Wednesday, February 25, 2015

‹‹ከሃይማኖት ልዩነት ጋር ወደ ትዳር እያመራን ነው፡፡››

ከእጮኛዬ ጋር ከተዋወቅን ሁለተኛ ዓመት ሆኖናል፡፡ነገር ግን በሃይማኖት ከእኔ የተለየ በመሆኑና የፕሮቴስታንት እምነትን ስለሚከተል መግባባት አልቻልንም፡፡በዚህ ሁኔታ ትዳር መመሥረት በራሱ ከባድ ሆኖብኛል፡፡ምክርዎን እጠብቃለሁ፡፡

                                                                                                          ሜሮን ከአዲስ አበባ
እኅታችን በመጀመሪያ ለጥያቄሽ መፍትሔ ለማግኘት በመጻፍሽ አመሰግናለሁ፡፡ወደ ጥያቄው መልስ ስንሔድ ከላይ እንዳነሣሽው ጓደኛሽ የፕሮቴስትንት እምነት ተከታይ በመሆኑ መግባባት አቅቷችኋል፡፡ከዚህ ልዩነት ጋር ትዳር መመሥረቱ ደግሞ በራሱ ለልቦናሽ ከባድ ሆኖ ታይቶሻል፡፡በጥያቄሽ ያላነሣሽው እጮኛሽን ለመመለስ ያደረግሽውን ጥረት ነው፡፡ከዚህ ቀደም እርሱን አስተምሮ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስ ጥረት አላደረግሽ ከሆነ ይህንን አስቢበት፡፡መምህራን አግኝተው እንዲያስተምሩት እውነቱን እንዲነግሩት አድርጊ፡፡መመለስ ከፈቀደም በስሜት እንይሆን የተወሰነ ጊዜ ሰጥተሽ ተመልከቺው፡፡
ስለመመለሱ እርግጠኛ ለመሆን የተቻለሽን ጥረት አድርጊ፡
ከዚህ ውጭ አስመክረሽው ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ አንቺም በሃይማኖትሽ እኔም በሃይማኖቴ እያለሽ ከሆነ ግን ይህ በትዳራችሁ ላይ ፈተና የሚሆን፣ከቤተክርስቲያንም አስተምሮ ዉጭ የሆነ አካሔደ ነዉ።ለመሆኑ እኛ የምንከተላትን የኦርቶዶከስ  ተዋሕደ ሃይማኖት የማይከተሉት በጋብቻ መዛመድ መልካም እንዳልሆነ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረን ለምንድነዉ? በሃይማኖቱ  ከተለየ ሰዉ ጋር  አንድ መሆን  የሚያስከትለዉ ጉዳት ምንድን ነዉ? ቀጥለን እንመልከት
፩- የእግዚብሔርን ሕግ መተላለፍ ስለሆነ  
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል እንዲህ ብሎናል፡፡ ‹‹ቀኝ ዓይንህ ብትሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንዱ ቢጠፋ ይሻላልና›› /ማቴ ፭ -፳፱/፡፡ ዓይን የተባለች ሚስት ናት፡፡ ከዓይን የሚሰወር እንደሌለ ከሚስትም የሚሰወር የለምና ዓይን ይላታል፡፡ ሚስትህ /ዓይንህ/ ያልሆነ ሥራ ላሠራህ ብትል ፈቃዷን አፍርስባት፡፡ ዛሬ በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ ፈጽመህ ኑረህ ኋላ ገሃነም ከምትገባ በዚህ ዓለም የሚስትህን ፈቃድ አፍርሰህ ኑረህ ኋላ መንገሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃል ሲለን ነው፡፡ ጌታችን እንዳስተማረን ሚስት ወይም ባል በሃይማኖት ከተለዩ አብሮ ገሃነም ከመውረድ ተለይቶ ራስን ማዳን ይገባል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሔድ አትጠመዱ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና; ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው?ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው?ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ቤት ጋር ምን መጋጠም አለው?;››/ ፪ቆሮ ፮-፲፬/ ይለናል፡፡ የማያምኑ የሚጠራጠሩ መናፍቃንን በማይመች አካሔድ መቅረብ/ ለትዳር፣ ለቤተሰባዊነት/ ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ ነግሮናል፡፡
እኅታችን በአንቺ ሚዛን መዝነሽ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሕግ ግንኙነታችሁን መርምሪው፡፡ ንስሐ ገብቶ እስካልተመለሰ በኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ለመያዝ እስካልወሰነ ድረስ በጋብቻችሁ ፈጣሪ እንደማይደሰት አትዘንጊ፡፡ መናፍቅ የሆነን ሰው ማግባት የክርስቶስን፣ የሐዋርያትን፣ የሊቃውንትና ትምህርት ማቃለል መሆኑን አንድ ነገር አትርሺ፡፡ የአንቺን ፍላጎትና ሐሳብ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንንም ትምህርት ሕግ የእግዚብሔርን ፈቃድ አስበሽ ወስኝ፡፡ለጊዜው ጥሩነቱን ዓይተሽ ብትወጅው እንኳን መልካምነቱ ለአንቺ ብቻ መሆኑን አስተውይ፡፡ የምታምኝውን እስካላመነ በትክክለኛ ሃይማኖት እስካልቆመ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጎድለው ትልቅ ነገር አለ፡፡
በምድራዊ ጉዳይ ላይ ወንጀል የሚሠራ ቢሆን ነፍስ ገዳይ፣ ዘራፊ ሽፍታ ቢሆን ለሕይወትሽ ስለምትፈሪ በማንነቱ ስለምታፍሪ ለጋብቻ አታስቢውም፡፡ መናፍቅነት ደግሞ በነፍስ ከቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር መንግሥት መሸፈት ነው፡፡ ቅዱሳንን ታቦቱን፣ መስቀሉን እያቃለሉ በመንፈሳዊነት ላይ ወንጀል መሥራት ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ካለ ሰው ጋር ተጉዘሽ ከፈጣሪሽ እንዳትለይ ለራሰሽ አስቢ፡፡
. የቤተሰብን ሕይወት ስለሚጎዳ
የተለያየ ሃይማኖት እየተከተሉ ትዳርን የሚመሠርቱ ባልና ሚስት የሚያፈሩትን ቤተሰብ ግራ ይጋባሉ፡፡የሚወልዷቸውን ልጆች የተመሰቃቀለ ሐሳብ ይዘው እንዲያድጉ ያደርጋል፡፡እርሷ ወይም እርሱ ኦርቶዶክሳዊ  ሆነው በጋብቻ አብሯቸው ያለው ሰው ሌላ እምነት ከተከተለ ችግሩ ለልጆቻቸውም ይተርፋል፡፡ሲወለዱ በጥምቀት ምክንያት ከሚነሣው ንትርክና ጭቅጭቅ አንሥቶ ኋላ ላይ በአስተዳደጋቸው ብዙ ልዩነቶች ይፈጠራሉ፡፡አንደኛው የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖትን ትክክለኛ ትምህርት ሲያስተምር ሌላው ኑፋቄውን ጥርጥሩን ይዘራል፡፡አንዱ ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ሲናገር ሌላው አማላጅነቷን በማቃለል ክህደት ይዘራል፡፡ይህ ደግሞ በራሱ ልጆቹ ሕሊና አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ያስከትላል፡፡
ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት በዘመኑ ፍጻሜ የሚሞትበት ቀን ሲቃረብ ልጁ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል መክሮታል፡፡ ‹‹እኔ የምድሩን ሁሉ መንገድ እሔዳለሁ በርታ ሰውም ሁን የምታደርገውንና የምትሔድበትን ሁሉ ታከናውን ዘንድ በሙሴ ሕግ እንደተጻፈ ሥርዓቱንና ትእዛዛቱን ፍርዱን ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ በመንገዱም ትሔድ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔር ትእዛዝ ጠብቅ›› /1ነገ.2.2/፡፡ ወላጆች በምድር ላይ ልጆቻቸውን አሳድገው የሚያወርሱት ምድራዊ ዕውቀትና ሀብት ብቻ አይደለም ትልቁ ውርስ ሃይማኖት ነው፡፡ ሃይማኖትም ለማውረስ ደግሞ እናትም አባትም መስማማት አለባቸው አንድ መሆን አለባቸው፡፡እናት ኦርቶዶክሳዊ እንዲሆን አስባ ልጇን ቅዳሴ ላይ አንዲገኝ እያደረገች ጠበል እያጠጣች፣ እጣን እንዲሸተው፣ የቤተ ክርስቲያን ፍቅር እንዲያድርበት እየመከረችው አባት ደግሞ ይህንን ሁሉ የሚያፈርስ ሐሳብ ይዞ ቢመጣ ልጆች በመካከል ግራ ይጋባሉ።ባለመግባባቱ ምከንያት ሃይማኖት አልባ ሆነው ሊቀሩም ይችላሉ፡፡
ከዚህ አንጻር እኅታችን ስለአንቺ መደሰትና ማዘን ለጊዜው መዋደድ ብቻ ሳይሆን ነገ ስለምታፈሪያቸው ልጆችም አስቢ፡፡በትክክለኛ ሃይማኖት ታንጸው እንዲያድጉልሽ እጮኛሽን ወደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት እንዲመልስልሽ፣አልያም ይህን ዓለማ ገንዘቡ ያደረገ በኦርቶዶክሶዊ ሃይማኖት የጸና ምእመን ለትዳር እንዲሰጥሽ ፈጣሪሽን ተማፀኚ፡፡
፫- የፍላጎት ልዩነት ስለሚከሰት
ለትዳር የሚተሳሰቡ እጮኛሞች ፍላጎታቸው ሐሳባቸው ዓላማቸው ተመሳሳይ ሲሆን ትዳር ጣፋጭ፣ሰላማዊ ፍቅርና መተሳሰብ የሞላበት ይሆናል፡፡የፍላጎት መለያየት /Interest conflict/ ካለ ግን ለጊዜው በስሜታዊነት አንዱ ሌላውን ላለማጣት ሲል ሸፍነውት ቢቆዩም የኋላ ኋላ ልዩነት አለመስማማት ይከሰታል፡፡ወደ አንድነትና መቀራረብ ለመምጣት ጥረት ካላደረጉ ልዩነታቸዉ እየሰፋ ይሄዳል።የፍላጎት መለያየት እንኳን በሃይማኖት ደረጃ ጎልቶ ይቅርና በመጠኑ በጥቃቅን ጉዳይ ላይ እንኳን  ሲኖር በራሱ ብዙ ፈተና አለው፡፡የሃይማኖት ልዩነት ደግሞ ከሁሉ የላቀና ባለቤቶቹ የልዩነታቸውን ምክንያት /ሃይማኖታቸውን/ የተረዱ ዕለት በጣም የሚያቃቅር ስለሆነ ይህን ልዩነት ይዞ ጋብቻ ከባድ ፈተና ያመጣል፡፡
