Tuesday, February 24, 2015

መንፈሳዊት ፍቅር


   ልዑል እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ከልዕልና ወደ ትህትና ወደዚህች ምድር መጥቶ የሰዎች ልጆችን ያዳነበት ምስጢር እጅግ ረቂቅ ጥልቅ ነው፡፡ አምላካችን ለኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠው ክብሩን በውርደት ለውጦ ነው፤ጠላቶቹ ስንሆን ነው የወደደን፡፡እንግዲህ በጥልቅ መንፈሳዊ ስሜት በእውነት ካስተዋልን አምላክ ሰው የመሆኑ ምስጢርና ለቤዛነት የመጣበትን ዓላማ በቃልና በድርጊት የፈፀማቸውን ስራዎች ስናስብ ልባችን በቅንነትና በማስተዋል የተመላ ከሆነ ዘወትር ይህንን ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን ለኛ ያለውን ወደር የማይገኝለትን ፍቅሩን ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡
 
 “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብፅሖ እስከለሞት” ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ
አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው ተብሎ እንደተፃፈ፡፡የሰዎች ልጆችን ከባርነት ወደ ነፃነት፣ከመከራ ወደ ደስታ፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ለመግባት ያስቻላቸው የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደር የማይገኝለት ታላቅ ፍቅሩ ነው፡፡ስደት እና መንገላታት ውረደት እና በጥፊ መመታት፤መናቅ በብረት መቸንከር እነ በጦር መወጋት ለሰባኪው እና ለሰሚዎች፣ለፀሀፊው እና ለአንባቢዎች ቀላል መስሎ ቢታየንም አምላካችን ስለኛ ብዙ መከራ ተቀብሎ ህይወትን ሰጥቶናል፡፡ከፍ ያለው ፍቅሩ በክብደት መለኪያዎች ተመዝኖ ይህን ያህላል አይባልም፡፡ወርድ እና ቁመቱም ግምቱም አይታወቅም፡፡


 ነገር ግን እፁብ እፁብ! ድንቅ! ግሩም ተብሎ ይደነቃል እንጂ፡፡ታላቅ ማስተዋል የነበረው ሐዋርያው ቅስ ዮሐንስ ወልደነጎድጓድ በፈጣሪው ላይ የደረሰውን የዕለተ አርብ መከራ ካየ በኋላ ለ & ዓመታት ልቡ በፈጣሪው ፍቅር ተማርኮ በተሰበረ ህሊና ግሩም በሆነ የፅድቅ ስራ በመኖር እኛም ስለእኛ ፍቅር ሲል የሞተልንን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ታላቅ ፍቅር እያሰብን የሰውን ዘር በመላ እንድንወድ መልእክቱን ያስተላልፍናል፡፡ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘለዓለም ህይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ፡፡እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷልና በዚህ ፍቅሩን አውቀናል፡፡ ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው ወንድሙም የሚያስፈልገውን ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴ ይኖራል ልጆቼ ሆይ በስራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ፡:1 ዮሐ 3÷15-18 ይላል፡፡

