Friday, February 27, 2015

አባ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ



አባ ሳሙኤል የታላቁ ርዕሰ መነኮሳት የአባ እንጦንስ ተከታይ የደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም መሥራች፣ በ፲፬ኛው ምዕተ ዓመት ይኖሩ የነበሩ፣ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ አባ ሳሙኤል የመሰረቱት ገዳም ደብረ ሃሌ ሉያ፤ በክብሩ ከደብረ ሲናና ከደብረ ዘይት የማያንስ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ስለ አባ ሳሙኤል ገድላቸው እንዲህ ይተርክላቸዋል፡፡
ስሟ መርታ በተባለች ሀገር የሚኖሩ፣ ሕገ እግዚአብሔርን እንደ ኖኅ እንደ አብርሃም የጠበቁ፣ በትውልድም የቡሩካን የደጋግ ሰዎች ወገን የሆኑ ስማቸው ይስሐቅ ለነ እግዚእ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህም ሰው ቅድስትነ ማርያም የምትባል ሴት በሕግ አገቡ፤ እርሷም እንደ ሃና እንደ ኤልሳቤጥ እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ ለድሃ የምትራራና በሁሉ ዘንድ የተወደደች ነበረች፡፡ በትውልድም የክቡራን ወገን ነበረች፤ ሙት የሚያስነሱ ድውያን የሚፈውሱ አቡነ ዓቢየ እግዚእ የተባሉ ጻድቅ ወንድም ነበሯት፡፡ ልጅ እንደፀነሰችም ባወቀች ጊዜ፤ ቡራኬ ለመቀበል ወደ እርሳቸው ለመሄድ መንገድ ጀመረች፡፡ እዚያም በደረሰች ጊዜ አቡነ ዓቢየ እግዚእ ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ሳሉ፣ እህታቸው ስትመጣ ስላዩአት፤ አጠገባቸው ከመድረሷ አስቀድሞ ግንባራቸውን መሬት አስነክተው ሰገዱላት፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህን በማየታቸው በመደነቅ "አባታችን ለዚህች ሴት በምን ምክነያት ሰገዱላት?" በማለት ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም "ልጆቼ ሆይ ለእርሷ የሰገድኩ አይምሰላችሁ፤ እኔ የሰገድኩት በብርሃኑ ምድረ ኢትዮጲያን ለሚያበራት፣ ዕንቁ ባሕርይ ለሆነ በማኅፀንዋ ላለው ልጅ ነው፡፡ እሱም በጸሎቱ የሚጠብቅ፣ በትሩፋቱ የሚያፀድቅ፣ በትምህርቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕዝብ የሚያድን፣ የኔንም ስም የሚያስጠራ ነው" የሚል ቃለ ትንቢት መለሱላቸው፡፡

አቡነ ዓቢየ እግዚእ በራዕያቸው ያዩት፣ በቃላቸው የተናገሩት ሁሉ ይደርስ ይደረግ ነበርና፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገራቸውን ሰምተው ቃላቸው እርግጠኛ መሆኑን አመኑ፡፡ ከዚህም ትንቢታዊ ንግግራቸው ቀጥሎ፤ ከእህታቸው ጋር እስኪነጋገሩ ድረስ ቆይታ ያደርጉ ዘንድ ደቀ መዛሙርቶቻቸውን አዘዟቸው፡፡ እህታቸውም "አባቴ ሆይ አንዲት ነገር ልጠይቅዎት፣ ፈቃድዎ ይሁንልኝ" በማለት ልመናዋን አቀረበች፡፡ እርሳቸውም "ነገሩ ምንድነው?" በማለት እንድትጠይቃቸው ፈቃድ ሰጧት፡፡ እርሷም "አባቴ ሆይ ወደ እርስዎ ስመጣ ባዩኝ ጊዜ ለምን ሰገዱልኝ?" ብላ ጠየቀቻቸው፡፡ እርሳቸውም አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቶቻቸው እንደነገሯቸው "የሰገድኩት ለአንቺ አይደለም፤ ነገር ግን እንደ ዕንቁ ፈርጽ ለሚያበራ፤ በማኅፀንሽ ላለው ልጅ ነው፡፡ አንቺም እግዚአብሔርን ደስ ከማያሰኙ ከማናቸውም ነገሮች ከርኩሱም ነገር ሁሉ ተጠበቂ ከአንቺ የሚወለደው ልጅ እግዚአብሔር የመረጠው ቅዱስ ነውና፡፡ ተጠንቅቃችሁ አሳድጉት" ብላው መከሯት፡፡ እርሷም "አባቴ ሆይ በረከትዎን የሳድሩብኝ ያዘዙኝን ሁሉ ለማድረግ እንድችል ይጸልዩልኝ" በማለት ቡራኬ ተቀብላ ወደ ሀገሯ ተመለሰች፡፡ ይህ የተነገረው ትንቢትም ጊዜው ሲደርስ ተፈፀመና መልኩ እንደፀሐይ የሚያበራ ልጅ ተወለደ፡፡ በመወለዱም እናት አባቱ እንዲሁም ዘመዶቹ ሁሉ ተደስተው ስሙን ነአኩቶ ለአብ ብለው ሰየሙት፡፡ በመልካም አስተዳደግም አሳደጉት፡፡ ጥቂት ከፍ ብሎም ለትምህርት በደረሰ ጊዜ አባትና እናቱም ወስደው ለእናቱ ወንድም ለአቡነ ዓቢየ እግዚእ ሰጡት፡፡

አቡነ ዓቢየ እግዚእም ሐዋርያት በሲኖዶስ "ልጆቻችሁን ጽሕፈት፣ ድጉሰት፣ አንብቦተ መጻሕፍትን አስተምሯቸው" እንዳሉ በተጨማሪም ሲራክ "ልጅህን አስተምረው በመከራህ ጊዜ ይረዳሃል፤ ልጁን የሚያስተምር ሰውነቱን ያሳርፋል" እንዳለ በማሰብ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን በምክርና በተግሣጽ አስተማሩት፡፡ በግብረ መላእክትም አሳደጉት፤ ወዲያውም "ሥራ መፍታት ስንፍና እና ክፉ ሃሳብን ታስተምራለች" ያለውን መንፈሳዊ ቃል ስለሚያውቁ ተግባረ ዕድን አለማመዱት፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን ማዘውተርን፣ ሕይወተ ሥጋን ሕይወተ ነፍስን የሚሰጠውን ሥጋ ወደሙን መቀበልን፣ አርምሞንና ትዕግስትን ዘወትር እንዲፈጽም ይመክሩት ነበር፡፡
 
አቡነ ዓቢየ እግዚእም ሐዋርያት በሲኖዶስ "ልጆቻችሁን ጽሕፈት፣ ድጉሰት፣ አንብቦተ መጻሕፍትን አስተምሯቸው" እንዳሉ በተጨማሪም ሲራክ "ልጅህን አስተምረው በመከራህ ጊዜ ይረዳሃል፤ ልጁን የሚያስተምር ሰውነቱን ያሳርፋል" እንዳለ በማሰብ መጻሕፍተ ብሉያትንና ሐዲሳትን በምክርና በተግሣጽ አስተማሩት፡፡ በግብረ መላእክትም አሳደጉት፤ ወዲያውም "ሥራ መፍታት ስንፍና እና ክፉ ሃሳብን ታስተምራለች" ያለውን መንፈሳዊ ቃል ስለሚያውቁ ተግባረ ዕድን አለማመዱት፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያን ማዘውተርን፣ ሕይወተ ሥጋን ሕይወተ ነፍስን የሚሰጠውን ሥጋ ወደሙን መቀበልን፣ አርምሞንና ትዕግስትን ዘወትር እንዲፈጽም ይመክሩት ነበር፡፡

ነአኩቶ ለአብም ተምሮ እውቀቱን ሁሉ ካመዛዘነ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ተጎብኝቶ በገዳም በዱርና በገደል ከሰይጣን ጋር የሚዋጉትን የቅዱሳንን ገድል ይመለከት ጀመር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ያገኘውንም የሰማዕታትንም ገድል እያነበበ ያዝንና ይተክዝ ያለቅስም ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በዜና የሰማቸውን ጻድቃን እንደምን እንደተጋደሉ በሕሊናው እየመረመረ ልቡናው በፍቅረ ምንኩስና ከመቃጠሉ በላይ ከአቡነ ዓቢየ እግዚእ ለመለየት ያስብ ጀመር፡፡ ነገር ግን በአባትነታቸው እንዳይረግሙት ስለፈራ አልቻለም፡፡ አቡነ ዓቢየ እግዚእም ነአኩቶ ለአብ የመሄድ ሐሳብ እንደተነሳሳበት በጸጋ እግዚአብሔር ስለተገለጠላቸው፤ ጠርተው "ምሥራቅና ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ የእግዚአብሔር ርስቱና ጉልቱ ግዛተም ናቸው የተባለውን አታውቅምን? አሁንም ታገስ እንጂ ከኔ መለየቱን አትውደድ ከዚሁም ሳለህም እግዚአብሔር ይቅር ይለናል" በማለት መከሩት፡፡ ነአኩቶ ለአብም "አባቴ ሆይ ምሥጢሬን ካወቁልኝ አሳቤን ገልጬ ልንገርዎት፤ ይረግሙኛል ብዬ ስለፈራሁ ነው እንጂ ከዚህ ስፍራ አንዲት ሌሊት እንኳን ለማደር አልፈልግም ነበር፤ አሁን ግን በፍቅር አሰናብተውኝ እንድሄድ እዚህም ተቀመጥ ብለው እንዳይማልዱኝ እለምንዎታለሁ" አላቸው፡፡ "ለዚህም የተነሳሳሁት በተወለድኩበት ሀገር፣ በእናት በአባቴ በዘመዶቼም መካከል ተቀምጬ ለመጽደቅ እንደማልችል አስብ ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐሰት በማይገኝበት ቃሉ "አባቱንና እናቱን፣ ሚስቱንና ልጆቹን፣ ቤቱንና ንብረቱን ስለእኔ ያልተወ ለእኔ ሊሆን ሊከተለኝ አይገባውም" ያለውን እንዲሁም "ለሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ቢገዛ፣ ምን ይረባዋል፤ ነፍሱንስ ካጠፋ ካጎደለ" ከማለቱ አስቀድሞ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር ፳፬ "ነፍሱን የወደደ ያጠፋታል፣ ነፍሱን ስለእኔ ያጠፋት ያድናታል" ብሎ የተናገረው ቃለ ምዕዳን ትዝ ይለኛልና ስለዚህ ነው" ብሎ መለሰላቸው፡፡(ማቴ ፲፥፴፯ ሉቃ ፱፥፳፭) አቡነ ዓቢየ እግዚእም ይህንን ንግግሩን ከሰሙ በኋላ ዝም ብለው በማድነቅ ብዙ ሰዓት ቆዩ፤ የሚናገረውም በላዩ አድሮ ያለው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ተረዱና ከዚያ ወዲያ ምንም ቃል አልመለሱለትም፡፡ ነገር ግን "ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ሐዋርያትን በአንብሮተ ዕድ እንደባረካቸው እኔም እጄን ከራስህ በላይ አኑሬ እባርክሃለሁና ራስህን ዘንበል አድርግ" አሉት፡፡ (ሉቃ ፳፬፥፶)
ነአኩቶ ለአብም የአባቱን ጉልበት ይዞ ከፊታቸው ተንበረከረከ፤ አቡነ ዓቢየ እግዚእም ቡራኬአቸውንና ምርቃታቸውን እንደሚከተለው ጀመሩ፡፡ "እንደ ቅዱስ አባታችን እንደ እንጦንስ፣ እንደ መቃርስ ስምህ በአፅናፈ ዓለም የተጠራ ይሁን፤ ኃላፊውን ዓለም ጠልተው እንደመነኑ እንደንጹሐን የቀደሙ መነኮሳት ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃህ" በማለት መረቁትና ተሰናበተ፡፡ ይህንንም ቡራኬና ምርቃት እንደልብስ ተጎናፅፎ ትምህርቱን ገና አልጨረሰምና ዜና ቅዱሳንን እየመረመረ፤ ገዳማትን እየጠየቀ መንገዱን ጀመረ፡፡
እንዲህ እያደረገ ሲሄድ ሥርዓተ ማኅበርና የአንድነት ኑሮ ያለበትን የአቡን እንጦንስን ገዳም ዜና ስለሰማ፤ ብዙ ምርኮ እንዳገኘ አርበኛ ደስ አለውና ዘለለ፡፡ ምክነያቱ ደግሞ በዚያም ጊዜ ገዳማቱ አልፎ አልፎ መነኮሳቱም ጥቂት ነበሩና ነው፡፡ ነአኩቶ ለአብን መንፈስ ቅዱስ እየመራው አባ እንጦንስ ካሉበት ገዳም ደረሰ፡፡ መነኮሳቱን "አባታችን ያሉበት በዓት የትኛው ነው?" ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም "አባታችንን የምትሻው ለምንድን ነው?" ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ "ልዩ ኑዛዜ ስላለብኝ ሰውነቴን ላስመረምር እፈልጋለሁ ንገሩኝ" አላቸው፡፡ እነሱም ለአባ እንጦንስ ከነገሩለት በኋላ በገባ ጊዜ አባ እንጦንስ መንፈስ ቅዱስ እንዳደረበት በማወቃቸው አመጣቱ ስለምን እንደሆነ ጠየቁት፡፡ ነአኩቶ ለአብም "አባቴ ሆይ ያመነኩሱኝ ዘንድ መጥቼአለሁ" ብሎ ስለመለሰላቸው አባ እንጦንስ "ሸክሙ የከበደ የምንኩስናን ቀንበር ለመሸከም ትችላለህን?" አሉት፡፡ "አባቴ ኃይለ ጸሎቶ፣ ሀብተ ንጽሕናዎ ይርዳኝ" አላቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም አመጣጡ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ ያውቁ ነበርና እሽ ምን ከፋኝ ብለው ወንድሞች ከገዳም የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ግራና ቀኝ ተበትነዋል እስኪሰበሰቡ ጥቂት ቆይ አሉት፡፡

ወንድሞችም ከሄዱበት ከገቡ በኋላ ዕለቱ ታላቅ በዓል አጋጥሞት ነበርና አባታችን ደውል ደውሉ ብለው አዘዙ፡፡ ደውሉ ከተደወለ በኋላ ቅዱሳን መነኮሳት ተሰብስበው የሥርዓተ ምንኩሳና መጽሐፍ እንደሚያዘው ቆቡን ከመንበረ ታቦት ፊት ለፊት ነአኩቶ ለአብን በመካከላቸው አድርገው ሥርዓተ ምንኩስናን አደረሱለት፡፡ ከዚያም አቡነ እንጦንስ ቆቡን ባርከው ሲያመነኩሱት ስማቸውን ሳሙኤል ብለው ሰየሟቸው፡፡