በሃይማኖት ተለያይተዉ አብረዉ የሚኖሩ  እጮኛሞች ለጊዜው አንዱ የሌላውን ሃይማኖት ሳይነካ ተከባብረው ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ሁለቱም ሃይማኖታቸውን እንዳያጠብቁ እየፈሩ አላልተውት ሊሰነብቱ ይችላሉ፡፡ይህ ግን ለሁል ጊዜም አይቀጥልም። አንድ ቀን ወደ የሃይማኖታቸው መመለሳቸው አይቀርም ያን ጊዜ ልዩነቱ ሰፊ መሆኑን መረዳት ይጀምራሉ፡፡ለጊዜው ባል መናፍቅ ቢሆንም ጉዳት የለውም ያለች ሚስት አንድ ቀን ንስሐ መግባት መቁረብ ስትፈልግ ልዩነታቸውም እንደሚከለክላት ትረዳለች።አርሱ ካልተመለሰ  ንስሐ ለመግባት ለመቁረብ የግድ መለየት እንዳለባት ስትረዳ ታዝናለች።በአንድ በኩል ክርስትናዋ በሌላ በኩል ትዳን እያሰበች አጣብቂኝ ዉስጥ ተወድቃለች።ግር ተጋባለች።የጋብቻ ቀኗን መርገምም ልትጀምር ትችላለች፡፡
እህታችን ልዩነታችሁ ለጊዜው ቀላል ቢመስልሽ እንኳን የኋላ ኋላ ግን የማትወጪውን ፈተና ይዞብሽ ይመጣል፡፡ንስሐ መግባት ብትፈልጊ፣የእግዚአብሔር ልቦናሽን መልሶት መቁረብ ብትፈልጊ፣አብረሽው በምትኖሪው ሰው ምክንያት ሳትችይ ተከልክለሽ መቅረት ይመጣል፡፡ምናልባት ያን ጊዜ ይመለሳል ብለሽ ማሰቡ በውስጥሽ ካለ እርሱ ሁልጊዜ አይሳካም፡፡አሁን በአዲስነቱ አንዱ ለሌላው በጣም ታዛዥ በሚሆንበት የእጮኝነት ሕይወት ሳይታዘዝሽ  ያን ጊዜ ይመለሳል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ይልቁንም እርሱንም ፓስተሮቹ አግኝተውት የበለጠ በስሕተቱ እንዲገፋ ሊያደረጉት ይችላሉ፡፡እርሷን አምጣት ብለው አንቺንም እንዲያስትሽ ሊመክሩት ይችላሉ፡፡ይህን አስበሽ ልዩነታችሁን በጊዜ ለማጥበብ/እርሱን ለመመለስ/አልያ ግን ከልዩነት ጋር ትዳርን ላለመጀመር ራስሽን ብታሳምኚ መልካም ነው፡፡
እኅታችን ከላይ ያሉትን ሌሎች የተለያዩ ችግሮች ስላሉት በሃይማኖት የማይመስለን ሰው ይዞ ወደ ጋብቻ መጓዝ ከባድ ነው፡፡‹‹ፍቅር›› ብለሽ የምትጠሪው እጮኛሽን የወደድሽበት መውድድ ከላይ ያሉትንም ጉዳዮች ያገናዘበ እንዲሆን አድርጊ፡፡ሃይማኖት ለትዳር የምንመርጠውን ሰው የምንመዘንበት ትልቁ መስፈርት ነው፡፡ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ ለሃይማኖትሽ ቅድሚያ ስጭ፡፡ከእጮኛሽ ጋር  በጀመራችሁትም ጉዞ አንዴ ተበላሽቷል ብለሽ አትግፊበት፡፡ወደ ፊት የሚፈጠሩት ችግሬች አስካሁን ከነበረው ሁሉ የሚከፉ ናቸው፡፡ትዳር  ስትመሠርቱ  ልጆች  ስትወልዱ  ከላይ  እንዳየነው  ልዩነታችሁ  በገሃድ  መገለጡ  ስለማይቀር  ችግሮቹ  ግልጥ እየሆኑ ይመጣሉ።አንቺንም  የምትወልጃቸዉንም ልጆች ህይወት ወደ ሚያዉኩበት ደረጃ ይደርሳሉ።ስለዚህ  ዉሳኔሽ   ማስተዋል  የተሞላበት ለነገዉም  ሕይወትሽ  የሚበጅ ይሁን።ለሁሉም  ፈጣሪ  ቀናዉን መንገድ ሁሉ ያመልክትሽ።
                                                                                    
                                                                                   ምንጭ፡- የያሬድ ቤት ብሎግ

No comments:

Post a Comment