው፣ታዲያ እንዲህ ያለ ፍጡር ሞኝ አይደለም? እናናተስ በዚህ ዓለም የምትኖሩት አርባ፣ ሃምሳ፣ ስድሳ ቢበዛ ደግሞ ዘጠና ነው፡፡ እስቲ ከዚህ በኋላ የት እንደምትሄድ ንገረኝ? በዚህ ዓለም የምትኖሩት ጥቂት  በወዲያኛው ዓለም የምትኖሩት ግን እልፍ አእላፍት ወትእልፊት . . . ምኑ ተቆጥሮ? ታዲያ ሰውን ያህል አወቂ ፍጡር ዘመን የማይቆጠርለትን ደስታ ዘመን በሚለወጥለት ጊዜያዊ ነገር ይለወጣል?
           እግዚአብሔር የለም እያለ ሲያሾፍ የነበረውን ስንት ትዕቢተኛ እያጣደፍኩ ወስጄ ለሰማያዊ ፍርድ ሳቀርበው የነበረው ጭንቀትና የነበረው ውጥረት፣ የነበረው ለቅሶ - ኤዲያ ሰው ማለት ማሽላ ነው፡፡ ይስቃል - ያራል( “ራ” - ጠብቃ ትነበብ)፡፡ለምን ትሞኛላችሁ? የፈለጋችሁትን ያህል ተደሰቱ፣ ብሉ፣ ጠጡ፣ አጊጡ፣ ሥልጣን ያዙ፣ ግዙ፣ ንዱ እንጂ ከእኔ እጅ አታመልጡ፣ ጭብጥ ጭብጥብጥ፣ ኩምትር ኩምትርትር አድርጌ አፋፍሼ ስወስዳችሁ በኋላ ቀጭውን እንዳየ ህፃን ልጅ ልትቁለጨለጩ ዛሬ ላይ ምንድነው ኩራቱ፣ ትዕቢቱ?
           አሁን ያ የአማሌቃውያን ንጉሥ አጋግ/1ኛ ሳሙ 15፥32/ እንዲያ ሕዝቡን ሁሉ መከራ ሲያሳይ፣ በእግዚአብሔር ላይ ሲቀልድ ኖረና በእጄ የገባ ጊዜ “በውኑ ሞት እንደዚህ መራራ ነውን?” ብሎ ዐረፈው፤ ፈሪ ሁላ! ቀድማችሁ አትዘጋጁም! ብቻ ብዙ አስለፈለፍከኝ፡፡ የሚገርመኝ ሞኝነታችሁ ነው፡፡
ጥያቄ፡-   ለመሆኑ መኖሪያህ የት ነው?                  
ሞት፡-     የት ይመስልሃል? እንደእናንተ እንደእናንተ እማ ሩቅ ነኝ፡፡ ሞኝ ሁላ! ከጐናችሁ ነኝ፡፡ ካጠገባችሁ ነኝ፡፡ አንዳንዱማ እሬሳ ላይ ወይም መቃብር ላይ ብቻ ያለሁ ይመስለዋል፡፡ አይ ሞኝ! ስትበሉ፣ ስትጠጡ፣ ስትፀልዩ፣ ስትጾሙ እታዘባለሁ፡፡ እኔ ከሰው እርቄ አላውቅም፡፡ እናንተ ግን ትረሱኛላችሁ፡፡ መኖሬም ትዝ ስለማይላችሁ ዘላለም በዚህች ምድር ትኖሩ ይመስል ካለ ሥጋ ፈቃድ ሌላ አይታያችሁም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታሳዝኑኝና በበሽታ፣ በጓደኛ ሞት፣ ወዘተ… አስደነግጣችኋለሁ፡፡ ምን ያደርጋል? “ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ” ነው ወዲያው ትረሱኛላችሁ፡፡ ሰው ሞትን ይረሳል እንጂ ሞት ሰውን አይረሳም፡፡
ጥያቄ፡-   በጣም የተደሰትክባቸው ቀናት ካሉ ብትጠቅስልኝ?
ሞት፡-     አሉ፡፡ እጅግ በጣም፡፡ ቃየል አቤልን ሲገል፣ የሰው ልጅ በኃጢአቱ በንፍር ውሃና በእሳት ተቃጥሎ ሲጠፋ፣ ከእስራኤል በአንድ ቀን ሃያ አራት ሺህ ሰው ሲረግፍ . . . ምኑን ልዘርዝርልህ ያን ቀን እየፈነደቅኩ ሳግዝ ነው የዋልኩት፡፡
ጥያቄ፡-   ዛሬ ዛሬስ በምን ትደሰታለህ?
ሞት፡-     አሁን አሁንማ ከማዝንበት የምደሰትበት ይበዛል፡፡ በኑፋቄና በክህደት ስትያዙ፣ በዝሙት፣ በአሸሼ ገዳሜ፣ በስርቆት ወዘተ… ስትዋጡ ፌሽታ ነው ደስታ፡፡ ብቻ ይህችን ምሥጢር ለማንም ትንፍሽ አትበል፡፡
ጥያቄ፡-   ወገን ወገን አለህ ወይስ አንድ ብቻ ነህ?
ሞት፡-     አለኝ፡፡
ጥያቄ፡-  እስቲ ዘርዝረህ ንገረኝ?
ይቀጥላል . . .
                                                (ይህ ጽሑፍ ከሐምሌ/ነሐሴ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፣ ፭ ዓመት ቁጥር ፬ ሐመር መጽሔት ዕትም ላይ የተወሰደ እና በጥቂቱ ተሻሽሎ የቀረበ ነው፡፡ )