በቅድሚያ ከዘመን ወደ ዘመን ያሸጋገረን ለብርሃነ መስቀሉ ያደረሰን በሀብቱ የሳበን በረድኤቱም ያቀረበን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡
ከላይ በርዕሱ ያነሣነው ኃይለ ቃል ቅዱስ አትናቴዎስ የመስቀሉን ነገር በተናገረበት ድርሳኑ የተናገረው ነው፡፡ አስተሀፈረ ኃጢአተ በዲበ ምድር ወሰአረ መርገመ በዲበ ዕፀ መስቀል ወአብጠለ ሞተ በውስተ ሲዖል ወነሰተ ሙስና እምውስተ መቃብር”
“በምድር ላይ ኃጢአትን አሳፈረ መርገምን በመስቀል ላይ ሻረ ሞተ ነፍስን በሲዖል አጠፋ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን በመቃብር አፈራረሰ” በማለት ጌታችን ለሰው ልጆች ነጻነት እና ድኅነት የከፈለውን የቤዛነት ሥራ በተናገረበት ክፍል የተናገረው ነው የሰው ልጆች ነጻነታቸው የተዋጀው በመስቀል ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በሥልጣኑ ለይቶ ዲያብሎስን በመስቀሉ ገሎ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲዖል ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ከአጋንንት ቁራኝነት ከሲዖል ግዛት ነጻ አውጥቷቸዋልና፡፡