ጾመ ነቢያት
እንኳን ለፆመ ነቢያት በሰላም ና በጤና አደረሳችሁ!፡፡ ፆሙ የሰላም የፍቅርና የደስታ ይሁንልን፡፡ ለብርሃነ ልደቱም በሰላም ያድርሰን!፡፡
ዘመኑ
ጾመ ነቢያት የተባለበት ምክንያት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለ ተፈጸመበት እንዲሁም በየዘመናቱ የተነሡ ነቢያት
እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ
እየተመለከቱ ያዩትም መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ስለ ጾሙ ስለ ጸለዩ ነው፡፡ ነቢያት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ
መወለድ፣ ወደ ግብፅ ስለ መሰደድ፣ በባሕረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቅ፣ በትምህርተ ወንጌል ጨለማውን ዓለም ስለ ማብራቱ፣
ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉና ስለ መሰቀሉ፣ ስለ ትንሣኤው፣ ስለ ዕርገቱና ስለ ዳግም ምጽአቱ
ትንቢት ተናግረው አላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍፃሜ እንዲያደርሳቸው
ፈጣሪያቸውን ተማፀኑትም እንጂ፡፡ በየዘመናቸው «አንሥእ ኃይለከ፣ ፈኑ እዴከ፤ ኃይልህን አንሳ እጅህንም ላክ» እያሉ
ጮኹ፡፡ በጾምና በጸሎት ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራትና በዓመታት ቆጠሩ፡፡
ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዌው ትንቢት በተናገረ በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ
ነስቶ ሰው ሆኗል፡፡
ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር
«የማያደርገውን አይናገር የተናገረውን አያስቀር» ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ፡፡ ለዘመነ ሥጋዌ ቅርብ የነበሩት
እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋልም፡፡ ኢሳ 58-1፡፡ በመሆኑም በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት
ስለ ተፈጸመበት ይህ ጾም «የነቢያት ጾም» ይባላል፡፡ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት የሰው ልጆች
ተስፋ የተመሰከረበት የምሥራቹ የተነገረበት ስለሆነም «ጾመ ስብከት» ይባላል፡፡