Tuesday, February 17, 2015

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሱዳን ካርቱም ያደረጉትን ሐዋርያዊ የሥራ ጉብኝት አጠናቀው ተመለሱ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሱዳን ከምትገኘው የኢትዮጵያ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቷ ልዑካንና ሊቃነ ጳጳሳትን አስከትለው በሱዳን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቀው የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ በሱዳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የተገነቡ የሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያና የከፍተኛ ኪሊኒክ ሕንፃዎች መርቀው ሥራ ለማስጀመርና ወደፊት ለሚሠሩት ሁለት ታላላቅ ህንፃዎች የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጥር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሱዳን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በሱዳን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዘምራንና ምእመናን በከፍተኛ የአቀባበል ሥርዓት ተቀብለዋቸዋል፡፡




በማግሥቱ እሑድ የካቲት 1ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት የቅዳሴውን ሥርዓት ከመሩ በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ የሱዳን መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ ሠራተኞችና የሃይማኖት መሪዎች በተገኙበት ግንባታቸው የተጠናቀቁትን ሁለቱንም ሕንፃዎች መርቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን አድርገዋል፡፡ አንዱ ሕንፃ ለተለያየ መንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ሱዳን የሚላኩ ሊቃነ ጳጳሳት የሚያርፉበት ሲሆን ሁለተኛው ለሕብረተሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጥ ትልቅ የክሊኒክ ሕንፃ ነው፡፡ ለወደፊት ለሚሠሩ ሁለት ታላላቅ ሕንፃዎችም ቅዱስ ፓትርያርኩ ከክቡር አምባሳደር አቶ አባዲ ዘሙ ጋር በመሆን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

