Wednesday, April 15, 2015

የትንሣኤው ትርጉምና የሰሙነ ፋሲካ ዕለታት

                     ትንሣኤ የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡

             መገኛ ቃሉም ተንሥአ =  ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡
ትንሣኤ ማለት = መነሣት፣ አነሣሥ፤ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡ ትንሣኤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም አምስት ክፍሎች አሉት፡፡
አንደኛው ትንሣኤ ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡
ሁለተኛውም ትንሣኤ ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡
ሦስተኛው ትንሣኤ ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡
አራተኛውትንሣኤ የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የትምህርታችንም መሠረት ይኸው ነው፡፡
ዐምስተኛውና የመጨረሻው የትንሣኤ ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ መሠረት ያደረገ ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡


  ወደ ተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ ፋሲካ ተብሎ ይጠራል፡፡

ፋሲካ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ፌሳሕ በጽርእ በግሪክኛው ስኻ ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር፤ መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛውፓስኦቨር ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደ ነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል ትንሣኤ ተተክቶበታል፡፡

ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ
o  ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣
o  ከኀሳር፤ ከውርደት ወደ ክብር፣
o  ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣
o ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገርንበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡

ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ እየተባባለ በመጠራራት አብሮ ሲበላ ሲጠጣ ልዩ ልዩ ጨዋታ ሲጨዋወት ለንስሐ አባትና ለሽማግሌዎች፤ ለወዳጅ ዘመድም የአክፋይ ዳቦ፣ ወይም የሥጋ ወጥ ግፍልፍል ሲወስድ ይሰነብታል፡፡

ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታትም ሰሙነ ፋሲካ ወይም ትንሣኤ እየተባሉ የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡ ይኸውም፡-

ሰኞ

ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሆና ፀአተ ሲኦል ማዕዶት ትባላለች፡፡ ዮሐ. 19-18፤ ሮሜ. 5-10-17፡፡ የዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ግን ገበሬው ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ፤ ሴቶቹ ደግሞ ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለሆነች እጅ ማሟሻ ሰኞ ትባላለች፡፡

ማክሰኞ

የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ በቶማስ ተሰየመች፡፡
ዮሐ. 20-24-30

ረቡዕ

ከሞተና ከተቀበረ ዐራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣውና፤ እርሱም ተነሥቶ በማየት በጌታችን ብዙ ሕዝብ ስለአመነበት፣ ቀኒቱ ለአልዓዛር መታሰቢያ ይሆን ዘንድ አልዓዛር ተብላ ትታሰባለች፡፡ዮሐ. 11-38-46
ኀሙስ

የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና የአዳም ኀሙስ ተብላ ትከበራለች፡፡ሉቃ. 24-25-49
ዐርብ

በክርስቶስ ደም ተዋጅታ ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ ቤተ ክርስቲያን ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ. 26-26-29 የሐ. ሥራ. 20-28
ይህች ዕለትም እንደ ዕለተ ኀሙስ ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም፡-
አንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን ጾም የሚፈጸምባት፤ የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን ተጽዒኖ ስትባል፤ በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ ትባላለች፡፡
ሁለተኛውም በመጀመሪያ የሰው አባትና እናት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፣ ኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም መከራ ተቀብሎ ስለተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለፈጸመባት ዕለተ ስቅለት አማናዊቷ ዐርብ ትባላለች፡፡
ሦስተኛው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች ማለት ነው፡፡
ቀዳሚት
በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበይባት የቁራ ገበያ የገበያ ጥድፊያ ስትባል በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ለአገለገሉት፤ በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ የትንሣኤው ዕለት ገና ከሌሊቱ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አንስት መልካም መታሰቢያ ሆና አንስት ተብላ ትጠራለች፡፡ ሉቃ. 23-27-33፣ 24-1-01፣ማቴ. 25-1-11
የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ...

በዚች ሰንበት ከላይ እንደተጠቆመው የትንሣኤው ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ በር ገብቶ በመካከላቸው ተገኝቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ብሎም ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ የጌታችን መነሣትና እንደተገለጸላቸውም በደስታ ሲነግሩት በኋላ እናንተ አየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን ሰምቼአለሁ ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም በማለቱ የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ ምክንያቱን ለይቶ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ሰላም ለሁላችሁ ይሁን በማለት በመካከላቸው ቆመ፤ ቶማስንም ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ፤ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደፍላጎቱ በመረዳቱ ጌታዬ አምላኬ ብሎ መስክሮ አመነ፡፡
እንግዲህ ይህ የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ ዳግም ትንሣኤ ተብሎ ሰንበቱ ይጠራበታል፤ ይከበርበታል፡፡ዮሐ. 20-24-30፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሁሉ ከቅዳሴው ውጭ ከሚፈጸመው ድኅረ ቁርባን በስ ተቀር ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ዕለት ሆኖ ይከናወናል፡፡
ለብርሃነ ዕርገቱ በሰላም ያድርሰን አሜን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር