Tuesday, February 24, 2015

መንፈሳዊት ፍቅር


   ልዑል እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ከልዕልና ወደ ትህትና ወደዚህች ምድር መጥቶ የሰዎች ልጆችን ያዳነበት ምስጢር እጅግ ረቂቅ ጥልቅ ነው፡፡ አምላካችን ለኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠው ክብሩን በውርደት ለውጦ ነው፤ጠላቶቹ ስንሆን ነው የወደደን፡፡እንግዲህ በጥልቅ መንፈሳዊ ስሜት በእውነት ካስተዋልን አምላክ ሰው የመሆኑ ምስጢርና ለቤዛነት የመጣበትን ዓላማ በቃልና በድርጊት የፈፀማቸውን ስራዎች ስናስብ ልባችን በቅንነትና በማስተዋል የተመላ ከሆነ ዘወትር ይህንን ቃላት ሊገልጹት የማይችሉትን ለኛ ያለውን ወደር የማይገኝለትን ፍቅሩን ለማድነቅ እንገደዳለን፡፡
 
 “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብፅሖ እስከለሞት” ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ
አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው ተብሎ እንደተፃፈ፡፡የሰዎች ልጆችን ከባርነት ወደ ነፃነት፣ከመከራ ወደ ደስታ፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ለመግባት ያስቻላቸው የመድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደር የማይገኝለት ታላቅ ፍቅሩ ነው፡፡ስደት እና መንገላታት ውረደት እና በጥፊ መመታት፤መናቅ በብረት መቸንከር እነ በጦር መወጋት ለሰባኪው እና ለሰሚዎች፣ለፀሀፊው እና ለአንባቢዎች ቀላል መስሎ ቢታየንም አምላካችን ስለኛ ብዙ መከራ ተቀብሎ ህይወትን ሰጥቶናል፡፡ከፍ ያለው ፍቅሩ በክብደት መለኪያዎች ተመዝኖ ይህን ያህላል አይባልም፡፡ወርድ እና ቁመቱም ግምቱም አይታወቅም፡፡

Sunday, February 22, 2015

ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮



ስንክሳር ዘየካቲት ፲፮

በዚችም ዕለት የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓልን ያደርጋል፡፡



በዚች ዕለት መታሰቢያዋን ለሚያደርግ ስሟን ለሚጠራ ለድኆችና ለችግረኞች እስከ ቀዝቃዛ ውኃ ለሚሰጥ የክብር ባለቤት ከሆነ ከተወደደ ልጅዋ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት ቃል ኪዳንን ተቀብላለችና፡፡
ይህችም የከበረች እመቤታችን ልጅዋ ንጹሕ ሥጋዋን ተዋሕዶ ከብቻዋ ኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ፈጽሞ ስለእኛ መዳን ወዶ ያደረገውን መከራ ተቀብሎ መቶ ተነሥቶ ከዐረገና ከአባቱ ዕሪና ከተቀመጠ በኋላ እርሷን እናቱን ማርያምን በደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ዘንድ ትቷት ነበር እነሆ ልጅሽ እርሱንም እነሆዋት እናትህ ብሎ አደራ እንዳስጠበቀው፡፡