ከዚህ በኋላ አቡነ እንጦንስ አቡነ ሳሙኤልን "ልጄ ሆይ ስሜ በአንተ ይጠራ" ብለው ቃለ ትንቢት ከተናገሯቸው በኋላ ከወንድሞች ጋር እንዲያገለግሉ መከሯቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በሚልኳቸው መልእክት እንደ ንስር ፈጣን ቅን ሆነው ከአበው ጋር በሥራ ይውላሉ፡፡ በመሸ ጊዜ ግን ወደ ወንዝ ወርደው ታላቅ ድንጋይ በራሳቸው ተሸክመው መዝሙረ ዳዊት እየደገሙ እንባቸውን እንደውሃ እያፈሰሱ እወንዝ ከማደራቸው በላይ ልብሳቸው ማቅ ሲሆን ደማቸው ወደ መሬት እስኪፈስ ሰውነታቸውን በድርብ ገመድ ይገርፉ ነበር፡፡ በሠጊድም እንደ ሠረገላ መንኩራኩር ከመስገዳቸው ጋር ረሃብና ፅምዕን ይታገሱ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ በምንኩስናቸው መጀመሪያ በፍቅር በስምምነት ስለሚያገለግሉ ከሰውም ወገን ደገኛ በመሆናቸው መነኮሳት መልአክ ነውን? ወይስ እንደኛው ሰው ነው? ይባባሉ ጀመር፡፡
ከጥቂት ቀንም በኋላ መነኮሳቱ ተሰብስበው ወደ አቡነ እንጦንስ ሄደው "አባታችን አቡነ ሳሙኤል በሁለት ወገን ሥጋቸው አለቀ ቀን ከእኛ ጋር በሥራ ይውላሉ ሌሊት በልዩ ልዩ የገድል ፈተና ሲፈተኑ ያድራሉ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በሌሊት ብቻ እንዲወሰኑ የነገራቸው" አሏቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም ቃላቸውን ተቀብለው ወዲያው አቡነ ሳሙኤልን አስጠርተው "ልጄ ሆይ እስከዛሬ ባደረኸው አገልግሎት ደስ አሰኝተኸናልና የድካምህን ፍሬ እግዚአብሔር የቀበልልህ እንግዲህ ወዲህ ግን በጸሎት ተወስነህ ኑር ዳዊት ድገም በዚህ ምክር ወንድሞችህ ሁሉ ተስማምተውበታል" በማለት ገለጹላቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም "አንድም ሥራ ሳልሠራ ለዚህ ማዕረግ ሳልበቃ ለምን እንዲህ ይሉኛል? አሁንም ፈቃድዎ ይሁንልኝና ሥጋዬን እያደከምኩ ልኑር፤ ይህም ባይሆን ስለኃጢአቴ አለቅስ ዘንድ አሰናብቱኝ፤ ወደ ሌላ ገዳም ልሂድ፡፡ አባታችን ጸሎት ያለሥራ ከንቱ ድካም ነው፤ የተባለውን ቃል አበው ይዘነጉታል?" ብለው መለሱላቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም ልጄ ሆይ ይህን ትተህ ቃሌን ስም ስላሏቸው እንዳይዝኑባቸው ፈርተው ቃላቸውን በመቀበል በጸሎት ተወሰኑ፡፡ ተልእኮአቸውንም ስላስተዋቸው በረሃብ፣ በፅም፣ የሚወዱትን ሁሉ በመተው ሰውነታቸውን አደከሙ፡፡
መነኮሳቱም ወደ አቡነ እንጦንስ ሄደው "አቡነ ሳሙኤል ሰውነታቸውን በገድል አለቀ፣ የሚሰሙ ከሆነ ይምከሯቸው" ሲሉ ለሁለተኛ ጊዜ ነገሯቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም ይህንን በሰሙ ጊዜ ደንግጠው "እንግዲህ ምን ላድርግ? ተልእኮውን ማስተዌ ከመከራው ጥቂት እንዲያርፍ ብዬ ነበር፤ እንሆ ከቀድሞው ይልቅ ገድሉ በዛ፤ ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች አያርፍም" በማለት እያዘኑና እየተከዙ ወደ አባ ሳሙኤል በአት ገቡ፡፡ አባ ሳሙኤልን ባዩአቸው ጊዜ፤ ሰውነታቸው ደርቆ፣ ጉሮሮአቸው ተዘግቶ፣ አገኟቸውን "ልጄ ሆይ መጻሕፍት አዋቂ ስትሆን ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? የጦር ዕቃህን በአንድ ጊዜ አትጨርሰው ያለውን ቃለ-አበው ልብ አታደርግምን?" ብለው መከሯቸው፡፡    
አቡነ ሳሙኤልም "እኔ ሥራ ፈት ነኝ፤ ምን በጎ ሠራሁ? ገና እስከ ዛሬ ድረስ እዳዬን አልከፈልኩምና፤ አባቴ ሆይ ከዚህ በፊት እንደነገርኩዎ አሁንም ዘመኔ በከንቱ ሳያልፍ ወደ ሌላ ገዳም እንድሄድ ያሰናብቱኝ" አሏቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም "ከኔ መለየት ፈቃድህ ከሆነ የምትሄድበትን ገዳም ላሳይህ" ብለው፤ ጣታቸውን በመዘርጋት ስሟ ደብረ ሃሌ ሉያ የምትባል ተራራ አመለከቷቸው፡፡ ዕድል ፈንታቸው እንደሆነች አወቋትና "ከዚያች ተቀመጥ ነገር ግን የቀጠሮ ቀን እስኪፈጸም ጥቂት እንድታነጋግረኝ እወዳለሁ" አሏቸው፡፡ የአቡነ እንጦንስ ትንቢታቸው የታወቀ የተረዳ ነበርና፤ በአፅባዕትየ በስቶ ሥራዬ በምትባል ሀገር ሳሉ፤ ደቀ መዛሙርቶቻቸውን "ልጆቼ ሆይ ታላቅ ምሥጢር ያለባትን ያችን የምታስፈራ ተራራ ታዩአታላችሁን" አሏቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውንም "አባታችን ሆይ ስሟ ማን ይባላል? ሰውስ ይኖርባታልን?" በማለት ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም "ስሟ ደብረ ሃሌ ሉያ ይባላል፡፡ ዛሬ ከአራዊት በቀር ሰው የለባትም ምድረ በዳ ነች፡፡ የተፈቀደለት ሰው በተራራዋ መኖር ከጀመረ በኋላ እንደ ንሥር የሚበሩ፣ እንደ መላእክት ምስጋና የማያቋርጡ፣ እንደ ሠረገላ መንኩራኩር የሚሰግዱ፣ አንበሳንና ዘንዶን የሚጫሙ፣ ዝናቸው ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የሚሰማላቸው ቅዱሳን መነኮሳት ይሰበሰቡባታል፡፡ እኔም በውስጧ እቀበራለሁ፤ ይህቺም ታሪኳ እንደ ደብረ ቁስቋም፣ ደብረ ዘይት፣ ደብረ ሲና፣ እንደ ደብረ ታቦር የተጠራ ይሆናል፡፡ ከኢትዩጵያ ተራሮችም የሚመስላትና የሚተካከላት የለም፡፡ ልብሰ መንግሥት የለበሱ ነገሥታትና መኳንንት ደጅ ይጠኑታል" በማለት ገለጹላቸው፡፡ አቡነ እንጦንስም ይህን ትንቢት የተናገሩት ገና ከአቡነ ሳሙኤል ጋር ሳይገናኙ ከብዙ ዓመታት በፊት ነበር፡
  

ከዚህ በኋላ አቡነ ሳሙኤል ከአቡነ እንጦንስ ቡራኬ ተቀብለው ወደ አሳዩአቸው ተራራ ወደ ደብረ ሃሌ ሉያ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ጥቂትም እልፍ እንዳሉ ምድረ በዳ በመሆኑ መንገድ ጠፋባቸው፡፡ ከልዑል እግዚአብሔር የታዘዘ መልኩ እንደ በረድ ነጭ የሆነ አንበሳ በቀኛቸው በኩል መጥቶ፤ መንገዱን እየጠረገና እየመራ ከዚያች ተራራ አደረሳቸውና ተሰወረ፡፡ ከዚያም በኋላ አንበሳው የደረሰበትን ለማወቅ አልቻሉም፡፡ እርሳቸው ግን ከዚህ ተራራ ላይ ሆነው ቸርነቱን ከእኔ ያላራቀ አምላኬና ፈጣርዬ ይክበር ይመስግን እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ፡፡ በተራራው ላይ እየተዘዋወሩ፣ ጤዛ ለብሰው ድንጋይ ተንተርሰው በመኖር ከዚህም ላይ በጾምና በጸሎት በማያቋረጥ ምስጋና ፈጣረያቸውን ያገለግሉ ነበር፡፡ በጾምና በጸሎት በትሕርምት ተወስነው ሳሉ አቡነ እንጦንስ ክፉና በጎ ያለየ ህፃን አስከትለው ሊጎበኟቸው መጡ፡፡ አቡነ ሳሙኤልም አባ እንጦንስን ባዩአቸው ጊዜ ከመሬት ወድቀው እጅ ከነሱአቸው በኋላ አንገት ለአንገት ተናንቀው ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የቅዱሳንን ገድል ተጨዋወቱ፡፡ አቡነ እንጦንስም ልጄ ሆይ በረሃብና በጾም፣ በሌሊት ቁርና በመዓልት ሐሩር እየደከምክ ነውና፤ እንጨት እየሰበረ ውሃ እየቀዳ ይረዳህ ዘንድ ይህንን ሕፃን ልተውለህ አሏቸው፡፡ ልጁም በኋላ አባ ገብረ መስቀል የተባለው ነው፡፡ አባ ሳሙኤልም ልጁን ለእርዳታ የምፈልገው አይደለሁም፤ ዳሩ ግን ጸጋ እግዚአብሔር እንዳደረበት አያለሁና ቢቀር ፈቃዴ ነው አሏቸው፡፡ ይህንን ከተናገሩ በኋላ አቡነ እንጦንስ ለሁለቱም ቡራኬ ሰጥተው ተሰነባብተው ተለያዩ፡፡
አቡነ ሳሙኤልም ይህንን የተውላቸውን ሕፃን በመንፈሳዊ ጥበብ ያሳድጉ ጀመር፡፡ ከዕለታት በአንደኛው ቀን ለምግባቸው የሰበሰቡት የእንጨት ፍሬ በማለቁ ለመልቀም ሲሄዱ ስለልጁ እንዲህ የሚል ሐሳብ ያዛቸው፡፡ ከዚህ ብቻውን ብተወው አራዊት ያይና ይፈራል፣ ይዤው እንዳልሄድ ከመንገድ ይደክምና ያስቸግረኛል በማለት በሃሳባቸው ካወጡ እና ካወረዱ በኋላ፤ በቁመቱ ልክ ጉድጓድ ምሰው ሕፃኑን ከጉድጓዱ ውስጥ አግብተው በላዩ ሳር ነሰነሱና እስክመጣ በዚህ ቆየኝ ብለው ወደ ሥራቸው ሄዱ፡፡ ከዚያም የእንጨት ፍሬ ሲለቅሙ ከበረሃም እሳት ተነሳና ጫካውን ያቃጥለው ጀመር፡፡ እርሳቸውም እሳቱ ወደ በዓታቸው መድረሱን አውቀው ስለልጁ ተጨነቁ፡፡  ወዲያው በሃሳባቸው ብሮጥ ስፍራው እሩቅ ስለሆነ እሳቱ ይቀድመኛል፤ ልጁን ላድነው አልችልም ስለዚህ ከዚህ ሆኜ ወደ ፈጣሪዬ ላመልክት አሉና፤ አናንያን፣ አዛርያን፣ ሚሳኤልን ከባቢሎን እሳት ያዳንኻቸው አንተ ነህና ዛሬ ይህን ለአገልግሎት የተጠመደውን ልጅ አድነው በማለት ጸለዩ፡፡ ከስፍራውም ሲደርሱ አካባቢው ተቀጣጥሎ አመድ ሲሆን ልጁ ምንም ሳይሆን አገኙት፡፡ በዚህ ሁሉ የሚቻልህና የሚሳንህ ለሌለ ለአንተ በእውነት ምስጋና አቀርባለሁ እያሉ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ፡፡ እንደዚህ በገድል እና ተአምራት ከቆዩ በኋላ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ከአምላካቸው ጥሪ በደረሳቸው ጊዜ፤ በክብር አረፉና በዚሁ ገዳም ተቀበሩ፡፡ ይኸውም ገድላቸው በገድለ ዜና ማርቆስ ተጽፎ ይገኛል፡፡

የአባታችን ረድኤታቸውና በረከታቸው፤ የፈጣሪያችን  ቸርነት አይለየን፡፡ አሜን

No comments:

Post a Comment