Friday, February 27, 2015

መባከን በመንፈሳዊ አገልግሎት


መንፈሳዊ አገልግሎት ሲባል ሁሌም የምትታወሰው ቤተ-ክርስቲያን ናት፡፡ይህ አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንን ህይወት በእጅጉ የተንተራሰ  ሠፊ የቅድስና መንገድ ነው፡፡ከዚህ ህይወት የምንረዳው አንዱና ትልቁ ነገር የቤተ ክርስቲያን ህይወት የተጋድሎ ህይወት መሆኑን ነው፡፡ይህ ትግልም ለግል ክብርና ዝና ወይም እንደ ህልም ታይቶ ለሚጠፋው ለዚህ ዓለም ሥልጣን እና ምቾት ሳይሆን በስጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ወልድ የገለጠውን የመዳን ምስጢርና እውነት ለመመስከርና ይህን የእውነት ቃል ለሰዎች ለማዳረስ የሚደረግ ተጋድሎ ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ ህይወት ውስጥ ብዙ ተቃራኒዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ማንሳት የፈለግነው ስለተቃራኒ ፈተናዎች ሳይሆን መንፈሳዊ አገልግሎት ራሱ የዲያብሎስ የቅንብር ስራ ሊሆን እንደሚችል እና ብዙዎቻችን በዚህ መንፈሳዊ መሰል አገልግሎት ተጉዘን ፍጻሜያችን ግን ምን ሊሆን እንደሚችል እንመለከታለን፡፡ዲያብሎስ የሰውን ልጆች ከጽድቅ መንገድ ማራቅ የተለመደ ስራው ነው፡፡ የሰው ልጆች ዕለት ዕለት ወደ አምልካቸው ወደ እግዚአብሔር በሚያደርጉት የቅድስና ጉዞ እንቅፋት በመሆንም ሊያገኙት ከነበረው ክብር እና ጸጋ ፈጽሞ እንዲለዩ ያደርጋል፡፡እንግዲህ ይህንን ተግባሩን በተለያዩ መንገዶች እና ስልታዊ በሆኑ ዕቅዶች ያከናውናቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ተስፋ በማስቆረጥ፣ጥርጣሬ በመትከል፣በማዘግየት፣መልካም ምግባራትን
ያለቦታቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ፣ሰለዓለማዊ ክብርና ሞገስ በማሳሰብ እና በሌሎችም እልፍ ምክንያቶች የተጋድሎ ህይወትን ሰዎች እንዳይመርጡ እና እንዳይጓዙባቸው አምርሮ ይዋጋቸዋል፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ግን አገልግሎትን አስመልክቶ የሚያዘጋጀው ፈተና የተለየ ነው፡፡ ይህም ሰዎች ከእግዚአብሔር ከራቁ ሠይጣን እንደሚያሸንፋቸው ስለሚያውቁ ወደ ቤተ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻላል ብለው ስለሚቀርቡ እና እርሱም እንደልቡ ሊያደርጋቸው ስለማይችል ያለው አማራጭ እነርሱ ብቻ ጥሩ አገልጋዮች እንደሆኑና ሹመት ሽልማት ውዳሴ እንደሚገባቸው እያሳሰባቸው ዋጋቸውን እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ በተጨማሪም የበለጠ እንዲያገለግሉ በልቦናቸው እየመጣ ሠፊ አገልግሎት ማገልገል እንዳለባቸው እና ጊዜያቸውን በሙሉ በአገልግሎት ወጥረው እንዲያሳልፉ ምክር ይለግሳቸዋል፡፡ይህም እነርሱ ባላወቁት ነገር ግን እርሱ መልካም አሳቢ መስሎ ፍጻሜውን ለማበላሸት ዘር የሚዘራበት ጊዜ ነው፡፡የሚገርመው ግን ይህንን የሚያደርገው ስለ እኛ መንፈሳዊነት ተጨንቆ ሳይሆን በቀጥታ መጥቶ ቢዋጋን መንፈሳዊነትን እንደማንለቅ ስለሚያውቅ በምንወደው፣ ባልጠበቅነው፣ ክብር እናገኝበታለን ብለን በያዝነው ተግባራችን ያለ አግባቡ ተጠቅመን ዋጋችንን እንድናጣ ማድረግ ስለሚፈልግ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ብዙዎቻችን ስለማገልገላችን እንጂ ምን እና ማንን እንዴት እያገለገልን እንዳለን አናውቅም፡፡ ከዓለም ተለይቶ ቤተ እግዚአብሔር በስራ ማሳለፍ ለእኛ ሠይጣንን ድል መንሻ አድርገን እንቆጥረው ይሆናል፡፡ ነገር ግን አናስተውለውም እንጂ በእንደዚህ አይነት አገልግሎት ስንኖር የጸሎት ህይወታችን፣ የምስጋና፣ መንፈሳዊ ንባባትን የምናነብበት ህይወታችን፣ ከእግዚአብሔር ጋር የምናሳልፈው ጊዜ፣ፆማችን፣ስግደታችን በሙሉ ተዘንግቶናል፡፡ አንዱንም ሳንፈፅም በተለይዩ መንፈሳዊ ሥራዎች ተጠምደን ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኘን የመሰለን ነገር ግን ትክክል በመሰለን ነገር እንድናባክን የታቀደብን የዲያብሎስ ሴራ መሆኑን አናውቅም፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ መንፈሳዊ ስራዎች እጅግ የምንባክን ስንሆን የምንጨብጠውን ስለምናጣ አገልግሎታችን ውጤታማ እና ፍሬ የማይሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ይህም አገልግሎት ወደ ልቦና የሚዘልቅ እና በነፍስ ውስጥ የሚሰርፅ ሊሆን አይችልም፡፡ ለጸሎት፣ዳዊት ለመድገም እና ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ለመሆን ጊዜ እስከሚያጡ ድረስ በማንኛውም ሰዓት በሌሎች ስራዎች በጣም ተወጥረው የሚታዩ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ብዙ ናቸው፡፡እነዚህ ባለፈው እና በመንፈሳዊ ጎተራቸው በነበረው እንጂ አዲስ በሚጨምሩት የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፡፡ህይወታቸው ለጥፋት የተጋለጠ ነው፡፡እዚህ ላይ ዲያብሎሰ የሚዋጋው መንፈሳዊ ስራዎችን ባለመስራት ሳይሆን ጊዜ በማሳጣት ነው ፡፡ከጸሎት፣ከቅዳሴ፣ከዝማሬ፣ከስግደት አያግድም፡፡ እንዲያውም እነዚህን መንፈሳዊ ተግባራት ስለማከናወንና ስለሚገኝባቸውም ጥቅም ስብከት እና ትምህርት እንድንሰጥ ይፈቅድልናል፡፡እኛ ራሳችን እንድናከናውናቸው ግን ጊዜ አይሰጠንም፡፡በዚህም “ደወል ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ይጠራል እርሱ ራሱ ግን አይሄደም” በማለት አባቶች የተናገሩት ምሳሌ በእኛ  ላይ ይፈፀማል ማለት ነው፡፡ ይልቁንም የስራችን ውጤታማ አለመሆን በእኛ ችግር ወይም ምክንያት ነው ብለን እንድናስብ እንኳን ጊዜ አይሰጠንም፡፡የዲያብሎስ ተንኮል ስለሆነ አናስተውለውም ምንአልባት አብረውን የሚያገለግሉ ሰዎች በአገልግሎት ሰዓት ያለመገኘት ስራውን ያበላሸው ይመስለናል፡፡የዲያብሎስ ስራ መሆኑ የሚታወቀው ፍጻሜ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ ከዚያም በአገልግሎት መሰላቸት፣ሰዎችን አሳንሶ መመልከት፣እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብሎ በማሰብ እና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች ራሳችንን ከአገልግሎት ማራቅ ለዚህ ጥሩ መፍትሄ መስሎ ይሰማንና ስራችንን እናቆማለን ከዚያም በዓለም ካለው አህዛብ ብሰን የውጭ ተመልካች እና ወቃሽ እንሆናለን ፡፡ ታዲያ ሠይጣን የሚፈልገውን አገኘ ማለት አይደለም?         

ግን እኮ በትክክል እግዚአብሔርን የማገልገል ዋጋ ፍፃሜው ከቤቱ መጥፋት እና በትዝታ እንዲህ ነበርኩ እከሌ ነበርኩ እያሉ በትዝታ መኖር አይደለም እስከመጨረሻው ጸንቶ በማገልገል በምድር ረድኤተ እግዚአብሔር ሳይለየን ኖረን በሰማይ ደግሞ  የድል አክሊልን ከእግዚአብሔር ለመቀበል ተጋድሎን የምንፈጽምበት ነበር፡፡
ማርታን የተዋጋት የማባከን ውጊያ አሁንም አለ፡፡ይህ ዓለም እስኪያልፍም ይቀጥላል፡፡ መባከኗን ያየ ጌታ ማርታን እንዲህ ነበር ያላት “ማርታ ማርታ በብዙ ተጨነቂያለሽ ትታወኪማለሽ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው” ሉቃ 10÷42፡፡ ስለዚህ በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነትና መንፈሳዊ ህይወታችን ሁልጊዜ የምንባክንባቸው ነገሮች ቁንጮ መሆን አለባቸው፡፡ጊዜያችንን በሰዓት ከፋፍለን ሁሉም ነገር ጊዜውን ጠብቆ ይከናወናል፡፡ ለድኅነታችን እና ለዘለዓለማዊ ህይወታችን ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ እንስጥ፡፡ከዚያ በኋላ ሌላው የፈለገ ጠቃሚ ነገር ቢመስልም እንኳ ሁሉን እንደ አስፈላጊነቱ በቅደም ተከተል ልናደርግ ይገባል፡፡ እዚህ ላይ “ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል”ማቴ 16÷26 የተባለውን ቃል ልናስታውስ ያስፈልጋል፡፡ነፍሳችንን ካጣን ስለነፍሳችን ቤዛ ምን እንሰጣልን? በሞት የተለዩ ወገኖቻችን በዚህ ዓለም ሳሉ በእንደዚህ ዓይነቱ እና መሰል ጉዳዮች መባከናቸው ለምን ጠቀማቸው? እነዚህ ይባክኑባቸው የነበሩ ጉዳዮቻቸውን እርግፍ አድርገው በመሄዳቸው ማን ተጎዳ?  ማንም አልተጎዳም፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለዚህ ዓለም የተናገረው ትክክል ነው፡፡ “እነሆ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ ከፀሐይ በታች ትርፍ አልነበረም” መክ 2÷11

በሌሎች ጉዳዮች ከመባከናችን በፊት ከእግዚአብሔር ጋር መሆን እንጀምር፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን፡፡ ከዚያም እንደ መዝሙረኛው “ አምላኬ አምላኬ በማለዳ ወደአንተ እገሰግሳለሁ፤ነፍሴ አንት ተጠማች”መዝ 62÷1 እንበል፡፡ በመቀጠል ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበትን ጊዜ እንዳይሻሙብን አገልግሎታችንን በመርሐ ግብር እነስቀምጣቸው፡፡ጠዋት ማድረግ ያለብንን መንፈሳዊ ተግባራት ሳናከናውን ወደ ሌላው ስራ አንሂድ ዲያብሎስ አሁን በያዝነውና እንቅፋት በሆነብን ስራ መባከናችን ብቻ ላያረካው ይችላል፡፡ ሌሎች ነገሮችን ወይም  አገልግሎቶችን በመጨመር ግራ ያጋባናልና፡፡እኛ ግን ራሳችንን እንጠብቅ ከሁሉ አባካኝ  ከሆኑ ስራዎች በፊት መንፈሳዊ ጉዳዮቻችንን  እናስቀድም ከሁሉ መንፈሳዊ ስራዎች በፊት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እና መንፈሳዊ ህይወታችንን እናስቀድም ሌላውን እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን እናከናውነው፡፡
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

No comments:

Post a Comment