Sunday, February 22, 2015

ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮



ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮

በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋል፡፡



በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና፡፡
ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ መቶ ተነሥቶ ከዐረገና ከአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው፡፡




ከዚህ ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ማርያም ትጸልይ ዘንድ ያለማቋረጥ ወደ ልጅዋ መቃብር ሁል ጊዜ ስትሔድ ኖረች ይኸውም ጎልጎታ ነው፡፡ አይሁድም በአዩዋት ጊዜ ቊጣንና ቅናትን ተመልተው በደንጊያ ሊወግሩዋት ወደዱ እግዚአብሔርም ከዓይናቸው ሠወራት ከዚህም በኋላ ዳግመኛ መጥታ በዚያ እንዳትጸልይ ተማክረው ከመቃብሩ ዘንድ ጠባቂዎችን አኖሩ እርሷ ግን በእየዕለቱ መሄድን አላቋረጠችም ጠባቆችም አያይዋትም የልጅዋ የጌትነቱ መጋረጃ ሠውርዋታልና መላእክትም መጥተው ያገለግሏታል ጌታችንም ዘወትር ይጐበኛታል የምትሻውንም ይፈጽምላት ነበር፡፡
ከዚህም በኋላ መላእክት ወደ ሰማያት አሳረጓትና የጻድቃንን ማደሪያዎች አሳዩዋት አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብም ወዳሉበት አደረሱዋት ከአዳም ጀምሮ እስከዚያ ዕለት በአካለ ነፍስ ያሉ አባቶች ሁሉ አንቺን ከሥጋችን ሥጋን ከዐፅማችን ዐፅምን ለፈጠረልን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአምላክ ልጅ ከአንቺ ሰው በመሆኑ በአንቺ ድኀነትን አግኝተናልና ከጥፋትም የሕይወት ወደብ ሁነሽልናልና እያሉ ሰገዱላት፡፡
ከዚያም ወደ ተወደደ ልጅዋ የእሳት መጋረጃ ወደተተከለበት ወደ ጌትነቱ ዙፋን አደረሱዋት ጌታችንም እጅዋን ይዞ ወደ ውስጠኛው መጋረጃ አስገብቶ ከጌትነቱ ዙፋን ላይ አውጥቶ ከእርሱ ጋር አስቀመጣት ያዘጋጀላትንም ዐይን ያለየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ ተድላ ደስታን ሁሉ ነገራት፡፡
ከጌትነቱ ዙፋንም በታች የእስራኤል ንጉሥ አባቷ ዳዊትን የነቢያትና የመላእክት ማኅበር እንደ ግድግዳ ከበውት በመሰንቆ ሲያመሰግን አየችው እንዲህም ይላል ልጄ ስሚ በጆሮሽም አድምጪ ወገንሽን የአባትሽንም ወገን እርሺ ንጉሥ ደም ግባትሽን ወዷልና እርሱም ጌታሽ ነውና፡፡
ዳግመኛም የሥቃይን ቦታ ያሳዩዋት ዘንድ መላእክት ከዚያ ወሰዱዋት ለሰይጣንም ለሠራዊቱ በእርሱ ጐዳና ለሚጓዙ ሁሉ ወደ ተዘጋጀ ወደ ጨለማው ዳርቻ አደረሷት፡፡ እመቤታችን ማርያምም ወዮልኝ ወደዚህ እንዳይመጡ ለሰው ልጆች ማን በነገራቸው አለች መልአኩም እመቤቴ ቡርክት ማርያም ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ በኋላም በቃል ኪዳንሽ ለሚታመኑ አትፍሪ አላት ከዚህም በኋላ ወደ ቦታዋ መለሷት፡፡
ከዚያንም ጊዜ ጀምራ እመቤታችን ድንግል ማርያም ስለ ኃጥአን እጅግ እያዘነች ኖረች እንደ ዛሬዪቱም የካቲት ዐሥራ ስድስት ቀን በጎልጎታ ቦታ ቁማ ወደ ልጅዋ እንዲህ ብላ ለመነች፡፡ ልጄ ሆይ በእግዚአብሔር አባትህ በክርስቶስ ስምህ ከአንተ ጋርም ህልው በሆነ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ አማፅንሃለሁ ዓለም ሁሉ ሊሸከምህ የማይችል ሲሆን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በተሸከመችህ ማኅፀኔ አማፅንሃለሁ ልጄ ሆይ ያለ ሕማም ያለ ድካም ከእኔ በመውጣትህ በመወለድህ በአሳደጉህ እጆቼ ከአንተ ጋር በተመላለሱ እግሮቼ አማፅንሃለሁ፡፡ በውስጡ በተኛህበት በረት በተጠቀለልክበት ጨርቅ አማፅንሃለሁ የምወድህ ልጄ ሆይ በልቡናዬ ያለውን ሁሉ ትፈጽም ዘንድ የልመናዬን ቃል ሰምተህ ወደእኔ ትመጣ ዘንድ ወዳንተ ፈጽሜ እማልድሃለሁ፡፡
የብርሃን እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም እንዲህ ብላ በጸለየች ጊዜ እነሆ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወረደ ከእርሱም ጋር አእላፋት መላእክት አሉ በዙሪያውም ሁነው ያመሰግኑታል፡፡ እርሱም እናቴ ማርያም ሆይ ምን ላድርግልሽ አላት እመቤታችንም ለተወዳጅ ልጅዋ እንዲህ ብላ መለሰችለት ልጄ ወዳጄ ሆይ ጌታዬና ፈጣሪዬ አለኝታዬና መጠጊያዬ በእናቴ ማኅፀንም ሳለሁ በአንተ ጸናሁ አንተም ጠበቅኸኝ ሁልጊዜም ስም አጠራሬ አንተ ነህ፡፡
አሁንም ጸሎቴንና ልመናዬን ስማኝ ቃሌንም አድምጥ እኔ እናት እኔም አገልጋይህ የምለምንህ ይህ ነው መታሰቢያዬን ለሚያደርጉ ነስሜ አብያተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ወይም የተራቆተውን ለሚያለብሱ የተራበውን ለሚያጠግቡ የተጠማውን ለሚያጠጡ የታመመውን ለሚጐበኙ ያዘነውን ለሚያረጋጉ የተከዘውንም ደስ ለሚያሰኙ ወይም ምስጋናዬን ለሚጽፉ ልጆቹንም በስሜ ለሚሰይም በበዓሌም ቀን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን በሰውም ልቡና ያልታሰበውን  በጎ ዋግ ስጣቸው በአማላጅነቴም የሚታመነውን ሁሉ ከሲኦል ነጻ አድርገው ከአንተ ጋር የደረሰብኝን ረኃቡንም ጥማቱን መከራውን ሁሉ አስብ አለችው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደልሽው ይሁንልኝ የሰጠሁልሽም ቃል ኪዳን እንዳይታበል በረሴ ማልኩልሽ አላት፡፡



ሰላም ለኪ መጽሐፈ ሕግ ወኪዳን፤

አምሳለ ጽሌ ዘዕብን፤

ለእለ ጸውዑ ስመኪ ውስተ ኵሉ መካን፤

ርኅርኅተ ልብ ለኃጥአን ርኅርኅተ ልብ ለግፉዓን፤

ርኅርኅተ ልብ ለኵሉ ማርያም አማን፡፡




ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን ድንግል ማርያም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን፡፡





No comments:

Post a Comment