Thursday, January 29, 2015

/ዜና/ 50 የአቋቋም ደቀመዛሙርት ተመረቁ

 ጥር ፳፩ ፳፻፯ .

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በጎንደር ከተማ በደብረ ኃይል ወደብረ ጥበባት በዓታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የአቋቋም ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ 50 ደቀ መዛሙርት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቁ፡፡

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአብነት መምህራን እና ምእመናን የተገኙ ሲሆን፤ ደቀ መዛሙርቱ ከብፁዕነታቸው እጅ የአቋቋም ምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ “አዝመራው ብዙ ነው ሠራተኛው ግን ጥቂት ነው” በሚል ርዕስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተው ለተመራቂ ደቀመዛሙርቱ በተማሩት ትምህርት ወንበር ዘርግተው በማስተማርና ለምእመናን ትምህርት ወንጌልን በመስጠት በተለይም ለገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በመድረስ የተጣለባቸውን አደራ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ብፁዕነታቸው አያይዘውም “አሁን በዝታችሁ ትታያላችሁ፡፡ ነገር ግን በየቤተ ክርስቲያኑ ስትከፋፈሉ ቁጥራችሁ አነስተኛ ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ብቻ በዓመት ከ50 ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናትን እንተክላለን፤ ለሁሉም እናዳርስ ብንል እንኳን በቂ አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየን አሁንም ብዙ መሥራት፣ መማር፣ ማስተማር እና የሊቃውንቱ ምንጭ እንዳይደርቅ ደቀመዛሙርትን ማፍራት ይገባል” ብለዋል፡፡

የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤቱ መምህር መጋቤ አእላፍ ክቡር ጥላሁን ባስተላለፉት መልእክትም “እነዚህ ደቀ መዛሙርት ዛሬ ተመርቀዋል፤ ነገር ግን እየለመኑ ተምረው እየለመኑ መኖር የለባቸውም፡፡ በርካታ ደቀ መዛሙርት ከትምህርት ገበታቸው የሚሠደዱት ሥራ አላገኝም እያሉ ነውና እንደ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶስ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚመደቡበትን መንገድ ቢያመቻች ጥሩ ነው” ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ማኀበረ ቅዱሳን የሚያሰራውን G+2 ሕንፃ በተመለከተም መጋቤ አእላፍ ክቡር ሲገልጹ “ሕንፃው የማጠናቀቂያ ሥራ ብቻ ይቀረዋል፤ ማኅበሩ ከሕንፃው በተጨማሪ ለ40 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው በየወሩ የ100 ብር ድጋፍ ያደርጋል፤ ቤተ ክህነትም ለ30 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው 84 ብር በየወሩ ይደጉምልናል፡፡

ማኀበረ ቅዱሳን ለጉባኤ ቤቱ ዘመናዊ ቤት ሰርቶልናል ነገር ግን አሁንም ሠርከ ኀብስቱ እጥረት አሳሳቢ ስለሆነ ለተማሪው ፍልሰት ምክንያት እየሆነብን ነውና መፍትሄ እንሻለን፡፡ ደቀመዛሙርቱ የሚማሩት ከየሀገራቸው ትንንሽ ልጆችን እያስመጡ ልጆቹ በየመንደሩ በመንቀሳቀስ “በእንተ ስማ ለማርያም” ብለው ምግብ ያመጡላቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ እነዚህን ልጆች ያስተምሯቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአብነት ትምህርት ቤቶች ከዚህ በላይ ትኩረት ሰጥታ መሥራት አለባት” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በሊቀ ብርሃናት ኤልያስ አድማሴ በዐብየ እግዚእ ኪዳነ ምሕረት ወመርቆሪዎስ ቤተ ክርስቲያን የብሉያት መምህር ትምህርተ ወንጌል፣ በመምህር ጌዴዎን በርእሰ አድባራት አበራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ጉባኤ ቤት መምህር ቅኔ እና በደቀ መዛሙርቱ ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል፡፡

ጉባኤ ቤቱም በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ሲሆን፤ ለአብነት ያህል አለቃ ገብረ ሐና፣ መሪጌታ ሐሴት፣ መሪጌታ ገብረ ማርያም፣ መሪጌታ ገብረ ዮሐንስ፣ መሪጌታ አሚር እሸቱ፣ መሪጌታ ላቀው፣ መምህር ክፍሌ ወልደ ፃድቅ፣ መጋቤ አእላፍ ሄኖክ ወልደ ሚካኤል እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በጉባኤ ቤቱ ከ200 ያላነሡ ደቀ መዛሙርት ይገኛሉ፡፡ በየዓመቱም የደቀመዛሙርቱ ምርቃት አይቋረጥም፡፡


1 comment:

Anonymous said...

egzabhir kenante gar yehune

Post a Comment