የጩጊ ማርያም አንድነት ገዳም ሰሜን ጎንደር ሀገረስብከት በወገራ ወረዳ ከሚገኙ ገዳማት አንዱ ነው፡፡ገዳሙ ከጎንደር ከተማ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ኮሶዬ ከተማ ሲደርሱ ሶስት ሰአት የእግር መንገድ እንደተጓዙ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡
የጩጊ ማርያም ገዳም በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተመሰረተ ጥንታዊ ገዳም ሲሆን የመሰረቱትም አባ ምእመነ ድንግል የተባሉ ጻድቅ ናቸው፡፡ገዳሙም ጻድቁ የጸለዩበት እና ከጌታችን ከመድሃኒታች ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃልኪዳን የተቀበሉበት ቅዱስ ቦታ ነው፡፡
የአባ ምእመነ ድንግል ታሪክ
አባ ምእመነ ድንግል የተወለዱት በወገራ አውራጃ ሲሆን ገና በህፃንነታቸው በእናት በአባታቸው ቤት እያሉ ጀምሮ መንፈሳዊ ትሩፋቶችን በመስራት በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ምእመነ ድንግል የምንኩስና ልብስና የእግዚአብሔር ጸጋ በመፈለግ አዳጋት ማርያም ወደ ምትባል ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዋልድባ ገዳም በመሄድ ብዙ ተጋድለዋል፤ጽናታችውን ያዩ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት አባትና መምህር እንዲሆኗቸው ቢጠይቋቸው እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ “እኔ መምህርና አባት ልሆን አይገባኝም ” በማለት እንቢ ቢሉም መነኮሳቱ አበምኔት አድርገው ሾመዋቸዋል፡፡ አባታችንም በተሾሙበት በዚህ ገዳም በከፍተኛ ተጋድሎና በእግዚአብሔር ጸጋ ብዙ መንፈሳዊ መነኮሳትንና መምህራንን በትምህርታቸው አፍርተዋል፡፡