Monday, April 20, 2015

  ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ዐረፉ           
002abune peteros 
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የባሕር ዳር፤ የአዊና የመተከል አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተወለዱ በ84 ዓመታቸው ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ጠዋት ዐርፈዋል፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ የተገነባውን መንፈሳዊ ኮሌጅ በቅዱስ ፓትርያርኩ ካስመረቁ በኋላ ድንገት በመታመማቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና ሲደረግላቸው ቢቆይም ሚያዝያ 10 ቀን ጠዋት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ሥርዐተ ቀብራቸው እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡


ልደት፡-
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከአባታቸው ከአቶ በዛ ካሳ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ውብሻው ወንድም በ1923 ዓ.ም. በጎጃም ክፍለ ሀገር በዳሞት ወረዳ በደብረ ገነት ልዩ ስሙ ዓይን አምባ ቁስቋም በተባለ ሥፍራ ተወለዱ፡፡

ትምህርት፡-
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ከመሪ ጌታ ደለለ ፈንታ ከፊደል እስከ ዳዊት ተምረዋል፤

መዝሙረ ዳዊትን እንደጨረሱ ቢቡኝ ወረዳ ድጓ ጽዮን በመሔድ ከመሪጌታ ወርቄ ጸዋትወ ዜማ ተምረዋል፤

በይልማና ዴንሳ ወረዳ በምትገኘው በአይባር ኪዳነ ምሕረት ከመሪጌታ ብዙአየሁƒ  በጎንደር ቆላ ድባ አውራጃ በተንከር ወረዳ እንዳበጋ ቅዱስ ሚካኤል ከመሪጌታ አክሊሉ ወርቅነህ፤ ጉታ ማርያም ከነበሩት ከታላቁ መምህር ከየኔታ ግጨው መንክር ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል፤

በ1953 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥርዓት አጥንተው ፤ ወደ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም በመሄድ ከመሪጌታ ልዑል ቅዳሴ ተምረዋል፤

በደብረ ዐባይ መዝገበ ቅዳሴና ባሕረ ሐሳብ ተምረው የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፤

በ1959 ዓ.ም. ወደ ግሸን ማርያም በመሄድ ከመምህር ወልደ ኪዳን ውዳሴ ማርያም፤ ቅዳሴ ማርያም፤ ኪዳን፤ ትምህርት ኅቡአት፤ ዐርባእቱ ወንጌል ትርጓሜ ተምረዋል፤

በ1977 ዓ.ም. ወደ ግብፅ ተልከው ለሦስት ዓመታት የኮፕትና የዐረብ ቋንቋ ተምረው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፤

ወደ ግሪክ ተልከው ለአንድ ዓመት ግሪክኛ ቋንቋ ካጠኑ በኋላ ኮሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፤

በአሜሪካን ሀገር ቦስተን በሚገኘው የግሪክ ቲዎሎጂ ትምህርት ቤት እንግሊዝኛ ቋንቋን አጥንተዋል፡፡

መዐረገ ክህነት፡-
ዲቁና በ1943 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፤

ምንኩስና እና ቅስና በ1953 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከብፁዕ አቡነ ባስልዮስ፤

ቁምስና በ1958 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ በአክሱም ጽዮን ተቀብለዋል፡፡

አገልግሎት፡-
በኡራ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ቅኔ አስተምረዋል፤

በግሸን ማርያም ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ቅኔ አስተምረዋል፤

በማንጉድ አባ ልብድዮስ ገዳም ለስድስት ዓመታት በቅዳሴ መምህርነት አገልግለዋል፤

በ1964 ዓ.ም ወደ ሱዳን ተልከው ለሦስት ዓመታት በአስተዳደሪነት ቆይተዋል፤

የሳማ ሰንበት ገዳምን ለአንድ ዓመት አስተዳደርዋል፤

ከ1985ዓ.ም. እስከ 1990 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም እና አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡

በአዲስ አበባ የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም እና አንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል በአስተዳዳሪነት በቆዩባቸው ዓመታት አብያተ ክርስቲያናቱን ያሳደሱ ሲሆን፤ ዕቃ ቤችንና ልዩ ልዩ የአገልግሎት ቤቶችን አሰርተዋል፤

ከነሐሴ 1 ቀን 1990 ዓ.ም. ጀምሮ እሰከ ሰኔ 30 ቀን 1991 ዓ.ም. በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት ቆይተዋል፡፡
በካሪቢያን ደሴቶችና አካባቢው የሚገኙ ጥቁሮችን በማሰባሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት በማስተማርና በማጥመቅ አገልግለዋል፡፡

ሰኔ 30 እና ሐምሌ 1 ቀን 1991 ዓ.ም. ከ16 ቆሞሳት ጋር ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠው በቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንብሮተ እድ ተፈጽሞላቸው የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሹመዋል፡፡

ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ፡-
ከሐምሌ 1 ቀን 1991 ዓ.ም. ጀምሮ የመላው አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የአውስትራሊያና የኔዘርላንድ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ከጥቅምት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የምዕራብ ጎጃም፤ የአዊና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሞተ ሥጋ እስከተለዩበት ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ የባሕር ዳር፤ የአዊና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

ግዚአብሔር የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ከቅዱሳን አባቶቻችን ነፍስ ጋር ያኑርልን፡፡ አሜን፡፡