ከዚህም የምንረዳው ቁም ነገር ፈጣሪያችን ስለእኛ ፍቅር ከሞተልን እኛም የሰውን ዘር በመላው መውደድ እንዲሁም ስለወንድሞቻችን መሞት እንደሚገባን ነው፡፡  ኃይለ ቃሉ ከእኛ ህይወት ጋር ሲነፃፀር በእርግጥ እኛ የክርስትና ዓላማ ገብቶናል ወይ? ሁላችንም ልንመልሰው የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ጥላቻ ኃጢአት ነው ነገር ግን የስንቶቻችን ልብ በጥላቻ ተመርዞ ተጎድቷል እንግዲህ በቅዱስ ወንጌል አንፃር በመንፈሳዊት ፍቅር መለኪያ ስንመዘን ቀለን እንዳንገኝ ስለሰው ዘር በመላው ያለዉ ሃሳባችን መልካም ቢሆን ዋጋችን በሰማያት ታላቅ ይሆናል፡፡  መንፈሳዊት ፍቅር በሁለት ትከፈላለች፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ቢጽ፡፡ ፍቅረ እግዚአብሔር በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግበንና ጤንነት ፣ በረከትና ሕይወት ያለ ዋጋ ያደለንን ከሁሉም በላይ ደግሞ በዕለተ ዓርብ ስለኛ ሲል ስጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ የሰጠንን አምላካችንን መውደድም ሕጉን በመፈፀም በፆም እና በፀሎት ስግደትና ምጽዋት ጸንቶ መኖር ነው፡፡ ፍቅረቢጽ ደግሞ በተፈጥሮ የሚመስሉንን የዓለም ሕዝቦች በመላው ነጭ፣ጥቁር፣እስላም፣ክርስቲያን፣የሚያምን፣ የማያምን፣የተማረ፣ያልተማረ፣ድሃ፣ባለጸጋ ሳይለዩ መውደድ ነው፡፡ዛሬ ከአለም ዓቀፍ ሁኔታዎች ጀምረን በእያንዳንዱ ሀገር ወደታች ዝቅ ብሎ በየቀዬው በየመንደሩ  የብዙዎች ደም ሲፈስ አጥንት ሲከሰከስ የምናየው መንሳዊት ፍቅር በመጥፋቷ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ግን ከቃል ይልቅ በተግባር ፈጣሪያቸውን መምሰል እንደሚገባቸው ዘወትር መታወስ አለበት፡፡

ፍቅር የሰውን ዘር በመላው መውደድ ነው ሰውን መውደድ በቃላት ብቻ ሳይሆን በድርጊት መገለጽ ያለበት ተግባር በመሆኑ ዛሬ በዓለማችን ላይ ላለው ችግር ጦርነት፣መድኃኒኒት ላልተገኘለት በሽታ፣ረሃብ፣ስደት፣ዕልቂት ፈጣሪያችን መፍትሔ እንዲሰጥ በብርቱ መጮኽ ይገባል፡፡ ከልብ በመነጨ ስሜት ወደ ፈጣሪያችን ከጮኽን አምላካችን መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግስት ሊመልስልን ይችላልና ይልቁንም ይህ የምንገኝበት ወራት አምለካችን ለይቅርታ የመጣበት በመሆኑ ጨርቅ ላነሳቸው ወራት ለባሳቸው ወገኖቻችን እጃችንን መዘርጋት ይጠበቅብናል ይህ ስለሰው ዘር ያለንን መልካም ስሜትና ርኅራኄ ይገለፃል፡፡ እስኪ የተቸገሩትን መደገፍና መርዳት ከአካባቢያችን እንጀምር፡፡  አገልግሎቱ እያደገ ሲሄድ ነፍስ  የመድሀኒታችንን ፈለግ በመከተል አምስት እንጀራ አበርክቶ አምስት ሺ ሰዎች የመገበውን የፈጣሪዋን አርአያ በመመልከት በተሰጣት ሥልጣን በፀሎትና በሱባኤ ትምህርትና ተአምራት በመታገዝ ለተራቡ ምግብ መስጠት፣ ለድሆች ማደሪያ በመስራት፣ እናትና አባት ለልጆቻቸው የሚፈፅሙትን ተግባር ማከናወን እንዳለባት ዘወትር መታወስ ይኖርበበታል፡፡

በዘመናችን በአብያተ ክርስቲያናቱ የሚደረገው ራስን የመርዳት የልማት እቅስቃሴ ቤተክርስቲያናችን ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረት አስፈላጊ ተገቢ ስራ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ከዚሁ ጎን መታሰብ ያለበት ጉዳይ ደግሞ ትኩረት ሊሰጠው አግባብ ነው፡፡ይኸውም ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ሰብስቦ ቀለብ መስፈርና ማደሪያ መስጠት እንዲሁም ማስተማር ከልማት ሁሉ የሚበልጥ ታልቅ ልማት ነው፡፡ ረጂ እና ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንና አረጋውያትም እንዲሁም ለአካለ ስንኩላን ማሰብ የቅድስት ቤተክርስቲያን ድርሻ ነው፡፡እንግዲህ መንፈሳዊት ፍቅር ምልክቷ ይህ ነውና ምዕመናንና የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አገልጋዮች ለዚህ የተቀደሰስ ስራ እንተባበር፡፡
                                        አምላካችን በቸርነቱ ለብርሃነ ትንሣኤው ድርሰን፡፡