የካቲት ፲፬ ፳፻፯ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓትና በትውፊት የበለፀገች መሆኗ የታመነ ነው፡፡ ሰፊ ሥርዓትና ትውፊት ያላት እንደመሆኗ መጠን የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትጾመው ጾም፤ የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትቆመው ማኅሌት በቂ ታሪክ፣ ትውፊትና ሥርዓት አለው፡፡ ያለታሪክ ያለትውፊትና ሥርዓት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጸልየው ጸሎት፤ የምትጾመው ጾም፤ የምታከብረው ሰንበትና በዓል፤ የምትዘምረውም መዝሙር የለም፡፡
በዚህ በያዝነው ወቅት የምንጾመው ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም እንደመሆኑ መጠን በዚሁ የጾም ወራት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በዘመነ ሥጋዌው ለሠራቸው የተአምራትና የትምህርት ሥራዎች መታሰቢያ በዓል በማድረግ ለእያንዳንዱ ሰንበት ስም በመስጠት በስሙ አንፃር የበዓሉን ታሪክ በመከተል ታመሰግናለች፤ ትዘምራለች፤ ትፀልያለች፤ ትቀድሳለች፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መዝሙር ንባቡን ከዜማው አስማምቶና አጠናቅሮ የተናገረው ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው በዓቢይ ጾም ውስጥ ለሚገኙት እሑዶች ሁሉ የተለየ መዝሙር ሰርቶላቸዋል፡፡ በመዝሙራቱ ውስጣዊ ምስጢር መሠረትም እያንዳንዱ እሑድ ስያሜ ተሰጥቶቸል፡፡ በዚሁም መሠረት ያሳለፍነውን ሳምንት ከቅበላው ዋዜማ ጀምሮ ዘወረደ ብለን በቤተ ክርስቲያናችን አክብረናል፡፡ በቀደመው ጽሑፋችንም የስያሜውን ትርጓሜ አይተናል፡፡ ለዛሬ ደግሞ እንደእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ የቀጣዩን ሰንበት/ሳምንት (የሁለተኛውን ሳምንት) ስያሜና ምሥጢሩን እንማማራለን፡፡