Wednesday, April 8, 2015

በሰሙነ ሕማማት የሚነሡ ጥያቄዎችና መልሶቻቸውአትምኢሜይል
መጋቢት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓዋጅ ከሚጾሙት አጽዋማት መካከል ዐቢይ ጾም፤ ጾመ ኢየሱስ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አሁን በጾሙ መጨረሻ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማምና ሥቃይ እንዲሁም እንግልት በምናስብበትና የጨለማውን ዘመን በምናስታውስበት ጊዜ /ሰሙነ ሕማማት/ ላይ እንገኛለን፡፡

ስለ ሰሙነ ሕማማት ስናነሣ በምእመናን ዘንድ የሚነሡ አንዳንድ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እኛም እነዚህን ጥያቄዎች ለሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በማቅረብ የሰጡንን ምላሽ ይዘን ቀርበናል፡፡

የግዝት በዓላት በሰሙነ ሕማማት ቢውሉ ስግደት መስገድ ይገባልን?
ጥያቄው በርካታ ምእመናን በየዓመቱ የሚያነሡት ጥያቄ ነው፡፡ የግዝት በዓል በሰሙነ ሕማማት ላይ ሲውል በአንዳንድ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሲያሰግዱ በአንዳንዶቹ ደግሞ ቀኑ የግዝት በመሆኑ ስግደት አይገባም ብለው ሲከለክሉ ይስተዋላል፡፡

የሰሙነ ሕማማት ቀናት የጌታችንን መከራና ሥቃይ የምናስብበት፣ የኃዘን የመከራ ጊዜያት ናቸው፡፡ በተለይም ደግሞ ስቅለት ከጌታችን ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በዓሉ ራሱ የሚከበረው በስግደት፣ በጾምና በጸሎት ነው፡፡

በዓሉ የጌታን መከራና ሥቃይ፣ መንገላታቱን የምናስታውስበት በመሆኑ በዓሉ የሚከበረው በስግደት፣ በጾምና፣ በጸሎት፣ በንባብና በትምህርት ነው፡፡ በመሆኑም ይህን በዓል የሚሸር ምንም ዓይነት የግዝት በዓል የለም፡፡ የግዝት በዓላት በየወሩ በውዳሴና በቅዳሴ የምናከብራቸው ወርኃዊ በዓላት ይኼንን በዓመት አንድ ቀን የሚመጣን ልዩና ዐቢይ በዓል ይሽሩታል የሚል ትምህርት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አላስተማሩም፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ንኡሳን በዓላትና ዐበይት በዓላት ተለይተው ይቀመጣሉ፡፡ ከጌታ በዓላት እንኳን ዐበይትና ንኡሳን ተብለው ተለይተው የሚቀመጡ በዓላት አሉ፡፡ ዘጠኙ የጌታ በዓላት ዐበይት ናቸው፡፡ በነዚህ በዓላት አይሰገድም፡፡ ነገር ግን ከእነዚህ ተለይቶ የስቅለት በዓል የበዓሉ ጠባይ በራሱ የሚከበረው በስግደት ስለሆነ በዚህ በዓል ስግደት ይገባል፡፡ በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሣት፣ ክህነት መስጠት፣ ለሞቱ ሰዎች መጸለይም አይገባም፡፡ ይላል ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 15 ቁጥር 600፡፡

የቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሕማማቱ በኃዘን፣ አብዝቶ በመጾም፤ ስለ መከራው በማሰብ፤ በስግደት እንዲከበሩ የሚያሳስብ መመሪያ የተላለፈበትን በዓል በወር የሚከበሩ የግዝት በዓላት አይሽሩትም፡፡ የሰሙነ ሕማማት በዓል ልዩና የስቅለቱን፣ የመከራውን፣ የሕማሙን ነገር የምናስብበት በመሆኑ መከበር የሚገባው በስግደት ነው፡፡ የሊቃውንቱም ትምህርት ይኸው ነው፡፡

ታችን በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት ቆይቶአልን?
ጌታችን በከርሰ መቃብር ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት መቆየቱ እውነት ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ቅዱሳት መጻሕፍት ያረጋግጣሉ /ዘፍ.22፤4፣ ዕብ.11፡17-19/፡፡ ለብዙዎች ጥያቄ የሆነው ጉዳይ አቆጣጠሩ በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

የጌታችን ትንሣኤ ትንቢተ ነቢያት የተፈጸመበት ነው፡፡ እርሱ ይጠግነናል፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል በሦስተኛውም ቀን ያነሣናል /ትን.ሆሴ. 6፤21/፡፡ የነቢዩ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ሌሊት ሦስት መዓልት መቆየቱ የትንሣኤ እግዚእ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ.12፡40-42፣ዮና.2፤1/፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንጽሖተ ቤተ መቅደስን በፈጸመበት ዕለት እንዲህ ለማድረጉ ምን ምልክት ታሳየናለህ? በማለት ለጠየቁት አይሁድ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አስነሣዋለሁ አላቸው፡፡ አይሁድ ለጊዜው አይረዱት እንጂ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር፡፡/ዮሐ.2፡18-21/

ሀ. ማታም ሆነ ጥዋትም ሆነ አንድ ቀን በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው አቆጣጠር የመጻሕፍትን ምስጢር ለመረዳት ከሚያግዙን ነገሮች መካከል መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን የዕብራውያንን ባህል ማወቅ አንዱ ነው፡፡ የዕብራውያን አንድ ሙሉ ቀን መቆጠር የሚጀምረው ማታውን ስቦ ነው፡፡ በመሆኑም ጌታችን ከተሰቀለባት ዕለተ ዓርብ ጀምረን እስከ ትንሣኤው ያለውን ማታና ጠዋት ስንቆጥር፣ የዕለተ ዓርብን መዓልት /ቀን/፣ የቅዳሜን ሌሊትና መዓልት እንዲሁም የእሑድን ሌሊት ስንቆጥር ዓርብ ሌሊቱን አምጥቶ እሑድ መዓልቱን ስቦ አንድ ቀን የሚባሉ ናቸውና ሦስት ቀን ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ቆይቷል፡፡

ለ. ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ የሚለው የኦሪት ዘፍጥረት ቃል የሚያስታውሰንም የብርሃንና ጨለማ መፈራረቅ አገልግሎታቸው ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት እንደሆኑ ነው፡፡

ሐ. ዓርብ ከነግህ እስከ ቀትር የነበረው ብርሃን አንድ መዓልት፣ በቀትር ከነበረው ጨለማ ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ /ማቴ.27፤45/፡፡ እንዲል አንድ ሌሊት በመሆን የመጀመሪያውን መዓልትና ሌሊት ያስቆጥራሉ፡፡

መ. ከዘጠኝ ሰዓት እስከ ዐሥራ ሁለት ሰዓት ያለው ብርሃን አንድ መዓልት፣ ቀጣዩ ጨለማ የቅዳሜ ሌሊት አንድ መዓልትና ሌሊት ሆነው ሁለተኛ ቀንን ይቆጥሩልናል፡፡

ሠ. የቅዳሜው መዓልትና /ቀን/ የእሑድ ሌሊት እስከ ትንሣኤው ጊዜ ድረስ ተቆጥሮ መዓልትና ሌሊት ሦስተኛን ቀን ያረጋግጡልናል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ተዋሕዶ፤ ሚያዝያ 1-5 ቀን 2004 ዓ.ም.