በሕንፃ ምርቃቱ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ ጎበና ስለ ሕንፃዎቹ አጠቃላይ የሥራ ሁኔታና ስለ ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የሥራ ፍላጎት ሰፊ ገለፃ ከሰጡ በኋላ የሰበካ ጉባኤው አጠቃላይ የሥራ ዝርዝርና የሒሳብ መግለጫ ሪፖርት በንባብ ተሰምቷል፡፡
በምርቃቱ ሥነ ስርዓት የተገኙት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር የሆኑት ክቡር አቶ አባዲ ዘሙ ባደረጉት ንግግር በቅድሚያ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምእመናንን ለመባረክና ቤተ ክርስቲያኗ በየጊዜው የምታደርገውን የሥራ እንቅስቃሴ ለመገንዘብ በሱዳን ጉብኝት ለማድረግ በመምጣቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ከገለፁ በኋላ የጎረቤት ሀገራት ሰላም፣ ደህንነትና ብልፅግና ለሀገራችን ሰላም፣ ደህንነትና ብልፅግና መስፈን የማይተካ ሚና ስለሚጫወት በመንግሥታት ደረጃ ከሚደረገው ግንኙነት በተጨማሪ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር በሚል የተያዘው የመንግሥታችን ጽኑ አቋም ይህ የቅዱስነትዎ ጉብኝት ሰፊ መሠረት የሚጥል ፋና ወጊ ተግባር ነው በማለት ገልፀውላቸዋል፡፡
በመቀጠልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ በማካሔድ ላይ ከምትገኘው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በተጨማሪ ከሀገራቸው ውጭ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጐቻችን በመንፈሳዊ እድገት እንዲበለጽጉ፣ ሕፃናትና ወጣቶች የሀገራቸውን ባሕልና ቋንቋ እንዲያውቁና እንዲረዱ፣ እንዲሁም በሀገራቸው ሥርዓተ ትምህርት እንዲማሩ በማድረግ ረገድ የቤተ ክርስቲያኗ ሚና እጅግ ተተቃሽ እየሆነ መምጣቱን አስታውሰው ለሀገራችን ብሎም ለአፍሪካ የኩትና ራስን የመቻል ተምሳሌት የሆነውን የሕዳሴ ግድባችን ግንባታ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያንም በየዓመቱ የዐሥራ ሁለት ሺህ (12,000) ዶላር የቦንድ ግዢ በመፈጸም ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ምእመናኑም ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደምትገኝ ሰፋ አድርገው መግለጫ አቅርበዋል፡፡
የምርቃቱ መርሐ ግብር ከመጠናቀቁ በፊት ቅዱስ ፓትርያርኩ ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለካህናትና ምእመናን ባስተላለፉት መልእክት ከአቀባበሉ ጀምሮ ስለተደረገላቸው አክብሮት የተሞላበት አቀባበል ከፍተኛ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ኢትዮጵያውያን በሔዱበት ዓለም ሁሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ታሪክ ሠሪ ትውልድ መሆናችንን ማስመስከርና የነበረንን ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪካችንን መመለስ አለብን በማለት ገልፀው አሁን በደብረ ሰላ ሰበካ ጉባኤና በምዕመናን ትጋት ተሠርቶ ለምርቃት የሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያና ከፍተኛ ክሊኒክ እጅግ የሚያስደስት ከመሆኑም በላይ ይህ ለሀገርና ለወገን ኩራት የሆነው ሥራ የኢትዮጵያዊነት ፍቅራችሁና ትብብራችሁ መገለጫ ስለሆነ ልትመሰገኑ ይገባል ብለዋል፡፡
በነጋታው ቅዱስ ፓትርያርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሴክሬታሪያት ከሆኑት ከአምባሳደር አብደላ ሐማድ አልአዝራቅ ጋር ተገናኝተው ስለ ሁለቱም ሀገራት መልካም ግንኙነት መቀጠል ስለሚገባቸው እሴቶች በማንሳት ጠቃሚ ውይይት አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በዋናነት በሕገ ወጥ መንገድ ወደሀገራቸው የሚገቡ ኢትዮጵውያን አስፈላጊ ማጣራት በማድረግ በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩበትን አግባብ እያመቻቹ እንደሚገኑ አብራርተዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩም በዜጎች አያያዝና ፈቃድ አወጣጥ ላይ ሱዳን እየተከተለችው ያለው መንገድ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልፀው ለወደፊቱም ይህንን መልካም ተግባር እንዲቀጥል አደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡
በመቀጠልም ቅዱስ ፓትርያርኩ የይማኖት ሚኒስትር ከሆኑት ከአቶ አልፈታህ ታጅ አልሰር አብደላ ጋር ተገናኝተው ስለ ሁለቱ ሀገራት ጥንታዊ ግንኙነትና ስለሃይማኖቶች መቻቻል በሰፊው ተወይይተዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አስቀድመው በኢትዮጵያ ስላለው የሃይማኖት የመቻቻል እሴት ከገለጹላቸው በኋላ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ በነፃነት ሃይማኖቻቸውን እንዲያመልኩ መፈቀዱ በጣም የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸውላቸዋል፡፡ ሚኒስቴሩም የእንኳን ደህና መጡ ንግግር ካደረጉ በኋላ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን በነፃነት እንዲያራምዱ የማድረግ ወንድማዊ ግዴታ አለብን ካሉ በኋላ አሁንም በፖርት ሱዳን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸውላቸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በሱዳን ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ በተገኑበት ጊዜ ስለ ጉብኝታቸው አስመልክቶ በጋዜጠኞች በተጠየቁበት ጊዜ ሐዋርያዊ ጉብኝቱ በጣም አስደሳችና ውጤታማ መሆኑን ገልጸው ያነጋገሩዋቸው የሱዳን የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ለኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ሁለገብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል የገቡላቸው መሆኑንና የኤምባሲው ቀና ተግባር ታክሎበት በሱዳን የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እያደረገው ያለው ወገንና ሀገርን የሚያኮራ ተግባር ይበል የሚያሰኝና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባዳደር የሆኑት አቶ አባዲ ዘሙ በበኩላቸው የቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ ጉብኝት መንግሥታችን ለያዘው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑንና ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ካደረጓቸው ውይይትም መልካም ውጤት መገኘቱን ለጋዜጠኞች ገልፀዋል፡፡
በፓትርያርኩ የተመራው ልዑክ በሱዳን-ካርቱም ለዐራት ቀናት ያደረገውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቆ የካቲት 4 ቀን 2007 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment